ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ 500 የሽብር ተከሳሾችን በጅምላ ፍርድ ቤት አቆመች
ናይጄሪያ በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ የሽብር ክስ የሆነው ከ500 በላይ የትጥቅ ጥቃት ያደረሱ ተከሳሾችን የፍርድ ሂደት ጀምራለች።
ተጠርጣሪዎች ቦኮ ሀራም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ከ17 ዓመት በፊት በተነሳበት በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ሽብርተኞችን በመደገፍ እና በመደበቅ ክስ ቀርቦባቸዋል።
ከዚህን ጊዜ ጀምሮ የደኅንነት እጦቱ በበርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በመዛመት አብዛኛው በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰብን በታጣቂ ቡድኖች እና ለገንዘብ ብለው በሚያግቱ ቡድኖች እጅ እንዲወድቅ አድርገውታል።
የጅምላ የፍርድ ሂደቱ ማክሰኞ ዕለት በዋና ከተማዋ አቡጃ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጀመረ ሲሆን፤ 227 ተጠርጣሪዎች በ10 ዳኞች ፊት መቅረባቸውን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል።
በዚህ የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቦምብ እና በሌሎች ጥቃቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እንደ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ከሆነ ዕረቡ ዕለት ታጣቂዎች በምዕራብ ኒጀር ግዛት ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ተገድለዋል።
በናይጄሪያ በሽብር ጥቃቶች የሚከሰሱ በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ ተጠርጣሪዎች በአብዛኛው ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በቁጥጥር ስር ውለው ለዓመታት በእስር ይቆያሉ።
ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት አካባቢ የፀጥታ ጥበቃው ጥብቅ የነበረ ሲሆን ተጠርጣሪዎች በወታደሮች፣ ፖሊስ እና የደኅንነት ተቆጣጣሪዎች ታጅበው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ቡድን እና የናይጄሪያ ጠበቆች ማኅበርን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችም ፍርድ ቤት ተገኝተዋል።
ተከሳሾቹ በአብዛኛው በሰሜን ናይጄሪያ በተፈፀሙ ጥቃቶች ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ታጣቂዎችን በገንዘብ፣ በመሣሪያ እና ሎጀስቲክስ አቅርቦት በመደገፍ ክስ ቀርቦባቸዋል።
አምስቱ ተከሳሾች ለተጣቂዎች ምግብ እና መረጃ በመስጠት ጥፋተኝነታቸውን አምነው ከሰባት ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የአገሪቱ ዓቃቤ ሕግ ላቲፍ ፋግቢሚ የዘመቻው ግዝፈት ጉዳዩን ለመፍታት መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የቀድሞ የጦር አዛዥ እና የደኅንነት ባለሙያ የሆኑት በሽር ጋልማ ለቢቢሲ ተከፋፍሎ የሚቀጥለው የፍርድ ሂደቱ ለናይጄሪያ ሽብር ትግል "አዎንታዊ እርምጃ እና "ግዙፍ ምዕራፍ" ነው ብለዋል።
"ለዓመታት ናይጄሪያዊያን ተጠርጣሪዎችን ለተጠረጠሩበት ወንጀል ሕግን እንዲጋፈጡ ከማድረግ በቁጥጥር ስር አውለው በማቆየት ቅሬታ ነበረ።
"ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉባቸው እና ለተጎዱባቸው ይህ እፎይታን ይረዞ ይመጣል" ብለዋል።
የፍርድ ሂደቱ ተጠርጣሪዎች በተደጋጋሚ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ተለቀው ሌላ የብር ጥቃት ይፈፅማሉ የሚለውን አሉባልታም ያስወግዳል የሚል እምነት አላቸው።
ይሁን እንጂ የደኅንነት ባለሙያው አንዳንድ ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ዓመታት ስለተቆጠሩ ዳኞች ይህን ከግምት ውስጥ በማገባት ይለቀቃሉ የሚል ትንበያ አላቸው።