ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ሴኔት 1.2 ትሪሊዮን ዶላር በመፍቀድ የመንግሥት ሥራዎች እንዳይቆሙ ወሰነ
የአሜሪካ ምክር ቤት (ሴኔት) መንግሥት እስከ መጪው መስከረም ድረስ ወጪውን የሚሸፍንበትን የ1.2 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመመደብ ከስምምነት ላይ በመድረሱ መንግሥታዊ እቅስቃሴዎችን ከመዝጋት ታደገ።
ባለፉት ቀናት ዋነኛ መነጋገሪያ የነበረው የበጀት ጉዳይ ለአገሪቱ እንደራሴዎች ቀርቦ ከአርብ እኩለ ሌሊት በፊት ተቀባይነት ባያገኝ ኖሮ በመላው አገሪቱ ያሉ የፌደራል እና የግዛት መንግሥታዊ አገልግሎቶች በከፊል ሥራ ለማቆም ይገደዱ ነበር።
የቀረበው የበጀት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ወሳኝ ከሆኑት መንግሥታዊ ሥራዎች ውጪ ላሉ እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልገው ገንዘብ ስለሚገኝ የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን ሳያቋርጡ ይቀጥላሉ።
ሕግ አውጪዎቹ በአስፈላጊው ገንዘብ ላይ ውሳኔ ካሳለፉ በኋላ በዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ማስተካከያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለውሳኔው ተግባራዊነትም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሕጉ ላይ ዛሬ ቅዳሜ ፊርማቸውን እንዲያኖሩበት ዝግጁ ይሆናል ተብሏል።
በዲሞክራቶች እና በሪፐብሊካን ተወካዮች መካከል ከባድ ክርክር የተደረገበት ውሳኔው፤ በመጨረሻ የጋራ ስምምነት ተደርሶበት በምክር ቤቱ ተቀባይነት ማግኘቱን የዲሞክራቶች የምክር ቤት መሪ ቸክ ሹመር ተናግረዋል።
ይህ በምክር ቤቱ በስምምነት የተደመደመው የበጀት ጥያቄ ረቂቅ ሰነድ፣ ለወራት በሁለቱ ፓርቲዎች እንደራሴዎች መካከል ሲካሄድ የነበረውን መጓተት እንዲያበቃ አድርጎታል።
ውሳኔው የጸደቀው ከምክር ቤቱ ተወካዮች አጠቃላይ ድምጽ 286 ድጋፍ አግኝቶ 134 ተቃውሞ ገጥሞት ነው።
ይህም ከሚያስፈልገው የሁለት ሦስተኛ ድምጽ በጥቂት ከፍ ብሎ ነው። ሁሉም ዲሞክራቶች ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ከተቃወሙት ውስጥ አብዛኞቹ ሪፐብሊካን ናቸው።
አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ለቀረበው የበጀት በጥያቄ ድጋፍ ለመስጠት እየጨመረ ያለውን በድንበር በኩል የሚገቡ የስደተኞችን ቁጥርን ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ሕግ እንዲወጣ ቅድመ ሁኔታን አቅርበው ነበር።
በአሜሪካ እንዲህ ዓይነት የመንግሥትን የሥራ እንቅስቃሴ እንዲቆም የሚያደርግ የበጀት ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም ቆይቷል። ነገር ግን በመጨረሻው ሰዓት እንደራሴዎች ከስምምነት ላይ በመድረስ የመንግሥት ሥራዎችን ከመዘጋት ታድገዋል።
በአሜሪካ የመንግሥት ሥራ መዘጋት ሊገጥም የሚችለው ቀጣይ የበጀት ዓመት ከመጀመሩ በፊት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በሕግ እንዲጸድቅ ሳያስደርግ ሲቀር ነው።
የገንዘብ መጠየቂያው ረቂቅ ሳይጸድቅ ከቀረ በፌደራል መንግሥቱ የሚከናወኑ ሥራዎች እንዲዘጉ ያደርጋል። በዚህም የሰው ሕይወትን ወይም ንብረትን ለመጠበቅ ከሚያስፈልጉት ሥራዎች ውጪ ያሉ በጣም አንገብጋቢ ከሆኑት ውጪ ያሉት የመንግሥት ሥራዎች ይቆማሉ።
ይህም ከፌደራል መንግሥቱ ባሻገር የግዛቶች እና የአካባቢ መስተዳደሮችንም እንቅስቃሴ ያስተጓጉላል።
እንዲህ ያለው ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ያገጠመ ቢሆንም፣ በፖለቲከኞች መካከል በሚደረስ የመጨረሻ ሰዓት ስምምነት የመንግሥት እንቅስቃሴዎች ከመዘጋት ድነዋል።