በኬንያ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ሕንጻ ላይ በተነሳ እሳት ቢያንስ 16 ተማሪዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Robert Maina
ረቡዕ ዕኩለ ሌሊት ናኩሩ በተባለው የኬንያ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ማደሪያ ሕንጻ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 16 ተማሪዎች ሞቱ።
ኡቱሚሻ በተባለው የሴቶች ትምህርት ቤት በተከሰተው አደጋ ከሞቱት ተማሪዎች በተጨማሪ ሌሎች 74 ተማሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ 220 የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሚኖሩበት የመኝታ ሕንጻ ላይ የተቀሰቀሰ እሳት ነው ጉዳት ያደረሰው።
የፖሊስ ሪፖርት እንዳመለከተው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ስለአደጋው ከሌሊቱ 10፡30 ላይ ለባለሥልጣናት ካሳወቁ በኋላ የነፍስ አድን ሥራ ተጀምሯል። የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር አደጋውን የተመለከተ መረጃ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገደማ እንደወጣ አሳውቋል።
የእሳት አደጋ ተከላካዮች፣ ፖሊሶች እና የነፍስ አድን ባለሙያዎችን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው ተሰማርተዋል። ባለሥልጣናት የነፍስ ማዳን ፍለጋ እያካሄዱ እና የእሳቱን መነሻ ምክንያት ለማወቅ እየጣሩ ነው።
የፖሊስ ምክትል አዛዥ የሆኑት ማሱድ ምዊንዬ እንደተናገሩት የአደጋውን መንስዔ እና የደረሰውን አሰቃቂ ጉዳት መጠን ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ ነው። ሰዎች ስለ ክስተቱ መላምት ከማሠራጨት እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።
የፖሊስ ባለሥልጣኑ ጨምረውም የኬንያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረቦች እና የፖሊስ መርማሪዎች ቦታውን ተቆጣጥረው ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
አደጋውን ተከትሎ አንዳንድ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ የማደሪያ ሕንጻ ወጥተው ወደ አቅራቢያ ቦታዎች በመሸሻቸው እነሱን ፈልጎ የማግኘት ሥራ እየተከነወነ ነው።
"አደጋው በተከሰተበት ሌሊት በድንጋጤ ከነበሩበት ወጥተው የሸሹ ተማሪዎችን ለማግኘት በአሁኑ ሰዓት የፖሊስ መኮንኖች አካባቢውን እየፈተሹ ነው" ሲሉ የፖሊስ ምክትል አዛዡ ተናግረዋል።
ባለሥልጣናት በእሳት አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ለመለየት እያንዳንዱ ተማሪ ያለበትን ቦታ ለማወቅ የስም ጥሪ በማድረግ እያጣሩ ነው።
ወደ ትምህርት ቤቱ መግባት ስላልተፈቀደ ከማለዳው ጀምሮ ወላጆች የልጆቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ ከትምህርቱ ውጪ ተሰብስበው በጭንቀት እየተጠባበቁ ነው።
የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ተማሪዎቹን ለመለየት እና ድጋፍ ለማድረግ ወላጆችን ብቻ ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዲገቡ እንደሚፈቅድ አስታውቋል።
ተማሪዎቹ በእሳት ከሚነደው ሕንጻ በፍርሃት ለማምለጥ ሲሞክሩ እንደነበረ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
ለበርካታ ተማሪዎች ሞት ምክንያት የሆነው የእሳት አደጋ በምን ምክንያት እንደተነሳ አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ሁሉም ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ ከታወቀ በኋላ እና የሚካሄደው ምርመራ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ መረጃ ይፋ እንደሚሆን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በኬንያ ውስጥ በትምህርት ቤት ላይ የሚደርስ የእሳት ቃጠሎ አዲስ አይደለም። ከዚህ ቀደምም በርካታ ተማሪዎች የሞቱባቸው የእሳት አደጋዎች ተከስተው ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት በማዕከላዊ ኬንያ በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 17 ተማሪዎች መሞታቸው ይታወሳል።















