የትራምፕ ልዑክ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር "በጣም ጥሩ ውይይት" ማድረጋቸውን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አማች እና የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ጃርድ ኩሽነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች እና የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ጃርድ ኩሽነር በአሜሪካ የሚደገፈውን የጋዛ የሰላም ዕቅድ እንደገና ለማስጀመር ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ረዥም ውይይት ማድረጋቸውን ቃል አቀባያቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ውይይቱ "በጣም ጥሩ ነበር" ያሉት ኩሽነር፣ በ30 ቀናት ውስጥ የተወሰኑ ለውጦች እንደሚኖሩ እና የተወሰኑ የሐማስ የጦር መሣሪያዎችን ማስወጣት ይጀመራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ለፎክስ ኒውስ ገልጸዋል። ለዚህም ከሁለቱም ወገኖች ትብብር እንደሚያስፈልግ መልዕክተኛው አክለዋል።

እስራኤል ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቁን ሳይፈታ በጋዛ መልሶ ግንባታ እንደማይኖር በፕሬዚደንት ትራምፕ ከተሰየመው የሰላም ቦርድ ጋር መስማማቷን ገልጻለች።

ኩሽነር ከኔታንያሁ ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድሞ በአዲሱ የሐማስ መሪ ከተመራ ልዑክ ጋር እሁድ ዕለት በግብፅ ኻሊል አል ሃያ ተገናኝተው እንደነበር አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ኩሽነር እሑድ ዕለት ከቡድኑ ጋር ብዙም ያልተለመደ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ ሐማስ ቦርዱ እስራኤል የሰላም እቅዱን እንድትቀበል "እንዲያሳስብ" ጠይቋል።

ባለፈው ሳምንት እስራኤል 15 ነጥቦችን የያዘውን የጋዛ የሰላም ዕቅድ እንደማትቀበል ገልጻ ነበር።

የሰላም እቅዱ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ እንዲወጡ እና ጋዛ በሲቪል በሚመራ አዲስ የፍልስጤም አስተዳደር መልሳ እንድትገነባ ያሳስባል። ሆኖም ኔታንያሁ ሐማስ "በተጨባጭ" ትጥቁን ካልፈታ ሠራዊታቸው እንደማይወጣ ተናግረዋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛው ኩሽነር ሰኞ ዕለት ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት፣ ከኔታንያሁ ጋር ያደረጉት ውይይት ለአራት ሰዓታት የዘለቀ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"መፍታት የምንችላቸው ተጨባጭ የሆኑ ስጋቶች ተነስተው ነበር" ያሉት ኩሽነር፣ እስራኤል የሰላም ዕቅዱን ከተቀበለች ሁለቱም ወገኖች የሚያሸንፉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

ከሐማስ ጋር ስላደረጉት ውይይትም የተጠየቁት ኩሽነር፣ " ትክክል የሆኑ ነገሮችን ነው ያነሱት፤ ሆኖም አስከፊ ወንጀሎችን የፈፀመ የሽብር ድርጅትን ማመን በጣም ከባድ ነው" ብለዋል።

ሆኖም ሌላ ገንቢ ስብሰባ እንደሚኖር ጠቅሰው፣ "እንዲነጋገሩ እድል እንሰጣቸዋለን" ብለዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡትም የሰላም ቦርዱ መልዕክተኞች ኒኮላይ መላድኖቭ እና ቶኒ ብሌር ሰኞ ዕለት ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው ነበር።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ ፣ "ኔታንያሁ እና ቦርዱ ጥልቅ እና ገንቢ ውይይቶች እንዳካሄዱ" ገልጿል።

ጨምሮም ሁለት ቡድኖቹን ለማቋቋም መስማማቱን እና አንደኛው ትጥቅ የሚያስፈታ እና ጋዛን ከወታደራዊ ቁጥጥር ነፃ የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል። ይህም እስራኤልም ሆኑ ቦርዱ ጋዛን መልሶ ከመገንባት በፊት ሊከናወን ይገባል ያሉት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብሏል።

ሁለተኛው ደግሞ ጽዳትን፣ ንጹህ ውሃ እና የኅብረተሰብ ጤና ጉዳዮችን ላይ የሚያተኩር ነው።

ሆኖም በርካታ እስራኤላውያን ሐማስ ትጥቅ ይፈታል ብለው አያምኑም።

የሰላም ቦርዱ በፕሬዚደንት ትራምፕ የሚመራው እና በጋዛ ሰላም ለማምጣት ቀደም ብሎ እንደ ዓለም አቀፍ ድርጅት የተቋቋመው ሲሆን ሌሎች ዓለም አቀፍ ግጭቶችን ለማካተት ሰፍቷል።

የሰላም ቦርዱ ምንም እንኳን ኔታንያሁ አዲሱን ፍኖተ ካርታ አልቀበልም ቢሉም የጋዛ የሰላም እቅድ መቀጠል እንደሚችል ማሳየት ይፈልጋሉ።

ሐማስ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ የሚወጡ ከሆነ በምዕራፍ በምዕራፍ መሣሪያውን ለማስረከብ ተስማምቷል። ነገር ግን እስራኤል ወታደሮቿን ከማስወጣቷ በፊት ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቁን መፍታት እንዳለበት አቋሟን ገልፃለች።

እስራኤል የሰላም እቅዱን አልቀበልም ብትልም በጋዛ የምትፈፅመው ጥቃት ጋብ ብሏል፤ ጥቃቶች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ነው።

ባለፈው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ተግባራዊ የሆነው የተሰስ አቁም ስምምነት አሁንም በተግባር ላይ አለ። ሆኖም የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ለማለት በሚቻል ሁኔታ ጥቃቶችን ፈፅሟል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከተኩስ አቁሙ ስምምነት ወዲህ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አሃዙ በተባበሩት መንግሥታትም ይታመናሉ። ዓለም አቀፉ የሕፃናት አድን ድርጅት ( ዩኒሴፍ) ቢያንስ 300 ሕፃናት ተገድለዋል ብሏል።