በኮንጎ-ብራዛቪል ለውትድርና ቅጥር ምዝገባ ወቅት በተፈጠረ መረጋገጥ 37 ሰዎች ሞቱ

ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በኮንጎ-ብራዛቪል ለወታደርነት የቅጥር ምዝገባ ወቅት በተፈጠረ መረጋገጥ ቢያንስ 37 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።

ነዋሪዎች እንዳሉት ለቅጥር የመጡ ሰዎች ምዝገባ ወደሚካሄድበት ስታዲየም በኃይል ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውን ተከትሎ አደጋው ተፈጥሯል።

ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ መንግሥት ከ18 እስከ 25 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 1500 ወታደሮችን የመቅጠር ዕቅድ እንዳለው አስታውቆ ነበር።

የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ ሕይወታቸው ካፈለው 37 ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

አሶሺዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ምዝገባ በሚካሄድባቸው ማዕከላት እስከ 700 ሰዎች በየቀኑ ሲመዘገቡ ነበር ብሏል።

በኮንጎ-ብራዛቪል የሥራ አጥነት ቁጥር ከፍ ያለ ነው። ከአገሪቱ ወጣት ሕዝብ 42 በመቶ ያህሉ ሥራ አጥ ሲሆኑ የአገሪቱ ጦር አባል መሆን ቋሚ ተቀጣሪነትን ስለሚያረጋግጥ ወጣቶች የአገሪቱ ሠራዊት አባል መሆኑን ይመርጣሉ።

ትናንት ሰኞ ኅዳር 10/2016 ዓ.ም. ያጋጠመውን ክስተት በተመለከተ እስካሁን በዝርዝር መረጃ ባይወጣም የዐይን እማኞች እንደሚሉት ከሆነ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለምዝገባ ከሚኬል ዲ’ኦርናኖ ስታዲየም በራፍ ላይ ተገኝተው ነበር።

በራንደን ጼቱ የተባለ ተመራቂ እና ከመረጋገጥ አደጋው የተረፈ ወጣት እንደሚለው ከንጋት ጀምሮ ተሰልፎ የቆየ ቢሆንም እስከ ምሽት ድረስ ተራው እንዳልደረሰው ይገልጻል።

“አስተባባሪዎቹ የመጨረሻ የምዝገባ ቀን ነው አሉ። ለመመዝገብ ተስፋ ስለነበረን እስከ ምሽት ድረስ ቆይተናል። አንዳንዶቹ ትዕግሥት አጥተው በኃይል ወደ ውስጥ ሲገቡ መረጋገጥ ተፈጥሮ ብዙ ሰዎች ሞቱ” ሲል ለኤፒ ተናግሯል።