ኢራን ምን ያህል የዩራኒየም ክምችት አላት?
አሁኑ ባለው ድርድር ውስጥ ዋነኛው መነጋገሪያ የኢራን የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ምን መሆን አለበት የሚለው ነው።
ጦርነቱ ሲጀመር ኢራን 440 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት እና ይህም 60 በመቶ የበለጸገ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር።
ይህም ጦር መሣሪያ ለማምረት ወደሚያስችለው 90 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም በአንፃራዊነት በፍጥነት ሊያድግ ይችላል።
ኢራን በተጨማሪም 20 በመቶ ድረስ የበለጸገ 1,000 ኪሎ ግራም፣ እንዲሁም 3.6 በመቶ ገደማ የበለጸገ 8,500 ኪሎ ግራም ዩራኒየም አላት።
ይህም በተለምዶ ለሰላማዊ አገልግሎት ማለትም ለኃይል ማመንጨት ወይም ለሕክምና ምርምር ይውላል።
ወደ ኒውክሌር ጦር መሣሪያነት ሊቀየር የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም በአብዛኛው በኢስፋሃን እንደተከማቸ ይታመናል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ዒላማ ከተደረጉት የኢራን ሦስት የመሬት ውስጥ የኒውክሌር ጣቢያዎች አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ከበለፀገው ዩራኒየም ምን ያህል በሌሎች ቦታዎች እንደተከማቸ ግልጽ አይደለም።
ምንጮች እንደሚሉት ቴህራን ለ20 ዓመት ኒውክሌር እንዳታበለጽግ የተቀመጠውን እገዳ ውድቅ አድርጋለች። በምትኩ ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት ያቀረበችውን የአምስት ዓመት ገደብ ለድርድር አቅርባለች።
በተጨማሪም 440 ኪሎ ግራም የበለፀገውን የዩራኒየም ክምችት እንድታስረክብ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።
ይህም ቀደም ሲል 60 በመቶ የበለፀገውን ዩራኒየሟን ለማዳከም በሚለው አቀወማ ጸንታለች።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮስ ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር ለኤፒ እንደተናገሩት ይህ መጠን የበለጠ ቢበለጽግ 10 የኒውክሌር ቦምቦች ለማምረት በቂ ይሆናል።