ኢራን፣ አሜሪካ ጥቃቶችን ዳግም መጀመር መወሰኗን ገልጻ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስታወቀች

የኢራን ጦር እሁድ ዕለት አሜሪካ የምትፈጽመውን ድብደባ ለመቀጠል እንደምትፈልግ የሚጠቁም መረጃ አንደደረሰው አስታወቀ። ጦሩ የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በሆነው ኢሪብ ላይ ባስተላለፈው መግለጫ “ ባገኘነው መረጃ መሠረት ወንጀለኛዋ አሜሪካ በአውሮፓ በተደረገ የጋራ ስብሰባ ላይ ከአንዳንድ የአካባቢው አገራት ፈቃድ በማግኘቷ፣ በኢራን ላይ እርምጃዎችን እንደገና ለመውሰድ ወስናለች” ብሏል። ጦሩ ዋሺንግተን “ስህተት የምትሠራ ከሆነ” በቀጣናው በሚገኙ አጋሮቿ ላይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን፣ አሜሪካ ጥቃቶችን ዳግም ለመጀመር መወሰኗን ገልጻ የአጸፋ እርምጃ እወስዳለሁ አለች

    የኢራን ጦር እሁድ ዕለት አሜሪካ የምትፈጽመውን ድብደባ ለመቀጠል እንደምትፈልግ የሚጠቁም መረጃ አንደደረሰው አስታወቀ።

    ጦሩ የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በሆነው ኢሪብ ላይ ባስተላለፈው መግለጫ “ ባገኘነው መረጃ መሠረት ወንጀለኛዋ አሜሪካ በአውሮፓ በተደረገ የጋራ ስብሰባ ላይ ከአንዳንድ የአካባቢው አገራት ፈቃድ በማግኘቷ፣ በኢራን ላይ እርምጃዎችን እንደገና ለመውሰድ ወስናለች” ብሏል።

    ጦሩ ዋሺንግተን “ስህተት የምትሠራ ከሆነ” በቀጣናው በሚገኙ አጋሮቿ ላይ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።

    “የአካባቢው አገራት በእስላማዊቷ የኢራን ሪፐብሊክ ላይ በሚከተሉት ባለሁለት አቅጣጫ ፖሊሲ በመቀጠል፣ . . . ሉዓላዊት በሆነችው ኢራን ላይ ለሚፈጽመው ጥቃት ድጋፍ የሚሰጡ ከሆነ፤ ሁሉም በዚህ ክፉ ድርጊት ተባባሪ እንደሆኑ እንደሚቆጠሩ እና ከኢራን ኃያል የጦር ኃይሎችም መታቀብን ወይም ጨዋነትን መጠበቅ እንደማይችሉ እናስጠነቅቃለን” ሲል መግለጫው አመልክቷል።

    አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ቴህራን በቀጣናው በሚገኙ አገራት እና የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።

    ኢራን በተጨማሪም የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታለች።

    ዋሺንግተን እና ቴህራን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም በሆርሙዝ መከፈት ላይ ባለመግባባታቸው ስምምነቱ ፈርሷል።

  2. አሜሪካ የገባችውን ግዴታ እስክትወጣ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ኢራን አስታወቀች

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ፣ አሜሪካ ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ለፈረመችው ስምምነት እስክትገዛ እና የቴህራንን ቅድመ ሁኔታዎች እስክታሟላ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዝግ ሆኖ ይቆያል አሉ።

    ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እሁድ ዕለት ለፓርላማው አባላት “በአሸማጋዮቻችን በኩል በግልጽ አቋማችንን አሳውቀናል” ብለዋል።

    ኢሪብ የዜና ወኪል እንደዘገበው "ጠላት የማታለል እና የአንድ ወገን አቋምን የመጫን አካሄድ እንደተዘጋበት በሚገባ ያውቃል፤ እነዚህ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ፣ የኢራን ሕዝብ ሕጋዊ መብቶች እስካልታወቁ እና አሜሪካ የገባችው ስምምነት እስካልተፈጸመ ድረስ፣ ወደ ቀድሞው የድርድር ሁኔታ ለመመለስም ሆነ የሆርሙዝን የባሕር መስመር እንደገና ለመክፈት ምንም ዓይነት ዕድል አይኖርም" ብለዋል።

    አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ቴህራን ላይ ጦርነት ካወጀች ጊዜ ጀምሮ የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል።

    ቴህራን፣ አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ እና የአሜሪካ ጦር ሠፈር በሚገኝባቸው አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ፈጽማለች።

    ዋሺንግተን እና ቴህራን ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    በኋላ ላይ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በሚኖር የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ሁለቱ አገራት መስማማት ባለመቻላቸው ስምምነቱ ፈርሷል።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ የሆኑት ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ “እየተዋጋን እንደራደራለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ይህም ማለት በወሳኝ ወቅት ጠላትን ወደ ኋላ እነዲያፈገፍግ ማድረግ እና ሙሉ የወታደራዊ አቅማችንን ተጠቅመን ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረግ ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

    “ይሁን እንጂ፣ በጦር ሜዳው ላይ ጉልህ ስኬት ካስመዘገብንና ጠላትም ከተዳከመ በኋላ፣ እነዚህን ውጤቶች ለማጠናከር ዲፕሎማሲን መጠቀም አለብን።”

    ኢራን በድርድር ላይ ያላት አቋም “ሙሉ በሙሉ ግልጽ፣ ምክንያታዊ እና ለድርድር የማይቀርብ ነው” ያሉት ጋሊባፍ አሜሪካ በስምምነቱ የገባችውን እስክትፈፅም ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

    የአፈ ጉባዔው ንግግር የተሰማው ለፓኪስታን እና ኳታር አደራዳሪዎች ከአሜሪካ ጋር ንግግር ለመጀመር ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ ከተነገራቸው ብኋላ ነው።

  3. በሞስኮ ክልል ላይ በተፈጸመ 'ከፍተኛ' የዩክሬን ድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ሩሲያ አስታወቀች

    ዩክሬን በሞስኮ ክልል በፈጸመችው በርካታ የድሮን ጥቃት ቢያነስ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና ስድስት መቁሰላቸውን አስተዳዳሪው አንድሬያ ቮሮቤይቭ ተናገሩ።

    የሞስኮ ከንቲባ ሰርጌይ ሶቢያኒን "ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ጥቃት" ለመፈጸም ወደ ዋና ከተማዋ ሲበሩ የነበሩ 450 ድሮኖች መመታታቸውንና መውደቃቸውን አስታውቀዋል። በዚህ ጥቃት የነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ በርካታ መኖሪያ ቤቶችም በእሳት ተቃጥለዋል።

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ፣ ኪየቭ በክልሉ የሚገኝ "ቁልፍ" የሩሲያ የነዳጅ ተቋምና የሎጂስቲክስ ማዕከል መምታቷን አረጋግጠው፤ እነዚህም "የጦርነት ማሽኑን የሚያንቀሳቅሱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዋጋ የሚያወጡ" ተቋማት መሆናቸው ተገልጿል።

    በሌላ በኩል የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ቅዳሜ ዕለት ሩሲያ በኪየቭ እና በሱሚ ክልሎች በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ሦስት ሕጻናትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።

    ሩሲያ እና ዩክሬን በቅርቡ የኃይል ማመንጫ እና የመጓጓዣ ተቋማትን እንዲሁም ዋና ዋና የሎጂስቲክስ ማዕከላትን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶቻቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

  4. ኡጋንዳ ከቱርክ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር አቋረጠች

    ኡጋንዳ ከቱርክ ጋር የገባችውን ዲፕሎማሲያዊ እሰጥ አገባ ተከትሎ ያላትን ወታደራዊ የመከላከያ ትብብር አቋረጠች።

    የኡጋንዳ መከላከያ ምክትል ቃል አቀባይ ትብብሩ ተቋርጦ የሚቆየው በስም ያልጠቀሷቸው አንዳንድ ጉዳዮች እስኪፈቱ ድረስ መሆኑን ተናግረዋል።

    ኡጋንዳ ከቱርክ ጋር ያላትን ወታደራዊ ግንኙነት ስለማቋረጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያወጣችው መግለጫ ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን ብቻ የያዘ ቢሆንም ከፍ ያለ ዲፕሎማሲያዊ አንድምታዎች አሉት።

    አርብ ዕለት፣ የጦር ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል ሙሁዚ ካይነሩጋባ በካምፓላ በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ውጭ የተቃውሞ ሰልፍ ላደረጉ እና እርሳቸው ለሚመሩት 'የዩጋንዳ ፓትሪዮት ሊግ' ምስጋና አቀርበዋል።

    ሠልፈኞቹ በኢንተርኔት አማካኝነት መንግሥትን የሚቃወም ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት የተከሰሱትንና በቱርክ የሚኖሩትን ኡጋንዳዊ ፍሬድ ሉምቡዬን ተላልፈው እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

    ግለሰቡ በኡጋንዳ ጠብ በማነሳሳት እና የሳይበር ወንጀሎች ይፈለጋሉ።

    የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ የሆኑት ጄኔራል ካይኔሩጋባ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቱርክ ባለሥልጣናትን በተደጋጋሚ ሲተቹ ታይተዋል።

  5. ሁቲዎች የሳዑዲ አረቢያን ዋና ከተማ በባሊስቲክ ሚሳይሎች ማጥቃታቸውን ተናገሩ

    በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ ተዋጊዎች በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ ላይ የድሮን እና የባሊስቲክ ሚሳይል ጥቃት መፈጸማቸውን ገለፁ።

    በተጨማሪም በአገሪቱ የቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ባሉ የኃይል ተቋማት ላይ መሰል ጥቃት መፈፀማቸውን ገልፀዋል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት ቅዳሜ ዕለት ወደ ሪያድ የተወነጨፈ አንድ ባሊስቲክ ሚሳይል ማክሸፋቸውን የተናገሩ ቢሆንም ሌሎች ጥቃቶች ወይም ጉዳቶች ስለመኖራቸው አላረጋገጡም።

    ባለሥልጣናቱ ይህን ከማለታቸው አስቀድሞ፣ ቅዳሜ ዕለት በሳዑዲ ዋና ከተማ አቅራቢያ ባለው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አካባቢ ካሉ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ጥቁር ጭስ ሲነሳ ታይቷል። ይህም በረራዎች ለአጭር ጊዜ እንዲስተጓጎሉ አድርጓል።

    ሁቲዎች በሐምሌ ወር በሳዑዲ አረቢያላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ካጠናከሩ በኋላ፣ በሪያድ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰምተዋል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አሜሪካውያን “ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ሊኖሩ ለሚችሉ የበረራ ስረዛዎች እና ሌሎች የጉዞ መስተጓጎሎች ዝግጁ እንዲሆኑ” አሳስቧል።

    “በኢራን የሚደገፉ ሁቲዎች ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የሲቪል አየር ማረፊያዎችንም ያካተተ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ወታደራዊ ግጭት በፍጥነት ሊባባስ ይችላል” ሲል ሚኒስቴሩ በመግለጫው ስጋቱን ጠቅሷል።

    በተጨማሪም አሜሪካውያን “ወደ ቀጣናው ወይም በቀጣናው ውስጥ የሚያደርጉትን ጉዞ ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል” ሲል በአጽንዖት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

    በሳዑዲ የሚመራው የጥምር ኃይል በቃልአቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ፣ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በቢሽ፣ ታይፍ፣ ፋራሳን እና ያንቡ ከተሞች ውስጥ ሲቪሎችን ለማነጣጠር የተደረጉ ሙከራዎችን” ማክሸፉን ገልጿል።

    የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ አል ሳሪያ ባወጡት መግለጫ፣ በሪያድ የሚገኙ “ስሱ ቦታዎችን” እንዲሁም በያኑብ ያለውን አራምኮ የነዳጅ ኩባንያ ለማጥቃት “በርካታ ቁጥር ያላቸው የባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳይሎች እንዲሁም ድሮኖችን” መጠቀማቸውን አስታውቀዋል።

    ጥቃቱን የፈፀሙት ሳዑዲ በሁቲ ቁጥጥር ስር በምትገኘው የሰነዓ ከተማ ላይ ላደረሰችው “የወንጀል ሙከራዎች” አፀፋ ለመስጠት እንደሆነም አክለው ገልፀዋል።

  6. አሜሪካ በኢራን ጦርነት እስካሁን ድረስ 43.6 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷ ተገለጸ

    የአሜሪካ ጦር በኢራን እያካሄደው ባለው ጦርነት እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ ብቻ 43.6 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱን በዚህ ሳምንት ለሕግ አውጪዎች ባቀረበው አዲስ ሪፖርት ላይ ይፋ አደረገ።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደውን ጦርነት በበላይነት የሚመራው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ይፋ ያደረገው ይህ አዲስ መረጃ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የወጣውን ወጪ ያሳየ የቅርብ ጊዜ ግምት ነው።

    የካቲት 21/2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በመሆን በቴህራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ቢሊዮኖችን እያስወጣ ይገኛል።

    ጦሩ እስከ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 38 ቢሊዮን ዶላር መውጣቱን የኮንግረሱ የበጀት ኮሚቴ ሪፖርት ያሳያል። ይኸው ሪፖርት በአንድ ወር ውስጥ ይህ በጀት በ3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጨምር አስታውቆ ነበር።

    የፈረንሳዩ የዜና ወኪል የተመለከተው ይህ በጀት የአሜሪካ ጦር አሁንም ውድ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን እንደሚጠቀም ያሳያል።

    በአንድ ወር ብቻ የጦር መሣሪያዎቹ ወጪ ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከፍ ያለ ሲሆን የማዕከላዊ ዕዙ እንዳለው የጦር መሣሪያዎቹ ወጪ መጀመርያ ከተገመተው 21.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ 28.1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።

    የኢራን ጦርነት ካስከተለው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ወጪ ባሻገር የዓለም የነዳጅ ዋጋን እና የአክሲዮን ገበያን ጭማሪ አስከትሏል።

    ጦርነቱ ያስከተለው ወጪ ይፋ የሆነው የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የ1.5 ትሪሊየን ዶላር ወታደራዊ በጀት ከጠየቀ በኋላ ነው።

    ዋይት ሐውስ በበኩሉ የኢራን ጦርነትን ለመደገፍ እና ሌሎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች የሚውል በማለት ኮንግረስ የ95 ቢሊዮን ዶላር ፓኬጅ እንዲያጸድቅ ጠይቋል።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት “1.5 ትሪሊየን ዶላር በጀት የጠየቅነው አገራችንን ጠንካራ አድርጎ ለማቆየት እንዲሁም እንደ ሳሮኒክ ያሉ ከፍተኛ ክፍያ የሚከፍሉ የአሜሪካ አምራቾችን በመደገፍ ለትውልድ የሚቆይ ሥራ ለመስራት ነው” ብለዋል።

  7. በሪያድ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ እሳት እና ጭስ መታየቱ ተዘገበ

    በሳዑዲ አረቢያ መዲና ሪያድ በሚገኘው ንጉሥ ካሊድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቁር ጭስ እና እሳት መታየቱን የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    የሳዑዲ መንግሥት ስለ ክስተቱ ማብራሪያ ቢጠየቀም ምላሽ እንዳልሰጠም ተዘግቧል።

    በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ በሚገኝ የሳዑዲ አራምኮ ንብረት የሆነ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ እሳት መነሳቱን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    ዘገባው እንደሚጠቁመው፤ ነዋሪዎች ፍንዳታ መስማታቸውን ገልጸዋል።

    ተሽከርካሪው የሳዑዲ አራምኮ መለያ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፤ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ሲረባረቡ የሚያሳዩ ምሥሎች ወጥተዋል።

    በሪያድ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአደጋ ጊዜ ደውሎች መሰማታቸውን የሳዑዲ የሲቪል መከላከያ ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል።

    በየመን የሁቲ አማጺያን እና በሳዑዲ መካከል የተፈጠረው ግጭት ከተባባሰ ወዲህ በመዲናዋ የማስጠንቀቂያ ደውሎች ሲሰሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    በረራዎችን የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 ድረ ገጽ እንዳለው በረራዎች ተራዝመዋል፤ እንዲሁም ተሰርዘዋል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት ስለ ክስተቱ መንስዔ ወይም ከሁቲዎች ጋር ከተነሳው ግጭት ጋር የሚገናኝ ስለመሆኑ አልገለጹም።

    የተነሳው እሳት በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ይሁን ወይም በአቅራቢያው እስካሁን ድረስ ግልጽ መረጃ አልወጣም።

  8. ደቡብ አፍሪካውያን በጆሃንስበርግ ተገድለው የተገኙትን ዘጠኝ ሴቶች ለመዘከር እና መፍትሔ ለመጠየቅ ተሰባሰቡ

    ደቡብ አፍሪካውያን በዚህ ሳምንት በጆሃንስበርግ አቅራቢያ ተገድለው የተገኙትን ዘጠኝ ሴቶች ለመዘከር እና መፍትሔ ለመጠየቅ ተሰባሰቡ።

    በርካቶች ሴቶች በየቀኑ የሚጋፈጡት እንደሆነ የሚገልጹት ጥቃት ቁጣ እና ስጋትን ፈጥሯል።

    ሮይተርስ እንደዘገበው ባለፉት ሁለት ወራት ፖሊስ በምሥራቃዊ ጆሃንስበርግ ኢኩርሁልኒ የዘጠኝ ሴቶችን አስክሬን ያገኘ ሲሆን ምርመራ እያካሄደ ነው።

    አብዛኞቹ ሟቾች በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ልብሶቻቸው የተቀዳደዱ ሲሆን ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተውባቸዋል።

    በጆሃንሰበርግ ከተገደሉት መካከል አንዷ የሆነችውን ኤሊዛቤት ሞስላክጎሞ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ዛሬ እየተካሄደ ነው።

    ኤሊዛቤት ለመሮጥ ከቤቷ ከወጣች በኋላ ነበር ከቀናት በኋላ አስክሬኗ የተገኘው።

    ሀዘንተኞች ሻማ በማብራት እና “በቃ! በሴቶች ላይ የሚፈፀም ግድያ ይቁም” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል።

    ጥቁር ለብሰው በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተገኙት መካከል ሊራቶ ሊንትሴላ የተባለች ሴት “እዚህ የተገኘነው ኤልዛቤትን ስላጣን ነው። ግን እኛም የትም ቦታ ደኅንነታችን የተጠበቀ አይደለም” ብላለች።

    ግድያዎቹ እአአ በ2025 ፆታን መሠርት ያደረጉ ጥቃቶች ብሔራዊ ቀውስ ሆኖ በታወጀባት ደቡብ አፍሪካ ቁጣን ቀስቅሷል።

    በርካታ ሴቶች ለጥቃቱ የተሰጠው ትኩረት እና የባለሥልጣናት ቃል ደኅንነት እንዲሰማን ማድረግ አልቻለም ብለዋል፥።

    ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ሐሙስ ዕለት ደቡብ አፍሪካ እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት እንድትለምድ እንማይፈቅዱ እና ድርጊቱን ፈፃሚዎች ለፍርድ እንደማያቀርቡ ቃል ገብተዋል።

    ነገር ግን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አገልግሎት በሙስና እና በበጀት እጥረት ተዳክሟል። በዚህም ምክንያት ከ10 ግድያዎች ውስጥ ምርመራ ተደርጎ ለፍርድ የሚቀርበው አንዱ ብቻ ነው።

    ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከሚፈጸምባቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን በአማካኝ በዓለም ላይ ከሚገደሉ ሴቶች መካከል በአገሪቱ የሚገደሉት አምስት እጥፍ እንደሚበልጥ የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት መረጃ ያሳያል።

  9. ከሁቲዎች ጋር የሚደረገው ውጊያ ከተባባሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሪያድ የማስጠንቀቂያ ደወሎች ተሰሙ

    በሳዑዲ አረቢያ መዲና ሪያድ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአደጋ ጊዜ ደወሎች መሰማታቸውን የሳዑዲ የሲቪል መከላከያ ድርጅት ገለጸ።

    በአገሪቱ እና በየመን ሁቲዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ከተባባሰ ወዲህ በመዲናዋ የማስጠንቀቂያ ደወሎች ሲሰሙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    የዜና ወኪሎችም በሪያድ ቢያንስ ሁለት ፍንዳታዎች መስማታቸውን ዘግበዋል።

    ማስጠንቀቂያው የተሰማው የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ በሰንዓ ተፈፀመ ያሉትን እና ሳዑዲ አረቢያን ተጠያቂ ያደረጉበትን “ የወንጀል ድርጊቶች” ማክሸፋቸውን አስታውቀው፣ ለድርጊቷ ምላሽ እንደሚሰጥ ከዛቱ በኋላ ነው።

    የሳዑዲ የሲቪል መከላከያ ድርጅት ቅዳሜ ጠዋት በአካባቢው ያለው ሁኔታ ወደ መደበኛ መመለሱን ገልጿል።

    ሕዝብ የሚበዛበትን አብዛኛውን የየመን ሰሜናዊ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው የሚገኙት ሁቲዎች በቀይ ባሕር የሳዑዲ መርከቦችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት ከፍተዋል።

    ሁቲዎች ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በፍጥነት እየገሰገሱ ሲሆን የየመንን የቀይ ባሕር ዳርቻዎችን በሙሉ ተቆጣጥረዋል።

    ይህንንም ተከትሎ ሰሞኑን የሳዑዲ አየር ኃይል በአካባቢው ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎች መፈፀሙን ገልጸዋል። ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 26 ጥቃቶችን ፈፅማለች ብለዋል ሁቲዎች።

    የአርብ ዕለቱን ጥቃት ጨምሮ ባለፈው ሳምንት ብቻ ሳዑዲ የፈፀመችው ጥቃት 300 መድረሱንም ታጣቂ ቡድኑ አስታውቋል። እነዚህ ጥቃቶች ዒላማ ያደረጉት በየመን ሁቲ የሚቆጣጠራቸውን ቦታዎች እንደሆነም ገልጿል።

    እአአ በ2014 በየመን የተቀሰቀሰው ጦርነት በ2022 በታጣቂ ቡድኑ እና በሳዑዲ መካከል በተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ብሎ ቢቆይም ሐምሌ ወር ላይ እንደገና አገርሽቷል።

  10. የኡበር ሹፌር ተሳፋሪዋን አውራ ጎዳና ላይ አውርዶ ለኅልፈት በመዳረጉ ኩባንያው 40 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወሰነ

    በካሊፎርኒያ፣ የኡበር ሹፌር የ23 ዓመት ሴትን አውራ ጎዳና ላይ ከመኪናው አውርዶ ለኅልፈት በመዳረጉ ኩባንያው 40 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወሰነ።

    አሽከርካሪው አውራ ጎዳና ላይ መኪናውን አቁሞ ተሳፋሪዋ ኤምሊ ኖርማንዲን-ፓርከር እንድትወርድ ማስገደዱ ተገልጿል።

    ከጓደኞቿ ጋር ኡበር ጠርታ ወደ ቤት እየሄደች የነበረችው ኤምሊ ከመኪናው ከወረደች በኋላ በሌላ ተሽከርካሪ ተገጭታ ሕይወቷ አልፏል።

    ቤተሰቦቿ እንደተናገሩት ኤምሊ አልኮል ጠጥታ ነበር። ጓደኛዋ መኪና ውስጥ ሳለች በመታመሟ ሲያስመልሳት እንደነበርም የፍርድ ቤት ሰነዶች ያሳያሉ።

    አሽከርካሪው በግሉ የሚሠራ ተቀጣሪ ስለሆነ ኡበር ኃላፊነት እንደማይወስድ በመግለጽ በፍርድ ቤት ተከራክሯል።

    የኤምሊ ቤተሰቦች በሰጡት መግለጫ “ኤምሊ የሚጠበቅባትን አድርጋለች። ኡበር ቤቷ በሰላም እንደሚያመጣት አምና ነበር። ነገር ግን ሕይወቷን አጥታለች” ብለዋል።

    ለአምስት ቀናት የኤምሊ ቤተሰቦች እና ኡበር ከተደራደሩ በኋላ ዳኛ ሪቻርድ ስቶን ኩባንያው በገንዘብ እንዲቀጣ ወስነዋል።

  11. ትራምፕ ሲኤንኤን እና ፖሊቲኮ ዋይት ሃውስ እንዳይገቡ እንደሚያግዱ አስታወቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሲኤንኤን፣ ኤምኤስ ናው እና ፖሊቲኮ ዋይት ሃውስ እንዳይገቡ እንደሚያግዱ አስታወቁ።

    ይህም ትራምፕ ከመገናኛ ብዙኃኖቹ ጋር ባላቸው የሻከረ ግንኙነት የሰነዘሩት የቅርብ ጊዜ ዛቻ ነው።

    ፕሬዚደንቱ አርብ ዕለት በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “ሁልጊዜ ፈጠራ ወይም ውሸት ይጽፋሉ፤ ይዘግባሉ” ሲሉ ከስሰዋል። ሆኖም ትራምፕ ለዚህ ክሳቸው ያቀረቡት ማሳያ የለም።

    ትራምፕ በኋላ ላይም እርምጃውን “በጣም ቀላል ገደብ” ያሉት ሲሆን እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም። የሚዲያዎቹ ሰራተኞች በአጠቃላይ ወደ ዋይት ሃውስ እንዳይገቡ ይከለክል እንደሆነም ግልጽ አይደለም።

    ሲኤንኤን ለእርምጃው ወዲያውኑ ምላሽ የሰጠ ሲሆን በአሜሪካ የፕሬስ ነፃነት ላይ የተፈፀመ “ሕገ ወጥ ጥቃት” ብሎታል።

    ፖለቲኮም መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው በዋይት ሃውስም ሆነ በቀጣይ ሥራዎቹ ሚዛናዊ ዘገባዎችን ማቅረብ እንደሚቀጥል ገልጿል።

    በቀድሞ ስሙ ኤምኤስኤንቢሲ እና የአሁኑ ኤምኤስ ናው ግን አስተያየት ለመስጠት አልፈቀደም።

    ትራምፕ እርምጃው ካስታወቁ በኋላ በኦቫል ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ ላይ የፖለቲኮ እና የሲኤንኤን ጋዜጠኞች ዋይት ሃውስ ነበሩ።

    በመግለጫቸው “መገናኛ ብዙኃን ስለአሜሪካው ፕሬዚደንት፣ የትራምፕ አስተዳደር ወይም ስለአሜሪካ ሲዘግቡ ያለማቋረጥ የፈጠራ ወሬ እና ውሸት መጻፍ አይችሉም። . . . ሌሎች ሚዲያዎችም ይከተላሉ” ብለዋል።

    ሌሎች ሚዲያዎችም ይከተላሉ ማለት ምን ማለታቸው እንደሆነ ከአንድ ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄም ከሐሰተኛ ዜና ጋር በተያያዘ በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመው፣ "ታውቃለችሁ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ ሐሰተኛ ነው፣ ዋሽንግተን ፖስት ሐሰተኛ ዜና ነው የሚያሰራጨው” ሲሉ መልሰዋል።

    የፕሬዚደንቱን እርምጃ ተከትሎ የዋይት ሃውስ ዘጋቢዎች ማኅበር ፕሬዚደንት እና የፎክስ ኒውስ ዘጋቢው ጃኪ ሄንሪች ሥራቸውን በመስራታቸው ብቻ ተለይተው የተጠቀሱትን ባልደረቦቻቸውን ለመከላከል ከጎናቸው እንደሚቆሙ ተናግረዋል።

    የትራምፕ እርምጃም ሕጋዊ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ይችላሉ።

    ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተደጋጋሚ መገናኛ ብዙኃንን በሐሰተኛ መረጃ የሚከሱ ሲሆን እንዲዘጉ ያደረጓቸውም አሉ።

  12. ትራምፕ በሩሲያ እና በኢራን ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ረቂቅ ላይ ፊርማቸውን አኖሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ተግባራዊ እንዲሆን ፊርማቸውን አኖሩ።

    ማዕቀቡ የሩሲያን ምጣኔ ሃብት የሚያዳክም ይሆናል።

    ማዕቀቡ እንዲጣል የቀረበው ረቂቅ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ነው ትራምፕ ፊርማቸውን ያኖሩት።

    ከሩሲያ ጋር ትስስር ያላት ኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን ዘላቂ ማድረግም የረቂቁ አካል ነው።

    በዚህም እንደ ቻይና እና ሕንድ ያሉ ከሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ የሚገዙ አገራት ላይ ትራምፕ 100% ታሪፍ መጣል ይችላሉ።

    ማዕቀቡ የኢራን የኢነርጂ እና የጦር መሣሪያ ምርት ዘርፍንም ይመለከታል።

    ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት የሕዝብ እንደራሴ ሊንዚ ግራሀም ስም የተሰየመው ረቂቅ 48 ገጾች አሉት።

    የሩሲያን የተፈጥሮ ጋዝ ከ15% በታች በሆነ መጠን የሚያስገቡ እና ሩሲያ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ እየሞከሩ ያሉ አገራት በታሪፉ አይካተቱም።

    ማዕቀቡ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እና ሌሎች የሞስኮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን፣ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማትን ያካትታል።

    ሩሲያ የተጣለባትን የነዳጅ ማዕቀብ በማለፍ ነዳጅ የምታዘዋውርባቸው መርከቦች (ሻዶ ፍሊት) ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦችም ይገኙበታል።

  13. ሩሲያ በአውሮፓ ላይ የምትፈፅመው ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱን የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ተናገሩ

    የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሩሲያ በአውሮፓ እና በፈረንሳይ ላይ የምትሰነዝረው ወታደራዊ እና የሳይበር ጥቃትን ጨምሮ ወታደራዊ ያልሆኑ “ቅይጥ” ጥቃቶች እየተባባሱ መጥተዋል ሲሉ አስጠነቀቁ።

    ማክሮን በኤሊስ ቤተ መንግሥት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በዚህ ስጋት ምክንያት ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን እና የመከላከያ ኢንደስትሪ ቦታዎችን ለመጠበቅ እቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

    ፈረንሳይ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሩሲያ “ቅይጥ” ጥቃቶች ኢላማ ሆና እንደነበር የተናገሩት ፕሬዚደንቱ፣ ለዚህ "ምላሽ ሳይሰጥ እንደማይቀር” ገልጸዋል።

    በርካታ የአውሮፓ መሪዎችም ሩሲያ አገራቱ ዩክሬንን ለመደገፍ ምን ያህል ቁርጠኛ መሆናቸውን ለመፈተሽ ጥቃት ለመፈፀም እየተዘጋጀች ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

    የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ማስጠንቀቂያውን የሰጡት የመካከለኛው ምሥራቅ እና የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ተፅዕኖ ላይ ለመወያየት ከፓርቲ መሪዎች ጋር ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

    ማክሮን ባለፈው ወር በጀርመን ሌፕዚግ አየር ማረፊያ ላይ የተፈፀመውን የድሮን ጥቃት እንዲሁም የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ሩሲያ በፖላንድ እና በሌሎች የኔቶ አባል አገራት ላይ የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃቶችን ለመፈፀም እያቀደች መሆኑን በመግለጽ የሰጡትን አስተያየት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

    ባለፈው እሁድ ዕለትም የሩሲያ ድሮን በዩክሬን እና ፖላንድ ድንበር አቅራቢያ አንድ የመንገደኞች ባቡርን መትቷል። ጥቃቱ የተፈፀመው የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እና ከፍተኛ የአውሮፓ የደኅንነት ባለሥልጣናት በተመሳሳይ መስመር ካለፉ ብዙም ሳይቆይ ነበር።

    የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በተደጋጋሚ ሩሲያ አውሮፓን የማጥቃት እቅድ እንደሌላት ተናግረዋል።

    ሆኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ የአውሮፓ አገራት ወደ ዩክሬን ወታደር መላክ በሩሲያ “እንደ ጦርነት እወጃ” እንደሚቆጠር በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

    “ አውሮፓ ሩሲያን ካጠቃች፣ ጦርነቱ የተለየ ነው የሚሆነው። በጣም አጭር ነው የሚሆነው” ብለዋል።

  14. የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት አገራቸው በኢራን ጦርነት ውስጥ ጣልቃ እንደማትገባ ተናገሩ

    የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚደንት ሊ ጃይ ሚዩንግ አገራቸው ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ጣልቃ እንደማትገባ እና የጦር ኃይላቸውንም እንደማይልኩ ተናገሩ።

    ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ከቅርብ ወራት ወዲህ ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦችን ከጥቃት የመጠበቅ ዘመቻን ልትቀላቀል ትችላለች የሚሉ ወሬዎች ከተናፈሱ በኋላ ነው።

    ከሁለት ሳምንት በፊትም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ማንኛውም ዓይነት ተሳትፎ ወይም ወታደራዊ ስምሪት “ለእብሪተኞች ቀጥተኛ ድጋፍ እንደማድረግ እንደሚቆጠር” እና “ከፍተኛ መዘዝ እንደሚያስከትል” በመግለጽ ደቡብ ኮሪያን አስጠንቅቀው ነበር።

    ፕሬዚደንት ሚዩንግ ዛሬ አርብ መስከረም 8፣ 2019 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አገራቸው በዚህ ላይ እንደማትሳተፍ እና ከኢራን ጋር በሚደረገው ጦርነት ጣልቃ እንደማትገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

    ጨምረውም በውጪ ጦርነት ወታደሮቻቸው እንዲሳተፉ ለመላክ በፍፁም እንደማይስማሙ አረጋግጠዋል።

    በሌላ ንግግራቸውም ፕሬዚደንቱ “ትራምፕ ንግግር እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው፣ እናም ወደ ንግግር እንዲመጡ እኔም እጠይቃቸዋለሁ” ብለዋል።

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር ደቡብ ኮሪያን እንደ አንድ የእስያ አጋር ጠቅሰው፣ በጦርነቱ አገራት እያደረጉላቸው ያለው እርዳታ “በጣም ትንሽ” እንደሆነ ተናግረዋል።

    አሜሪካ ከአገሪቱ ጋር የምታደርገውን ዓመታዊ ወታደራዊ ልምምድ የቀነሰች ሲሆን ትራምፕ ይህንን ደቡብ ኮሪያ በኢራን ጉዳይ "ትንሽም ድጋፍ ለማድረግ" ፈቃደኛ ካለመሆኗ ጋር በግልጽ አያይዘውታል።

    ከዚህም በተጨማሪ ወታደራዊ ልምምዶቹ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህ ልምምዳቸው ከሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ባላቸው “በጣም መልካም ግንኙነት” ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።

    የጋራ ወታደራዊ ልምምዱ መቀነስ እና ትራምፕ ከፒዮንግያንግ ጋር ንግግር ለመቀጠል እያደረጉት ያለው ጥረት ሴዑልን ከሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራም ድርድር ውጭ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

  15. በፓኪስታን በመስጊድ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎች ሞቱ

    በፓኪስታን ቦምብ የተጠመደበት ተሽከርካሪ ከመስጊድ ጋር ተጋጭቶ አምስት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ ቢያንስ 16 ሰዎች መሞታቸውን አንድ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን አስታወቁ።

    በካይበር ፓክቱንክዋ ግዛት ኮሃት ከተማ የፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ በሚገኘው መስጊድ በጥቃት ፈፃሚዎቹ እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለው የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉም ተገልጿል።

    ከጥቃት አድራሾቹ አንደኛው መገደሉ የተገለጸ ሲሆን የፖሊስ ባለሥልጣኑ የነፍስ አድን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

    ጥቃቱን ተከትሎ የአገሪቷ ፕሬዚደንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ በሰጡት መግለጫ፣ በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች በፍጥነት እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሃማድ ሸህባዝ ሻሪፍም ጥቃቱን አውግዘዋል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የካይበር ፓክቱንክዋ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ኢንስፔክተር ጀነራል ኡልፊካር ሃሚድ ጥቃቱ "አጥፍቶ መጥፋት" እንደሆነ ገልጸዋል።

    ሆኖም ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።

    ከቅርብ በራት ወዲህ ጦሩን እና ፖሊስን ዒላማ ያደረጉ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በአገሪቷ ድንበሮች አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

    ኢስላማባድ ታጣቂዎች ለመሰልጠን እና በፓኪስታን ላይ ጥቃት ለመፈፀም አፍጋኒስታን እንደ ምቹ መደበቂያ ይጠቀማሉ ስትል ከስሳለች።

    የአፍጋኒስታን የታሊባን መንግሥት ግን ክሱን ያጣጣለ ሲሆን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የፓኪስታን የውስጥ ችግር ነው ብሏል።

  16. የኒጀር ወታደራዊ ባለሥልጣናት የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ የአምስት ሰዎችን ዜግነት ነጠቁ

    የኒጀር ወታደራዊ ባለሥልጣናት የአገሪቷን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከቀድሞው አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸውን የአምስት ሰዎችን ዜግነት ነጠቁ።

    በወታደራዊ መሪው ጄነራል አብዱራህማን ቲቺያኒ የተፈረመው ትዕዛዝ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡሆሞውዶ ማህመዱን እና ሌሎች ግለሰቦችን በስም ጠቅሷል።

    በመንግሥት የሚተዳደረው 'ኒጀሪያን ዲ ፕረስ' እንደዘገበው አምስቱ ግለሰቦች የሕግ ሥርዓትን የሚያናጋ ሐሰተኛ መረጃን በማሠራጨት፣ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር፣ በስም ማጥፋት፣ የጦሩን እና የአገሪቷን ክብር የሚነኩ ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም ብሔራዊ ጦሩን እና ማኅበራዊ ግንኙነቱን በማጣጣል ተከስሰዋል።

    እነዚህ ክሶች የቀረቡባቸው አብዛኞቹ ግለሰቦች ሐምሌ 2023 ሥልጣን የተቆጣጠሩትን ወታዳራዊ ባለሥልጣናት ከሚቃወመው የቀድሞው አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

    ዜግነታቸው ከተነጠቁት አንዱ የሆኑት ኦሆሞዶ ማህማዶ በመፈንቅለ መንግሥት በተገረሰሱት ፕሬዝዳንት ባዞም የሥልጣን ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

    የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አምስቱ ግለሰቦች ከኒጀር ውጭ እንደሚኖሩ የሚታመን ሲሆን፣ የት እንዳሉ ግን ትዕዛዙ የተላለፈበት ደብዳቤ አልጠቀሰም።

    ቢቢሲ የተወሰኑትን ግለሰቦች ለማነገጋር ጥረት ቢያደርግም በተወሰደው እርምጃ ላይ አስተያየት አልሰጡም።

    ወታደራዊ ባለሥልጣናቱ አሁን ላይ የወሰዱት እርምጃ በ2024 ወታደራዊው አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ ዜግነታቸውን የተነጠቁ ኒጀራዊያንን ቁጥር 25 አድርሶታል።

    ቀደም ብሎ በተወሰዱት እርምጃዎች የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶች እና ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ባዙም አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ዒላማ ተደርገዋል።

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች እርምጃው አገር አልባ የመሆንን አደጋ የሚያባብስ እንደሆነ ገልጾ፣ ከ2024 መጨረሻ አንስቶ ቢያንስ 18 በውጭ የሚኖሩ ተቃዋሚዎች በጊዜያዊነት ዜግነታቸውን መነጠቃቸውን ጠቅሷል።

    ወታደራዊ አስተዳደሩ ግን እርምጃው ብሔራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ እና ሕግ ለማስከበር የተወሰደ ነው በማለት ራሱን ተከላክሏል።

    ሆኖም የመብት ተሟጋች ቡድኖች ወታደራዊ አስተዳደሩ ትችት በሚሰነዝሩበት ላይ እየወሰደ ያለውን እና እየጨመረ የመጣውን የዜግነት ነጠቃ እርምጃ በጥብቅ ተችተዋል።

  17. በናይጄሪያ እስር ቤት ውስጥ በሕገ ወጥ ማዕድን ማውጣት ተጠርጥረው የታሰሩ በርካታ ሰዎች ሞቱ

    በሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ በሕገ ወጥ ማዕድን ማውጣት ተጠርጥረው የታሰሩ 37 ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ መሞታቸውን የአካባቢ ባለሥልጣናት ገለጹ።

    የእስረኞቹ ሞት መንስኤ ምን እንደሆነ ለማጣራት ፖሊስ ምርመራ የጀመረ ሲሆን፣ የናይጄሪያ የደኅንነት እና የሲቪል መከላከያ ጓድ ሞቶቹ የተከሰቱት በበሽታ ወረርሽኝ ሳቢያ እንደሆነ ገልጿል።

    ይሁን እንጂ፣ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ የደረሰ የደኅንነት መረጃ፣ እስረኞቹ የሞቱት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በነበረው ከፍተኛ መጨናነቅ እና የአየር ዝውውር ማነስ ምክንያት መሆኑን ያመለክታል።

    ማረሚያ ቤቱ የሚገኘው በናይጄሪያ ኒጀር ግዛት ውስጥ ነው።

    የግዛቱ አስተዳዳሪ ሞሐመድ ኡማሩ ባጎ ሐሙስ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በእረኞቹ ላይ የደረሰውን ሞት “አሳዛኝና አስከፊ” ሲሉ ገልፀዋል።

    ከክስተቱ ጋር በተያያዘ አንድ የናይጄሪያ የደኅንነት እና የሲቪል መከላከያ ጓድ አዛዥ ታስሯል ሲሉም ባጎ አክለዋል።

    በተጨማሪም የሦስት ቀናት የሐዘን ጊዜ አውጀው፣ ለጥር ወር የታቀደው የምርጫ ዘመቻ እንዲዘገይ አድርገዋል።

    ባለሥልጣናት፣ በማዕድን ሀብት በበለጸገችው የኒጀር ግዛት በምትገኘው ቦርጉ አካባቢ በሕገ ወጥ የማዕድን ማውጣት ተግባር የተጠረጠሩ ወጣቶችን ማክሰኞ እለት ነበር በቁጥጥር ስር ያዋሉት። አካባቢው በአነስተኛ መጠን የወርቅ ማዕድን ማውጣት በስፋት የሚካሄድበት ቦታ ነው።

    የናይጄሪያ የደኅንነት እና የሲቪል መከላከያ ጓድ በሚያስተዳድረው እስር ቤት ውስጥ ከታሰሩት ተጠርጣሪዎች መካከል 37 ሰዎች ሞተው የተገኙት ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

  18. በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን መንግሥትን በመደገፍ አደባባይ ወጡ

    ላለፉት ሁለት ወራት ከአሜሪካ ጋር ጦርነት ውስጥ የቆየው የኢራን መንግሥት ባዘጋጀው ሠልፍ ላይ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞች መታደማቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሠልፈኞቹ አስፈላጊ ከሆነ ታጥቀው ከመንግሥት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    የኢራን መንግሥት ሕዝቡን ለማስተባበር እና ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጥረት እያደረገ ነው ተብሏል።

    ሠልፉ የተካሄደው የአሜሪካ የባህር ኃይል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ካገደ እንዲሁም በመንግሥት ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለመጨመር በሚል አሜሪካ አዳዲስ ማዕቀቦች ከጣለች በኋላ ነው።

    “ሕይወታቸውን ለኢራን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ” በሚል በጎ ፈቃደኞች ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰዱ ሲሆን እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደሠለጠኑ በይፋ አይታወቅም።

    በቴህራን የተካሄደው ሠልፍ ላይ የታደሙ ሰዎች ወታደራዊ አልባሳትን ለብሰው፣ ባንዲራ ይዘው መፈክር ሲያሰሙ ታይተዋል።

    ለቀናት የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ሰልፉን ለመታደም የአገሪቱ ዜጎች አደባባይ እንዲወጡ ሲቀሰቅሱ ነበር።

    መገናኛ ብዙኃኑ በቅርቡ በጎ ፈቃደኞች ከመሳሪያ ጋር ስልጠና እንደሚሰጣቸው የዘገቡ ሲሆን በጎ ፈቃደኞቹ የአብዮታዊ ዘቡ አጋር እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

    የቴህራን ዘብ አዛዥ የሆኑት ጄነራል ሃሳን ሃሳንዛዴህ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን 600,000 ሰዎች በበጎ ፈቃድ ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

    አንድ ሚሊዮን ሰዎች በሥልጠናው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጨምረው ተናግረዋል።

    አርብ ማለዳ መገናኛ ብዙኃኑ 300,000 ያህል ሰዎች አደባባይ መውጣታቸውን ዘግበዋል።

    አዲሱ የባሲጅ አዛዥ ሆሴን ታኤብ፣ በጎ ፈቃደኞቹ “ለተሟላ መከላከያ” ዝግጁ እንደሚደረጉ ገልፀው በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ሠልፍ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

    አዲሶቹ ሠልጣኞች ለኢራን ጠላቶች “ቅዠት” እንደሚሆኑባቸው ታኢብ ተናግረዋል።

    በቴህራን የተደረገው ሕዝባዊ ሠልፍ ላይ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዙሽኪያን፣ ወታደራዊ አዛዦች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

    አንዳንድ ሠልፈኞች የአሜሪካ እና እስራኤልን ባንዲራዎችን ሲረጋግጡ ታይተዋል። ሌሎች ደግሞ “ሞት ለአሜሪካ” እንዲሁም "ሞት ለእስራኤል" የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

    ከትንሽ ልጇ እና ከባለቤቷ ጋር በሰልፉ ላይ የተገኘችው የ24 ዓመቷ ማርዚህ አፋጊ “እዚህ የተገኘሁት ትራምፕ፣ በእኛ በኢራናውያንና በአገራችን ላይ ለሚሰነዝሩት ማስፈራሪያ ምንም ዓይነት ፍርሃት እንደሌለን ልነግራቸው ነው” ብላለች። “በታሪክ ውስጥ ማንም ሰው ኢራንን ወርሮ እዚህ መቆየት አልቻለም።”

    በሠልፉ ላይ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ለእይታ ቀርበዋል።

  19. ጂቡቲ በሁቲ ታጣቂዎች ላይ ለሚካሄድ ወታደራዊ ዘመቻ ግዛቷን እንደማትፈቅድ አስታወቀች

    የጂቡቲ የገንዘብ ሚኒስትር ኢሊያስ ሙሳ ዳዋሌ አገራቸው በሁቲ ታጣቂዎች ላይ ለሚካሄድ ማንኛውም ወታደራዊ ዘመቻ ግዛቷን እንደማትፈቅድ አስታወቁ።

    ሚኒስትሩ ከቢቢሲ ሶማልኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከዚህ ቀደም አሜሪካ በአገሪቱ ያላትን ጦር ሠፈር በሁቲ ላይ ዘመቻ ለማካሄድ እንድትጠቀም አለመፍቀዷን አስታውሰው አhuንም የተለወጠ አቋም አለመኖሩን አስረድተዋል።

    ጂቡቲ በየትኛውም ወታደራዊ ዘመቻ ውስጥ መሳተፍ እንደማትፈልግ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በየመን በተለያዩ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል።

    ጂቡቲ ለቀጣናው ኃያላን ጦር ማሰባሰቢያ ማዕከል አትሆንም ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ ዳዋሌ፣ አገሪቱ የራሷ ከፍተኛ ኃላፊነቶችና ጫናዎች እንዳሉባት ገልጸዋል።

    ጂቡቲ በኤደን ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ የምትገኝ ስትሆን ለየመን እና ባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች።

    ሚኒስትሩ የባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥን ክፍት አድርጎ መቆየት ለጂቡቱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አስረድተዋል።

    ጂቢቱ በየመን እየተዋጉ የሚገኙ አካላት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጠይቀው አገራቸው ባሕር ተሻግሮን የሚመጣ አለመረጋጋት እንደማትፈልግ ተናግረዋል።

    በየመን እየተባባሰ የመጣው ግጭት በጂቡቲ ላይ የሰብዓዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ በርካቶች ተፈናቅለው ወደ አገራቸው መግባታቸውን አስረድተዋል።

    በግጭቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት ወደ ጂቡቲ መድረሳቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።

    ከየመን የሚነሱ አነስተኛ ጀልባዎች ጂቡቲ ለመድረስ ከአንድ ሰዓት ያነሰ ጊዜ ብቻ የሚፈጅባቸው ሲሆን ይህም በርካቶች ወደ አገሪቱ እንዲሸሹ አድርጓቸዋል ሲሉ አብራርተዋል።

    የጂቡቲ መንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት የአገሪቱን ሕዝቦች ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ ነው ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ በየመን ውስጥ የተከሰተው ማንኛውም አለመረጋጋት በአገራቸው ውስጥ ለሚኖረው ተጽዕኖ መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

    የዓለም አቀፍ መንግሥታት ለተፈናቃዮቸ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የጠየቁት ሚኒስትሩ ግጭትን ሸሽተው ጂቡቲ የገቡት ዜጎች "ያለ በቂ ድጋፍ መተው የለባቸውም" ብለዋል።

    ዳዋሌ የጂቡቲ ጎረቤቶቿች በተለይ ደግሞ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አገራት ለየመን ግጭት መፍትሄ ለመስጠት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

    ሚኒስትሩ ጂቡቲ የባብ ኤል ማንዳብ የባሕር መስመር ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ድጋፏን እንደምትሰጥ የገለጹ ሲሆን፣ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ወገኖችም መረጋጋትን በመላበስ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።

  20. በለንደን ለሰባት ዓመታት ጠፍታ የነበረች ሴት አስከሬን በሰደድ እሳት በተቃጠለ ቁጥቋጦ ውስጥ ተገኘ

    በደቡብ ምዕራብ ለንደን የተከሰተን ሰደድ እሳት ተከትሎ ለሰባት ዓመት ያህል ስትፈለግ የነበረች ሴት አስከሬን ተገኘ።

    የሦስት ልጆች እናት እና የ44 ዓመት ጎልማሳ የሆነቸው ጆአን ሼን የጠፋችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ኅዳር ወር ላይ ነው።

    የሜትሮፖሊታን ፖሊስ አባላት እአአ ነሐሴ 12 በእሳት በወደመው ቁጥቋጦ ውስጥ የሰው አጽም መገኘቱን ተከትሎ ወደ ስፍራው ተጠርተዋል።

    ፖሊስ ግለሰቧን በመግደል የጠረጠረውን የ56 ዓመት ጎልማሳ በቁጥጥር ስር አውሏል።

    በለንደን የሚገኙ መርማሪዎች የተገኘው አጽም የሼን መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ምርመራውን ለአካባቢው ፖሊስ አሳልፈው ሰጥተዋል።

    ሼን በጠፋችበት ወቅት ፖሊስ ሰፊ እና ውስብስብ ምርመራ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን ከ4,000 በላይ ፍንጮችን በመከተል ከ300 በላይ ቃሎችን ተቀብያለሁ ብሏል።

    ከዚህም በተጨማሪ ከ10 በላይ አድራሻዎች እና በርካታ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝርዝር ፍተሻ አካሂዷል።

    ፖሊስ የሼን አስከሬን መገኘቱን ተከትሎ አሁንም ስለ አጠፋፏ መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው እንዲተባበረው ጠይቋል።

    ነሐሴ 5 ከሁለት ሄክታር በላይ ያወደመ እሳት በተቀሰቀሰበት ወቅት የለንደን የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተጠርተው እሳቱን ያጠፉ ሲሆን ከሳምንት በኋላ አጽሙ ተገኝቷል።

    አጽሙ ላይ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ሟች እድሜዋ ከ25 እስከ 45 መካከል የሆነ ሴት እንደሆነች ይፋ ተደርጓል።

    የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ቃል አቀባይ አጽሙ የተገኘው በአካባቢው ነዋሪ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

    ምርመራውን ለሚተባበር ማንኛውም ግለሰብ 20,000 ፓውንድ ሽልማት ማዘጋጀቱንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

    የሼን ቤተሰቦች መጥፋቷን ለፖሊስ ያስመዘገቡት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 የካቲት ወር ነው።

    በ2020 በርካታ ሰዎች በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ነበር።

    ፖሊስ ግለሰቧ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ፣ መኪና ወይንም የባንክ አካውንት እንደሌላት አስታውቆ ነበር።