በመካከለኛው ምሥራቅ የተደረሱት ሁለት የተኩስ አቁም ስምምነቶች የያዙት ተስፋ እና አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በመካከለኛው ምሥራቅ አንድ ሳይሆን ሁለት የተኩስ አቁሞች መኖራቸው ለታሪካዊ ስምምነት የተመቻቸ ጊዜ አስመስሎታል።
በኢራን እና በሊባኖስ የተደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነቶች ሁለቱም "የሚዋልሉ" ጸንተው ለመቆም የሚውተረተሩ ተብለው ሲገለጹ ይደመጣል።
ይህ ግን በተኩስ አቁሞች ዘንድ የተለመደ ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ ጎልቶ የሚሰማው የጦርነት ነጋሪት፣ የሚሳዔሎች ውንጨፋ፣ የሮኬቶች እና የድሮኖች ተኩስ ሰከን ሲል ስምምነቱ ዕድል መያዙ አልያም አደጋ ማርገዙ ይታያል።
እውነቱን ለመናገር ሐሙስ ምሽት በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ መካከል የሚደረገው ጦርነት ለአስር ቀናት እንዲቆም መደረጉ ለኢራን ድል ነው።
በቴህራን ያለው አገዛዝ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቆ ነበር፤ ያለበለዚያ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት ሊቀጥል፤ ሊሰምርም አይችልም ሲል ተደምጧል።
ኢራን አሁን የተኩስ አቁሙን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ "ሙሉ በሙሉ ክፍት" መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥታለች።
ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በኢዝላማባድ የተደረገው ረዥም ድርድር እንደሚያሳየው፣ በሊባኖስ የነበረው ጦርነት እየቀጠለ ቢሆንም ከመግባባት ላይ ለመድረስ ዕድል መኖሩን አመላክቷል።
ነገር ግን ኢራን እና ፓኪስታን በተኩስ አቁም ላይ ሊባኖስ መካተት እንዳለባት አጥብቀው ተሟግተዋል።
በእስራኤል ላሉ አንዳንዶች አሁንም ኢራን ጨዋታው ሜዳ ላይ የበላይ ሆና ወጥታለች። ዛሬም የእስራኤል የረዥም ጊዜ ጠላት ሁኔታዎችን የምትዘውር እና የቀጣናውን ፖለቲካ የምትወስን ሆናለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለአሜሪካው ወዳጃቸው ፍላጎቶች እጃቸውን ሰተዋል ብለው የተቆጡም አልጠፉም።
ታዋቂው ሃዮም ሺሪት አቪታን ኮሄን "ትናንት ሄዝቦላህ አለቃው እና የሊባኖስ ጦር አሁንም መሪውን እንደጨበጡ መሆናቸውን እና በቀጣናው ውስጥ የሚሆነውን ነገር መቆጣጠራቸውን እንደሚቀጥሉ የመጨረሻ ማረጋገጫ አግኝቷል" ሲል ጽፏል።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በእነዚህ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በተጋመዱ ግጭቶች ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ተፋላሚዎች ከቅርብ ጊዜው ስምምነት የየድርሻቸውን ማግኘታቸውን አይቀርም።
ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በኢራን ላለው አመራር፣ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በማድረጋቸው ዕውቅና ይቸራቸዋል።
ኔታንያሁ በበኩላቸው የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ እንደሚቆዩ ሊያስረዱ ይችላሉ።
ለሊባኖስ መንግሥት ደግሞ ከወራት ሙከራ እና ጥረት በኋላ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ድርድር የማድረግ ዕድል አግኝቷል።
ሄዝቦላህ ደግሞ ምንም እንኳ አሁንም "ጣቴ በቃታው ላይ" ቢሆንም የተኩስ አቁሙን አከብራለሁ ብሏል።
ነገር ግን ትጥቅ እንደማይፈታ አጥብቆ ይናገራል።
"ትክክለኛው፣ እውነተኛው የተኩስ አቁም ስምምነት እስኪደረግ ድረስ፣ እስራኤል እስክትወጣ ድረስ አይሆንም። እስረኞቹ ከመመለቀቃቸው በፊት፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ከመመለሳቸው በፊት እንዲሁም ከዳግም ግንባታው በፊት አይሆንም። እስከዚያው ድረስ ስለ ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያዎች ማውራት አይቻልም" ሲሉ የቡድኑ ከፍተኛ መሪ ዋፊቅ ሳፋ ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በለንደን የሚገኘው የቻተም ሃውስ የምርምር ማዕከል አባል የሆኑት ሊና ካቲብ እንደተናገሩት የተኩስ አቁም ስምምነቱ እስራኤልና ሊባኖስ የቀጥታ ንግግራቸውን እንዲቀጥሉ መንገድ ይከፍታል፤ ነገር ግን በሁለቱ መካከል የሰላም ስምምነት እንዳይደረግ ብዙ እንቅፋቶች አሉ።
"ጉዳዩ በጣም የተወሳሰበ ነው" የሚሉት ተመራማሪዋ "ከድንበር ማስከበር ጋር፣ ሄዝቦላህን የጦር መሣሪያ ከማስፈታት እና እስራኤል ከሊባኖስ ግዛት ለቅቃ ከመውጣቷ ጋር የተያያዘ ነው።"
እስራኤል እና ሊባኖስ እአአ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ በጦርነት ውስጥ ነበሩ ማለት የሚቻል ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የላቸውም።
ነገር ግን ካቲብ ይህ ስምምነት ኢራን በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ከማጠናከር ይልቅ፣ በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን በእስራኤል እና በሊባኖስ አምባሳደሮች መካከል የተደረገው ቀጥተኛ ውይይት፣ ሊባኖስን ከኢራን እጅ ፈልቅቆ የማስወጣቱ መንገድ ተጀምሯል ሲሉ ይከራከራሉ።
"የቀጣናው የኃይል ሚዛን ከኢራን እየሸሸ ነው" የሚሉት ተመራማሪዋ "አሁን ሊባኖስን እንደ መደራደሪያ መጠቀም አትችልም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ነገር ግን ብዙው ነገር አሁንም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚሆነው ሌላኛው የዲፕሎማሲ ሂደት ላይ የተመሰረተ ነው።
በኢዝላማባድ ይካሄዳል የተባለው እና በስፋት የሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር ድርድር የሚሳካ ከሆነ አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን የማደፍረስ ባሕሪ የሚቀንስ እርምጃ መውሰድ ይፈልጋሉ።
በተለይ ለእስራኤል፣ ኢራን በየመን ውስጥ ላሉ ሁቲዎች፣ የሊባኖሱን ሄዝቦላህ፣ እና ለጋዛው ሐማስ የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ትፈልጋለች።
ይህም ማለት ኢራን ለአስርት ዓመታት እስራኤልን ለማስፈራራት እና ለማስጨነቅ የቻለችባቸውን ኃይሎች ታጣለች ማለት ነው።
ኢራን በቀጣናው ወሳኝ የሆኑትን የተጽዕኖ መሣሪያዎቿን በቀላሉ አትተውም።
ነገር ግን ይህ ከፊታቸው ካሉት ከባድ ፈተናዎች አንዱ ብቻ ነው።
ሌሎቹ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዕጣ ፈንታ እና የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የወደፊት ዕጣ የተወሰነ ድርድር ይጠይቃል።
ትራምፕ እንደተለመደው፣ ከኢራን ጋር ከስምምነት ለመድረስ "በጣም ቅርብ" ነን፣ ጦርነቱ "ያለምንም እንከን" እየተካሄደ መሆኑን በመግለጽ አሁንም ሁኔታዎች በእርሳቸው ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ለማሳየት ይሞክራሉ።
ኢራን ባለፈው ዓመት በኢስፋሃን በተፈጸመው ድብደባ ፍርስራሽ ስር የተቀበረውን 440 ኪሎ ግራም (970 ፓውንድ) የሚመዝን የበለፀገ ዩራኒየም ለማስረከብ መስማማቷንም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማይል ባጋይ ይህንን የትራምፕ ሃሳብ ውድቅ አድርገው "ዩራኒየም ወደ አሜሪካ መተላለፉ እንደ አማራጭ አልቀረበም። የኢራን የበለፀገ ዩራኒየም ለእኛ እንደ ኢራን አፈር ቅዱስ ነው፤ እና በምንም ዓይነት ሁኔታ ወደየትኛውም ቦታ አይተላለፍም" ብለዋል።
በኒውክሌር ሰነዱ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ፈጽሞ እንደማትገነባ ቃል መግባት እንዲሁም ማበልጸጊያውን ለምን ያህል ጊዜ ለማቆም ፈቃደኛ እንደምትሆን ስምምነት ማድረግን ይጠይቃል።
ከዚያም የኢራን ሌላ የጦር መሳሪያ አለ፤ ሁልጊዜም በአገሪቱ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም በቅርብ ጊዜ ብቻ የተተገበረ ነው፤ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋት።
ኢራን በዚህ ጠባብ የውሃ መስመር ውስጥ የባህር ትራንስፖርትን ለመቆጣጠር አዲስ አሰራር እንደምትፈልግ ትናገራለች።
ይህም ከኦማን ጋር በመሆን ከባህር ሰላጤው ውስጥ የሚወጣውን እና የሚገባውን ለመቆጣጠር እንደ ሉዓላዊ መብቷ የሚቆጥር የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደስታ እንደሚቀበሉ በመግለጽ የባህር ወሽመጡ "በቀሪው የተኩስ አቁም ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት ነው" ብለዋል።
በሌላ አነጋገር ሆርሙዝ እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ክፍት ይሆናል ማለታቸው ነው።
አንድ ማስጠንቀቂያ አለ፡- መርከቦቹ አራግቺ "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ወደቦች እና የባህር ድርጅት አስቀድሞ እንደገለጸው የተቀናጀ መንገድ" ብሎ የጠራውን እንዲጠቀሙ ይጠበቃል።
እነዚህ አዎንታዊ ለውጦት በቀጣናው ውስጥ ቢኖሩም ተደራዳሪዎች መነጋገር ያለባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
እአአ በ2015 ከኢራን ጋር የተደረሰው የመጨረሻው ስምምነትን ለመደራደር 20 ወራት ያህል የፈጀ ሲሆን የኒውክሌር ጉዳዩን ብቻ ነው መፍታት የቻለው። ትራምፕ አሜሪካን ከዚህ ስምምነት በ2018 አስወጥተዋል።
ትራምፕ ራሳቸውን በፍጥነት ከስምምነት ላይ የሚደርሱ መሪ አድርገው መሳል ይፈልጋሉ። ያደረጓቸው ስምምነቶች በትክክል ምን እንዳሳኩ ወደ ኋላ መለስ ብለው አይመለከቱም።.
እንደ አውሮፓውያኑ በ2018-19 ከሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ያደረጉት ሁለት ጉባዔዎች ብዙም ውጤት አላስገኙም። ፒዮንግያንግ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ቀጥላለች።
ባለፉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ ከተከሰቱት ነገሮች በኋላ፣ አንድ ዓይነት የዲፕሎማሲ ሂደት በጥሩ መስመር ላይ እንደሚገን ያሳያል።
ይህ የዲፕሎማሲ መንገድ ደግሞ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ድጋፍ አግኝቷል።
ወደ ጦርነት እንዳይመለስ ለመከላከል በቂ ነው? ይህንን ግን ትራምፕ እንኳን በበቂ አያውቁም።















