ቻይና እና ሩሲያ ለምን 'የቅርብ ወዳጆች' ሆኑ?

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ያለፈው መስከረም የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቲያናሚን አደባባይ ሲዘዋወሩ ስለ ቀዶ ሕክምና እያወሩ ነበር።
ቤይጂንግ ውስጥ እየተዘዋወሩ ሳለ የሰዎችን የሰውነት ክፍሎች በቀዶ ሕክምና መለወጥ ሕይወትን እንደሚያራዝም መከሩ።
የፑቲን አስተርጓሚ "የሰዎች ሰውነት በተከታታይ ሊለዋወጥ ይችላል። ብዙ በኖርን ቁጥር ወጣት እንሆናለን። ሞትን ማምለጥ እንችልም ይሆናል" ሲሉ ተሰምቷል።
የዢ አስተርጓሚ ደግሞ "በዚህ ክፍለ ዘመን እስከ 150 ዓመት መኖር እንደሚቻል የሚገምቱ አሉ" ሲሉ ተደምጧል።
ሁለቱ መሪዎች የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ይናገራሉ። አገራቸውን ለአሥርታት የመሩት ፕሬዝዳንቶች በቅርቡ ሥልጣን የሚለቅቁ አይመስልም።
የሁለቱ መሪዎች ምሥጢራዊ ነው። በቲያናሚን አደባባይ ያደረጉት ንግግር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳላቸው በጥቂቱ ያሳያል።
ሁለቱ አገራት የመልካም ጎረቤትነት ስምምነት ከተፈራሙ 25 ዓመት አስቆጥረዋል። ይሄንን ታሳቢ በማድረግም በዚህ ሳምንት ፑቲን ወደ ቤይጂንግ ያቀናሉ።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ቤይጂንግ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ከወርቅ የተሠራ መመገቢያ ቀርቦላቸዋል፤ ጥንታዊ ቤተ መቅደሶችን ጎብኝተዋል።
ስለ ፑቲን ጉብኝት ብዙም መረጃ አልወጣም። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ስለ ጉዞው የሚሰማው ከመሪዎቹ በቀጥታ ነው ብለዋል።
ዢ ጂንፒንግ ከትራምፕ ጋር ሲገናኙ ስለ ፑቲን ማውራታቸው ተሰምቷል።
ለውጭ ጎብኚዎች ክፍት የማይሆነውን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ቅጥር ጊቢን ትራምፕ ጎብኝተዋል። ፑቲንም ይሄንን ሥፍራ የመጎብኘት ዕድል አግኝተዋል።
ትራምፕ የቻይናውን ፕሬዝዳንት ከፑቲን በተሻለ ለመቅረብ ይሞክራሉ ብለው የጠበቁ ነበሩ፤ የተሳካ ግን አይመስልም።
ቻይና እና ሩሲያ ወዳጅነታቸውን "ገደብ አልባ" ብለው ይገልጻሉ።

የቻይና የበላይነት
የሁለቱ አገራት ግንኙነት የቻይና የበላይነት የሚታይበት እንደሆነ የካርኒጌ ራሽያ ዩሬዥያ ሴንተር የባለሙያዎች ቡድን ዳይሬክተር አሌክሳንደር ጋብሮቭ ይናገራሉ።
"ቻይና ሩሲያን በኪሷ አስገብታለች። ፈላጭ ቆራጭ ናት" ይላሉ።
ምጣኔ ሃብትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎችም ያለው የአገራቱ ግንኙነት ተመሳሳይ መልክ አለው።
ቻይና የሩሲያ ዋነኛ የንግድ አጋር ናት። ከቻይና ዓለም አቀፍ ንግድ ሩሲያ 4 በመቶ ብቻ ድርሻ ነው አላት።
ቻይና ከየትኛውም አገር በላቀ ለሩሲያ ሸቀጥ የምትልክ ሲሆን፤ ምጣኔ ሃብቷም የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ከቻይና ውጭ የንግድ አጋር እንዳይኖራት አስገድዷል። አሜሪካ ማዕቀብ የጣለችበት እና ዩናይትድ ኪንግደም ከ5ጂ ኔትወርክ ያስወጣችው ሁዋዌ ዋነኛ ገበያው በሩሲያ ይገኛል።
ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነቷ የተቀዛቀዘው ቻይና በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀዳሚ ምርጫ ለመሆን ትፎካከራለች።
የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሩሲያ በዋናነት የቻይናን መሣሪያዎች እየተጠቀመች ነው።
ብሉምበርግ በቅርቡ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ሩሲያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተጣለባትን ማዕቀብ በማለፍ ከምትፈልጋቸው ምርቶች 90 በመቶ የሚሆነውን ከቻይና ትገዛለች። ግብይቱ ከአምናው 10 በመቶ ጨምሯል።
ሩሲያ ከቻይና ጋር ያላትን አለመመጣጠን በቀላሉ እንደማትወስደው የሩሲያ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ባለሙያ ዲሚትሪ ትሬኒን ይናገራሉ።
ሩሲያ "ለማንም አልበገርም" የሚል አቋም እንደምታራምድ ያክላሉ።
"ከቻይና ጋር ሩሲያ ያላት ግንኙነት እኩል መሆን አለበት። ሩሲያ እኩል አጋር እንጂ የበታች መሆን አትችልም" ይላሉ።
ሩሲያ ከቻይና ውጪ ያሏት አማራጮች ውስን ናቸው። የቻይና የንግድ ትስስር ለሩሲያ የሕልውና ጥያቄ ነው።
ቻይና ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት አሳስቧት ከሩሲያ ጋር ያላትን ትስስር ብታላላ የሞስኮ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መለወጥ ይኖርበታል።
ሩሲያ ከአቋሟ ፈቀቅ የማትል አገር መሆኗ በቻይና የበላይነት ሙሉ በሙሉ እንዳትዋጥ ያግዛታል።

የፎቶው ባለመብት, Kremlin Press Office/Anadolu via Getty Images
በቻይና፣ ግላስጎው ዩኒቨርስቲ የደኅንነት ጥናት መምህር ማርሲን ካዝማሪስኪ እንደሚሉት ቻይና ሩሲያን የሚያስቀይም ነገር እንዲፈጠር አትሻም።
"ቻይና በሩሲያ ጉዳዮች ቁጥብ አካሄድ ታራምዳለች። ሩሲያን መግፋትም አትፈልግም" ይላሉ።
ቻይና ይሄንን ፖሊሲ የምታራምደው ያለ ምክንያት አይደለም። ቤይጂንግ የበላይነት ቢኖራትም እንኳን ሞስኮ ኩሩ ናት።
የካርኒጌ ራሽያ ዩሬዥያ ሴንተር ዳይሬክተር አሌክሳንደር "ቻይና ሩሲያን ለማስገደድ ብትሞክር ሞስኮ አትቀበልም" ሲሉ ይገልጻሉ።
በአውሮፓውያኑ 2023 ጂንፒንግ ወደ ሩሲያ ተጉዘው በዩክሬን ላይ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንዳትጠቀም ቢጠይቁም፤ ከቀናት በኋላ ሞስኮ በቤላሩስ የኒውክሌር መሣሪያ ማከማቻ እንደምትገነባ አስታውቃለች።
ሩሲያ በምታሳልፋቸው ውሳኔዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት ቦታ እንደሌለው ለማሳየት የተወሰደ እርምጃ ነው።
ሩሲያ ዩክሬንን የመውረሯ ጉዳይ ቻይናም ታይዋንን ልትወርር የምትችልበት ዕድል እንዳለ ጠቋሚ ይመስላል።
"ሩሲያ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዋ አሁንም ገበያ ላይ መዋል የሚችል ነው። የቻይናን መሣሪያዎችም ትሞክራለች" በማለት ተንታኙ ያስረዳል።
የሩሲያ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ለቻይና ስትራቴጂያዊ ጥቅም አለው። ሁለቱ አገራት "የነዳጅ ምርት ትብብራቸውን ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መቃረባቸውን" ፑቲን በቅርቡ ተናግረዋል።
የሩሲያው ጋዝፕሮም እና የቻይናው ናሽናል ፔትሮልየም ኮርፖሬሽን በጥምረት ጋዝ የሚያስተላልፉበት መስመር ለመዘርጋት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተዘግቧል። ሳይቤሪያ 2 የተባለው የነዳጅ ቧንቧ መስመር ለመገንባት ሲደረግ የነበረው ንግግር መሀል ላይ ቢቋረጥም በስተመጨረሻ ስምምነት ተፈርሟል።
ይሄ መስመር ከተዘረጋ በሞንጎሊያ በኩል በ50 ቢዮን ኪውቢክ ሜትር የሩሲያን ጋዝ ለቻይና ያደርሳል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ቻይና ሌሎች አማራጮችን እንድታማትር አስገድዷል።
የሩሲያን ነዳጅ መውሰድ አዋጭም ዘላቂነት ያለው ንግድን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock
ከጠላት ይልቅ ወዳጆች
የቻይና እና የሩሲያ ግንኙነት ከመደበኛው የአገራት ትስስር የተለየ መልክ አለው።
በሞስኮ የአውስትራሊያ ኤምባሲ የቀድሞ ምክትል የተልዕኮ ኃላፊ ቦቦ ሎ እንደሚናገሩት፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንካራ ለመሆኑ ምክንያቱ አንድም ወታደራዊ እና ስትራቴጂያዊ ትስስራቸው ነው።
"ትብብር ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ትስስር ነው ያላቸው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ምዕራባውያን የቻይና እና የሩሲያን ግንኙነት በሁለት መንገድ ይገልጹታል። አንደኛው "የአምባገነኖች ትስስር" የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለመፍረስ የተቃረበ ወዳጅነት በሚል ነው።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሠረት ምዕራባውያንን ለመገዳደር ያላቸው ፍላጎት መሆኑም ይታመናል።
ሁለቱም የምዕራባውያን አገላለጾች የቻይና እና የሩሲያን ግንኙነት በጥቅሉ አያሳዩም።
ሁለቱ ጎረቤቶች በሌላ የማይተካ ወዳጅነት የመሠረቱት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማድረግ ነው። ትኩረታቸው የሚያስሟሟቸው ነጥቦች ናቸው።
ሁለቱ አገራት ከምዕራባውያን ጋር ያላቸው ግንኙነት ቢታደስም እንኳን የሚያስማሟቸው ነገሮች ሚዛን ስለሚደፉ ትስስራቸው እንደማይላላ ቦቦ ሎ ያስረዳሉ።
ቻይና እና ሩሲያ 4,300 ኪሎ ሜትር ድንበር ይጋራሉ። ምጣኔ ሃብታቸውም እርስ በርስ ይደጋገፋል። ሩሲያ በዋነኛነት የነዳጅ አቅራቢ ስትሆን ቻይና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ትመራለች።
አሜሪካ የምትመራው የዓለም ፖለቲካዊ አሰላለፍ ሁለቱንም አገራት አያስደስትም።
ከሁለቱ አገራት በተለየ ሁኔታ ምዕራባውያን ከሰብአዊ መብት ጋር በተያያዘ ማዕቀብ በመጣል ጫና ለማሳደር ይሞክራሉ።

ቻይና በዢንጃንግ ግዛት የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ትከሰሳለች። ቤይጂንግ ክሱን ታስተባብላለች።
ሩሲያ በተቃዋሚ ፖለቲከኛው አሌክሲ ናቫልኒ ሞት ተጠያቂ ስለምትደረግ ምዕራባውያን አገራት ከሞስኮ ጋር አብሮ ለመሥራት አይፈቅዱም። ቻይና ግን ጉዳዩ ብዙም ግድ አይሰጣትም።
የካርኒጌ ራሽያ ዩሬዥያ ሴንተር ዳይሬክተር አሌክሳንደር "በዢንጂንግ ጉዳይ ወይም በናቫልኒ ግድያ አንዳቸው ሌላኛቸውን አይተቹም። በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይም ተመሳሳይ አቋም ይዘው ይቀርባሉ፤ ይህም ትስስራቸውን ያጠናክራል" ይላሉ።
ግንኙነትን ማጠናከር ከሶቪየት ኅብረት ዘመን አንስቶ የሚታይ መሆኑን የሚገልጹት ተንታኙ፤ ቻይናም ለዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ትስስር መዘርጋትን እንደምታስቀጥል ያስረዳሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቻይናዊ ተንታኝ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት ግንኙነት "አንድነት እና ዘላቂነትን" ለማሳየት ቢሞከርም "ከታይታ ያለፈ" እንዳልሆነ ያምናሉ።
ልዩነትን ገሸሽ አድርጎ በጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። ሁለቱም አገራት "የምዕራባውያንን የበላይነት" ይኮንናሉ።
ሩሲያ የአሜሪካን የበላይነት የተሻገረ የዓለም አሰላለፍን ማየት ትፈልጋለች። ቻይና ግን በቀጥታ ይሄንን መተግበር አትሻም።
ቤይጂንግ ቀስ በቀስ በሚወሰዱ እርምጃዎች ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማስፈንን ታስቀድማለች።
የኢራንን ጦርነት ብንመለከት፤ ቻይና የሰጠችው ምላሽ ቁጥብ ከመሆኑም ባሻገር ትራምፕን ተቀብላ አስተናግለች።
"ቻይና ተንኳሽ የመሆን ወይም በር የመዝጋት ፖሊሲን አታራምድም። ከዋሽንግተን ጋር መቆራረጥን አትፈልግም" ሲሉ ተንታኙ ይገልጹታል።
ሞስኮ ደግሞ ከዚህ የተለየ አካሄድ ትከተላለች።

የፎቶው ባለመብት, Sputnik/ Kremlin/ PA/Shutterstock
ሰብአዊው ገጽታ
የቻይና እና ሩሲያ ግንኙነት ከጂኦ-ፖለቲካ እና ደኅንነት አንጻር ብቻ ሲታይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ችላ ይባላል።
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ወዳጆች መሆናቸውን ደጋግመው ይናገራሉ። ከሰሞኑ ፑቲን ለ25ኛ ጊዜ ቤይጂንግን ይጎበኛሉ።
በከፍተኛ ፖለቲከኞች ደረጃ ግንኙነቱን የሚያጠናክር ጉዞ ይሆናል።
በቻይና የቀድሞ የብሪታኒያ ዲፕሎማት ቻርልስ ፓርቶን በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ዜጎች ያላቸው የባህል ትስስር ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
"ቻይናውያን ሞስኮ መማር እና መኖር ይፈልጋሉ? አይፈልጉም። ሩሲያውያን ምርጫው ቢሰጣቸው በምዕራባውያን አገራት ኢንቨስት ማድረግ ይመርጣሉ። ከቤይጂንግ ይልቅ ፓሪስ ወይም ለንደን ቤት መግዛት ይሻላቸዋል።"
የካርኒጌ ራሽያ ዩሬዥያ ሴንተር ዳይሬክተር አሌክሳንደር በዚህ ዕይታ አይስማሙም።
የሁለቱ አገራት ዜጎች ግንኙነት ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መምጣቱን ይገልጻሉ።
በተለይም አውሮፓውያን የቪዛ ማዕቀብ መጣላቸው ሩሲያውያን ወደ ቻይና እንዲያዘነብሉ አድርጓል።
ሁለቱ አገራት ያለ ቪዛ የመንቀሳቀስ ስምምነት ስላላቸው በሰዓታት ውስጥ ከሞስኮ ቤይጂንግ መግባት ይቻላል።
የምዕራባውያን ማዕቀብ ሲጠናከር ሩሲያውያን የቻይናን ስልክ እና መኪና ይጠቀማሉ።
"ያለ ቪዛ የመጓዝ ስምምነት ቻይና ከመቼውም በላይ ለሩሲያ ቅርብ እንድትሆን አድርጓል። ነጻ የትምህርት ዕድሎችም የሁለቱን አገራት ዜጎች አስተሳስረዋል" በማለት የፖለቲካ ተንታኙ ያብራራሉ።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ድክመቶች ቢኖሩትም እንኳን ወደ ቁርሾ የማምራት ዕድሉ ጠባብ ይመስላል።
በሞስኮ የአውስትራሊያ ኤምባሲ የቀድሞ ከፍተኛ ዲፕሎማት ቦቦ ሎ "ግንኙነታቸው ጠንክሮ ቀጥሏል። መክሸፍ እንደሌበት ሁለቱም ወገኖች ይስማማሉ። አንዳቸው ከሌላኛቸው ውጪ አማራጭ የሌላቸው መሆኑ ትስስሩን የበለጠ ያጠብቀዋል" ሲሉ ይገልጹታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images














