ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ሆርሙዝ እንዲከፈት እና ለሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ

ኢራን እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ መርከቦች እንዲያልፉ የሚያስችል የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ። ሁለቱ አገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ማክሰኞ ሌሊት ድረስ ማትከፍት ከሆነ “ዛሬ ማታ ሙሉ ሥልጣኔ ይወድማል” የሚል ዛቻ ካሰሙ ከሰዓታት በኋላ ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኪባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የእስራኤል ድብደባን እንዲያስቆም ጠየቁ

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ከፍተኛ የአየር ድብደባ ከተፈጸመ በኋላ "የሊባኖስ ወዳጆች በሙሉ" የእስራኤልን ወታደራዊ እርምጃ "በሚችሉት መንገድ ሁሉ" እንዲያስቆሙ ተማጸኑ።

    ናዋፍ ሳላም በኤክስ ገጻቸው ላይ "እስራኤል በሊባኖስ በተለይም በዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ በሕዝብ በተጨናነቁ የመኖሪያ ሰፈሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች" ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ያቀረቡት የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት በሄዝቦላህ ላይ ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለየ በመላው ሊባኖስ ዛሬ “መጠነ ሰፊ ድብደባ” መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው።

    ሳላም እንደሚሉት የአይዲኤፍ ጥቃቶች ለዓለም አቀፍ ሕግ "ፍፁም ቸልተኝነት" አሳይተዋል።

    አክለውም "እናም ሁሉም የሊባኖስ ወዳጆች እነዚህን ጥቃቶች በሁሉም መንገዶች ለማስቆም እንዲረዱን ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

    ሊባኖን 24 የተባለ የአረብኛ ዜና ወኪል በበኩሉ በኤክስ ገጹ ላይ በሊባኖስ የሚገኙ ሆስፒታሎች በተጎጂዎች መጨናነቃቸውን አጋርቷል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር በበኩሉ ዜጎች አውራ መንገዶችን ለአምቡላንሶች እንዲለቅቁ ጠይቋል።

    የሄዝቦላህ ደጋፊ የሆነው አል ማናር ቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ቤይሩት በፈጸመችው ጥቃት በርካቶች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን በቴሌግራም ገጹ ላይ ጽፏል።

    ኤልቢሲአይ የተባለ የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን በኤክስ ገጹ ላይ የአገሪቱን ጤና ሚኒስቴር ጠቅሶ በእስራኤል ጥቃት መቶዎች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን አጋርቷል።

    በመንግሥት የሚመራው የአገሪቱ የዜና ወኪል በበኩሉ በደቡባዊ ሊባኖስ አድሉን ከተማ በአንድ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሴቶች መገደላቸውን ዘግቧል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሲደርሱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ይህ “ሊባኖስን አያካትትም” ብለዋል።

  2. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን ከአሁን በኋላ ስጋት አትሆንም አሉ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ኢራን ላለፉት 47 ዓመታት ስጋት ሆና ቆይታ የነበረ ቢሆንም “ከአሁን በኋላ ግን አትሆንም” አሉ።

    ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

    ፒት ሄግሴት ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ከፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን ጋር በመሆን ነው።

    ፒት ሄግሴት "ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንን ቅጽበት ፈጥረዋል፤ ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ለምናለች፤ ይህንንም ሁላችንም እናውቀዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

    ሄግሰት ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ “ታሪካዊ እና እጅግ አስደናቂ ነበር” ያሉ ሲሆን የአሜሪካ ጦር “የኢራንን ጦር አውድሟል” ብለዋል።

    ሄግሴት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም የተደረሰበትን ዕለት “ለዓለም ሰላም ትልቅ ቀን” ሲሉ አሞካሽተዋል።

    አክለውም “በዓለም ግንባር ቀደም አሸባሪነትን የሚደግፍ መንግሥት ራሱን፣ ሕዝቡን ወይም ግዛቱን መከላከል ሙሉ በሙሉ አቅሙ የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሄግሴት ዩኤስ የኢራንን ባሕር ኃይል እና አየር ኃይል ጠራርጎ ለማጥፋት የያዘችውን ወታደራዊ ዓላማ አሳክታለች - አሜሪካ "ሰማያቸውን” ትቆጣጠራለች ብለዋል።

    ኢራን የተኩስ አቁሙን የተቀበለችው “በከፍተኛ ጫና” መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው ቴህራን የዋሺንግተንን ቅድመ ሁኔታዎች ባለትቀበል ኖሮ “ቀጥሎ ዒላማ የሚሆኑት ድልድዮቿ፣ የኃይል ማመንጫዎቿ፣ የነዳጅ እና ኢነርጂ መሠረተ ልማቶቿ ነበሩ” ሲሉ የፕሬዚዳንት ዛቻ ጠቅሰዋል።

    ኢራን መልሶ ለመገንባት አስርታት ዓመታትን ይወስድባት ነበር በማለት የግዛቲቱ መሪዎች ይህንን በመገንዘባቸው ከስምምነት ላይ መድረስን መርጠዋል ብለዋል።

    “ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራንን ምጣኔ ኃብት በደቂቃዎች ውስጥ ማሽመድመድ አቅም ነበራቸው ነገር ግን ርህራሄን መርጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ሚኒስትሩ የተኩስ አቁሙ “ለእውነተኛ ሰላም እና ለእውነተኛ ስምምነትን” ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው መስሪያቤታቸው “ለአሁኑ” የበኩሉን አድርጓል ፣ ግን ኢራን እያንዳንዱን ስምምነት ማክበሯን ለማረጋገጥ ዝግጁ ይሆናል” ብለዋል ።

    ሄግሴት እስራኤልን “ደፋር፣ ፈቃደኛ እና አቅም ያላትአጋር” በማለት ጠርተዋታል። የተቀረው ዓለም እና ሌሎች "የአሜሪካ አጋሮች ነን የሚሉ" አንዳንድ ማስታወሻዎችን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

    የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን በበኩላቸው የአሜሪካ ጦር “ከታዘዘ ወይም ጥቃት ዘመቻውን እንዲቀጥል ጥሪ ከቀረበለት ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃል ብለዋል።

    “የአሜሪካ ወታደሮች ባለፉት 38 ቀናት እንዳሳየነው ፍጥነት እና ቆራጥነት የጥቃት ዘመቻውን እንድንቀጥል ከታዘዝን ወይም ከተጠራን ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን እና ያ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን።”

  3. መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መንቀሳቀስ መጀመራቸው ተሰማ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፍ የሕንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፍ የሕንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የባሕር ላይ ትራንስፖርትን የሚከታተለው ማሪንትራፊክ የተሰኘ ድርጅት በኢራን ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ በነበረው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “የመርከቦች እንቅስቃሴ ምልክት” መታየቱን አስታወቀ።

    በወሽመጡ አንድ በግሪክ ባለቤትነት የተያዘች እና ሌላ ደግሞ በላይቤሪያ የተመዘገበች መርከብ ማለፋቸውን ጠቅሷል።

    ቢቢሲ የመረጃውን ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን አላጣራም።

    ባለፉት 40 ቀናት በወሽመጡ ላይ የሚደረግ የመርከብ እንቅስቃሴ የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

    ምንም እንኳ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ ወሽመጡ ክፍት ሆኗል።

    የተወሰኑ አገራት ቀደም ብሎ ከኢራን ጋር መርከቦቻቸው በወሽመጡ በኩል ያለምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    ከእነዚህ አገራት መካከል ፊሊፒንስ፣ ፓኪስታን እና ሕንድ ይገኙበታል።

    ቀሪው የዓለም አገራት መርከቦች ግን በወሽመጡ በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ ተደጋጋሚ ጥቃትን ከኢራን በኩል አስተናግደዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ በቆየባቸው ሳምንታት ውስጥ የነዳጅ ዘይት፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ነበር። ይህም የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈልገው ግብዓት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከኢራን ጦር ጋር በመተባበር እና “የቴክኒክ ቀርነቶችን ከግንዛቤ በማስገባት” ያለምንም ችግር ማለፍ ይቻላል ብለዋል።

  4. ለኢራን የጦር መሣሪያ ሲያቀርቡ የነበሩ አገራት ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ትራምፕ ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, YURI GRIPAS/POOL/EPA/Shutterstock

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢራን የጦር መሣሪያ ሲያቀርብ የነበረ አገር “አሁኑኑ ታሪፍ ይጣልበታል” አሉ።

    ትራምፕ በግል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ለኢራን የጦር መሣሪያ ሲያቀርብ የነበረ አገር ለአሜሪካ የሚሸጠው ማንኛውም ዕቃ ላይ "ከአሁን ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን” 50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልበት ተናግረዋል።

    ትራምፕ በዚሁ የማኅበራዊ ልጥፋቸው ላይ “ምንም የሚተው ወይንም የሚቀር ነገር የለም” ሲሉ ሙሉ በሙሉ ታሪፉ ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

    ትራምፕ ለኢራን መሣሪያ ሲያቀርብ ነበር ያሉትን አገር በስም አልጠቀሱም።

    ትራምፕ በዚሁ ልጥፋቸው ላይ ከኢራን ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር ትሰራለች ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “እኛ የወሰንነው በጣም ውጤታማ የሆነ የስርዓት ለውጥ ነው የተካሄደው!” ብለዋል።

    ትራምፕ ኢራን ዩራኒየም አታበለጽግም ያሉ ሲሆን አሜሪካ ከቴህራን ጋር በመሆን “ በጥልቅ የተቀበሩትን የኒውክሌር ብናኞች በመቆፈር ታስወግዳለች” ብለዋል።

    “አሁን በሳተላይት ቅኝት የት ስፍራ ላይ በትክክል እንደሚገኝ እየለየን ነው።”

    አክለውም “ጥቃት ከተፈጸመበት ዕለት ጀምሮ ምንም የተነካ ነገር የለም። ከኢራን ጋር ስለ ታሪፍ እና የማዕቀብ እፎይታ ተነጋግረናል፤ እየተነጋገርንም ነው። አብዛኞቹ 15 ነጥቦች ቀድሞውንም ከስምምነት ላይ ተደርሰዋል” ብለዋል።

  5. የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱ “በቀላሉ ሊጣስ” ይችላል አሉ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት አገራቸው ከቴህራን ጋር የገባችው የተኩስ አቁም ስምምነት “በቀላሉ ሊጣስ የሚችል ነው” በማለት ኢራን “በቀና ልቦና” ዘላቂ ለሆነ ስምምነት መደራደር አለባት አሉ።

    የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የምርጫ ቅስቀሳን ለመደገፍ በዋና ከተማዋ ቡዳፔስት የሚገኙት ቫንስ “ኢራናውያን ከእኛ ጋር በቀና ልቦና ለመሥራት ፈቃደኞች ከሆኑ” ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

    ነገር ግን “የደረስንበትን ደካማ የሆነ ስምምነት እንኳ እንዳይሳካ የሚያደርጉ ከሆነ ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኢራንን ከአሜሪkኣ ጋር በማደራደር ውስጥ ሚና የነበራቸው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በሁለቱ አገራት መካከል “ሁሉንም አለመግባባቶች ለመፍታት የሚያስችል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ድርድር" ለማድረግ የሚደረገውን ውይይት ኢዝላማባድ አርብ ዕለት እንደምታስተናግድ ተናግረዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቫንስ የአሜሪካ ተደራዳሪ ልዑካን ቡድንን እንደሚመሩ የዘገቡ ሲሆን፣ ዋሺንግተን ግን ይህንን አላረጋገጠችም።

  6. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኔቶ ዋና አዛዥ ጋር ተገናኙ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና አዛዥ ማርክ ሩቴ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና አዛዥ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ መገናኘታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ፕሬዝዳንቱ እና ዋና አዛዡ የተገናኙት በኢራን ጦርነት ምክንያት አሜሪካ ከሌሎቹ የጥምረቱ አባል አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከሻከረ በኋላ ነው።

    የኔቶ አባል አገራት አሜሪካ በኢራን የከፈተችውን ጦርነት መቀላቀል እንደማይፈልጉ ከገለጹ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገራቸውን 32 አባላት ካሉት ወታደራዊ ጥምረት እንደሚያስወጡ ተናግረዋል። ትራምፕን ከኔቶ ጋር ያቃቃረው የኢራን ጦርነትን የሚያስቆም የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም መደረጉ ይፋ ሆኗል።

    የኔቶ ዋና አዛዥ የሆኑት ሩተ ከትራምፕ ጋር ውጥረት ውስጥ የገቡባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ጥሩ ግንኙነት አዳብረዋል። የጂኦፖለቲካል ሁኔታው ቀውስ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ከትራምፕ ጋር የሚደረገው ንግግር የኔቶው አዛዥ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ፈተና ላይ እንደሚያስቀምጠው ተነግሯል።

  7. ተቋሞቻቸውን ከአሜሪካ ጥቃት ለመጠበቅ አደባባይ ወጥተው የነበሩት ኢራናውያን

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, መሠረተ ልማቶቻቸውን ከአሜሪካ ጥቃት ለመጠበቅ አደባባይ ወጥተው የነበሩት ኢራናውያን

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ሌሊት ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የኢራን መሠረተ ልማቶችን ለማውደም መዛታቸውን ተከትሎ የኢራን ባለሥልጣናት የአገሪቱ ዜጎች ዒላማ ወደሚሆኑት ተቋማት በመሄድ በዙሪያቸው ተሰባስበው እንዲከላከሏቸው ጥሪ አቅርበው ነበር።

    ሕዝቡም የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ አደባባይ ወጥቶ ታይቷል። በመጨረሻው ሰዓት አሜሪካ እና ኢራን ተኩስ ለማቆም ከስምምነት በመድረሳቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደዛቱት ጥቃቱ ሳይፈጸም ቀርቷል።

  8. የአውሮፓ አገራት ስለ አሜሪካ እና ኢራን ተኩስ አቁም ምን አሉ?

    የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

    አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገራት መሪዎች ትናንት ሌሊት ይፋ የተደረገውን የአሜሪካ እና ኢራን ተኩስ አቁም ስምምነት በበጎ ተቀብለውታል። መሪዎቹ ተኩስ አቁም ለመደረሱ ማን እውቅና ሊሰጠው ይገባል ስለሚለው እና በቀጣይ ምን መሆን አለበት ስለሚለው የተናገሩት እንዲህ ተጠናቅሯል።

    • የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ የተኩስ አቁሙ “ለቀጣናው እና ለዓለም የእፎይታ ጊዜ ያመጣል” ብለዋል። ስምምነቱ እንዲዘልቅ “ማድረግ የምንችለውን እናከናውን” ሲሉ ለአጋሮች ጥሪ አቅርበዋል።
    • የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው “ተኩስ አቁሞች ሁሉም ጥሩ ዜናዎች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን መንግሥታቸው “ዓለምን በእሳት ካነደዱ በኋላ በባልዲ ውሃ ይዘው ስለመጡ ብቻ ጭብጨባ" እንደማይቸር ገልጸዋል።
    • የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው አሜሪካ “ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መውሰዳቸው ጠቃሚ” መሆኑን ገልጸዋል። በድኅረ ጦርነት በሚኖረው የዓለም ሁኔታ ውስጥም “የሁሉንም አገር” ጥቅም ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ጠይቀዋል።
    • የአውስትሪያ ቻንስለር ክርስቲያን ስቶከር ደግሞ “የተሳካ የአደራዳሪነት ጥረት” አድርጋለች ላሏት ፓኪስታን ምስጋናቸውን ችረዋል። በተኩስ አቁም ስምምነት አማካኝነት የዲፕሎማሲ መስኮት “ከነበረው ጥቂት ከፍ ብሎ” ተከፍቷል። ብለዋል።
  9. የእስራኤል ጦር ኢራንን ማጥቃት ማቆሙን፣ የሊባኖስ ዘመቻውን ግን እንደሚቀጥል ገለጸ

    ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል ጦር ዛሬ ጠዋት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ፈጸመ። ይህ ጥቃት እስራኤል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስ ውስጥ ተግባራዊ እንደማታደርግ የሚጠቁም ሆኗል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ኢራን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማቆሙን፤ ሊባኖስ ውስጥ የሚያካሂደውን ዘመቻ ግን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

    በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ትይሬ እና ናባቲህ አካባቢዎች ረቡዕ ጠዋት ጥቃት የተፈጸመባቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ፤ የተኩስ አቁሙ በኢራን ከሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር የሚካሄደውን ግጭትም ያካትታል መባሉን ውድቅ አድርገዋል።

    የሊባኖስ መንግሥት እና ሄዝቦላህ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም። ስምምነቱን ያሸማገለችው ፓኪስታን በበኩሏ ተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጻለች።

    ባለፉት ቀናት ኢራን በምታደርገው ድርድር ውስጥ በሊባኖስ የሚደረገውን ግጭትም እንድታካትት ሄዝቦላህ መጠየቁ ተዘግቦ ነበር።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ “ኢራን ውስጥ የሚፈጽመውን ተከታታይ ጥቃት ማጠናቀቁን” ገልጿል። ከፖለቲካዊ አመራሩ “በደረው መመሪያ መሠረት” ኢራንን ማጥቃቱን እንዳቆመም አክሏል።

    እስራኤል ላይ ለሚፈጸም “ማንኛውንም ጥሰት ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን” ጠቅሷል።

    ሊባኖስ እና ሄዝቦላህን በተመለከተ ግን “የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዒላማ ያለውን የምድር ዘመቻ ማከናወኑን ይቀጥላል” ብሏል።

    እስራኤል በበኩሏ የሊባኖስ ግዛትን ተቆጣጥራ የመቆየት እንዲሁም ድንበሩ ውስጥ የደኅንነት ዞን የማቋቋም ዕቅድ እንዳላት ገልጻለች።

    የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስን የወረሩ ሲሆን ይህ እርምጃቸው የአገሪቱን ክፍሎች ተወርረው እንደተያዙ እንዲቀሩ ያደርጋል የሚል ስጋት ተፈጥሯል። እስራኤል ወርራ በምትቆየው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን እንደምታፈርስ እና ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንደማትፈቅድ አስታውቃለች።

  10. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጦርነቱ “ድል ማድረጓን” ገለጸች

    የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዋሽንግተን እና ቴህራን የተኩስ አቁም ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት አማካሪ ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ በተከታታይ የኢራን ጥቃቶችን ያስተናገደችው አገራቸው “ድል ማድረጓን” ተናገሩ።

    አማካሪው አንዋር ጋርጋሽ "ሉዓላዊነትን እና ክብርን እንዲሁም ክህደት በተሞላበት ጥቃት ፊት ስኬቶቻችን ባስጠበቀ ድንቅ ብሔራዊ መከላከያ ድል አድርገናል” ብለዋል።

    ኤምሬቶች ዛሬ ላይ “የገዘፈ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም፣ የሰላ ዕይታ እንዲሁም በወደፊቱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና ለመቅረጽ የሚያስችል ይበልጥ ጠንካራ አቅም” እንዳላት አማካሪው ጠቅሰናል። ይህንንም ተጠቅመን “ውስብስብ የሆነውን ቀጣናዊ ሁኔታ ለመምራት ወደፊት እንጓዛለን" ብለዋል።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ያከሸፋቸውን የኢራን ጥቃቶችን በተመለከተ በየጊዜው መደበኛው መረጃ ሲያወጣ ቆይቷል።

    ማክሰኞ ዕለት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ 2,221 ድሮን፣ 26 የክሩዝ ሚሳዔል እና 520 ባሊስቲክ ሚሳዔል ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተተኩሷል።

    የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን በበጎ ተቀብሎታል።

    ፓኪስታን ለማሸማገል ላከናወነችውን ሥራ ዕውቅና የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ፤ ወደ ቋሚ ተኩስ አቁም ለመድረስ ወደፊት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ "ጥረቶችን ማጠናከር" አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል።

  11. የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊባኖስንም ያካትታል?

    በእስራኤል ጥቃት የደረሰ ጉዳት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ቀጥላለች

    አሜሪካ እና ኢራን በደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ የሊባኖስ መካተት እና አለመካተት አካራካሪ ጉዳይ ሆኖ ወጥቷል።

    ኢራን እንዲሁም የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ያሸማገሉት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹህባዝ ሻሪፍ ስምምነቱ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጸዋል።

    በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የኢራን ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿ ጭምር ወደ ሊባኖስ አሰማርታለች።

    ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ግን የተደረሰው የተኩስ አቁም “ሊባኖስን አያካትትም” ብሏል።

    ነገር ግን በተኩስ አቁሙ ውስጥ ያሉ ቁልፍ ጉዳዮች የበለጠ መብራራት ያስፈልጋቸዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ እግረኛ ወታደሮቿን ያሰማራችው እስራኤል፣ ከሄዝቦላህ በኩል የሚመጣ ማንኛውም ዓይነት ስጋት እስኪወገድ ድረስ ወታደሮቿ ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ እንደሚቆዩ አስታውቃለች።

    እስራኤል በአካባቢው የሄዝቦላህ አባላት ይንቀሳቀሳሉ በማለት ቤቶች እና መንደሮችን በማፍረሷ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል። ከአካባቢው ሄዝቦላህ እስኪወገድ ድረስ ነዋሪዎቹ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እንደማይፈቀድላቸውም አስታውቃለች።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም መደረሱ ከመገለጹ ቀደም ብሎ በደቡባዊ ሊባኖስ ሲዶን ከተማ ውስጥ በተፈጸመ የእስራኤል ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውን እና 22 መቁሰላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን ቀጥሏል።

  12. አሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቀነሰ

    ነዳጅ ማደያ ላይ እየቀዳ ያለ ሠራተኛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት የሚያደርግ የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳየ።

    ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋን ለመለካት ጥቅም ላይ የሚውለው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ የአንድ በርሜል ዋጋ በ13 በመቶ ገደማ ቀንሶ 94.80 ዶላር ገብቷል። በአሜሪካ የሚሸጠው ነዳጅ ደግሞ የ15 በመቶ ቅናሽ በማሳየት ዋጋው 96.75 ዶላር ደርሷል።

    አሁንም ቢሆን ግን የነዳጅ ዋጋ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ሲሸጥ ከነበረበት በበርሜል 70 ዶላር ገደማ ዋና የጨመረ ሆኖ ቀጥሏል።

    በአሜሪካ እና ኢራን ጥቃት ተከፈተባት ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም ከዛተች በኋላ የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦች የተስተጓጎለ፣ ሲሆን የኤነርጂ ዋጋም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

    ወሽመጡ መዘጋቱን ተከትሎ ለረጅም ጊዜ ባሕር ላይ የቆዩ በርካታ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በአሁኑ ስምምነት እንዲያልፉ እንደሚፈቀድላቸው ይጠበቃል። የመርከቦቹ ማለፍ ለዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

  13. አሜሪካ እና ኢራን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ

    በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ነዋሪዎች የሁለት ሳምንቱን የተኩስ አቁም በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ ነዋሪዎች የሁለት ሳምንቱን የተኩስ አቁም በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋል

    ኢራን እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ መርከቦች እንዲያልፉ የሚያስችል የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ።

    ሁለቱ አገራት እዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ወሳኙን የባሕር መተላለፊያ ማክሰኞ ሌሊት ድረስ ማትከፍት ከሆነ “ዛሬ ማታ ሙሉ ሥልጣኔ ይወድማል” የሚል ዛቻ ካሰሙ ከሰዓታት በኋላ ነው።

    አገራቱን ሲያሸማግሉ የነበሩት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ የተኩስ አቁሙ ወዲያውኑ ገቢራዊ መሆን እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ቴህራን ከባሕረ ሰላጤው የሚወጡ የነዳጅ እና ሌሎች ምርቶች መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ የምትከፍት ከሆነ “ሁለት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ኢራን ላይ የሚፈጸመውን ድብደባ እና ጥቃት ለማቆም” መስማማታቸውን ገልጸዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በዚህ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም የተስማሙት “ሁሉንም ወታደራዊ ግብ ስላሳኩ እና ከዚያም በላይ” ስላገኙ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

    በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ኢራን ከወታደራዊ ኃይሏ ጋር በመቀናጀት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦች እንዲያልፉ ትፈቅዳለች።

    ኢራን በበኩሏ 10 ነጥቦች ያሉት እቅድ ይፋ አድርጋለች። በእቅዱ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና የመን ውስጥም ጥቃቶች መቆም አለባቸው የሚል ነው።

    ኢራን ላይ የተጣሉ ማእቀቦችን ለማንሳት “ሙሉ ቁርጠኝነት” እንዲኖር ማድረግ፣ በአሜሪካ የተያዙ የኢራን ገንዘብ እና ሀብቶችን መልቀቅ እንዲሁም በአገሪቱ ላይ የደረሰው ውድመት “መልሶ የሚገነባበትን ወጪ የሚሸፍን ሙሉ የካሳ ክፍያ” መፈጸሙም በእቅዱ ውስጥ ተጠቅሰዋል።

    የአገሪቱ መንግሥት፤ “ኢራን ማንኛውም የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት ላለመፈለግ ሙሉ ቁርጠኛ ይሆናል” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።

    የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ይህ ”የኢራን ድል በፖለቲካዊ ድርድር ላይም ይጸናል” ብሏል።

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ፤ የተኩስ አቁሙ እስራኤል በኢራን የሚደገፈውን ሄዝቦላህ ላይ ዘመቻ ከፍቻለሁ ባለችበት ሊባኖስ ውስጥም ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    የእስራኤል ባለሥልጣናት ግን በሄዝቦላህ የተጋረጠው ስጋት እስከሚወገድ ድረስ ከሊባኖስ እንደማይወጡ ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ የተኩስ አቁሙ ይፋ ከተደረገ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ “ኢራን በአፋጣኝ ሆርሙዝ ወሽመጥን የምትከፍት እንዲሁም አሜሪካ፣ እስራኤል እና ሌሎች የቀጣናው አገራት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት የምታቆም መሆኗን ተከትሎ የሚሰነዘርባት ጥቃት ለሁለት ሳምንት እንዲቆም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያስተላለፉትን ውሳኔ እስራኤል ትደግፋለች” ብለዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አክሎም “የተኩስ አቁሙ ሊባኖስን አያካትትም” ሲሉ እስራኤል እግረኛ ወታደሮቿን ባሰማራችባት ጎረቤት አገር ተፈጻሚ እንደማይሆን ገልጿል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የተኩስ አቁም ለማድረግ ውሳኔ ባሳለፉበት ሂደት ውስጥ እስራኤል ምን ያህል ተሳትፎ እንደነበራት ግልጽ አይደለም።

  14. በሆርሙዝ ላይ ለተመድ የቀረበው ውሳኔ በሩሲያ እና በቻይና ውድቅ ሆነ

    የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ድምጽ ሲሰጡ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ድምጽ በሰጡበት ጊዜ

    ለሆርሙዝ ወሽመጥ በተቀናጀ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግ በባሕረ ሰላጤው አገራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሩሲያ እና በቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ውድቅ ሆነ።

    ከምክር ቤቱ አባለት አስራ አንዱ የውሳኔ ሃሳቡን ሲደግፉ፣ ፓኪስታን እና ኮሎምቢያ ድምጻቸውን አቅበዋል፤ ሩሲያ እና ቻይና ስለተቃወሙት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

    የውሳኔ ሃሳቡ ረቂቅ ላይ ለሳምንታት ድርድር ሲደረግ ቆይቶ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመጠበቅ ወታደራዊ ኃይል መጠቀምን የሚፈቅደው ክፍል እንዲቀር ተደርጎ አገራት የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱ በሚል ተለውጦ ነበር።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስሰብባን የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አብዱላጢፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ በሰብሳቢነት መሩት ነበር።

    ሰብሳቢው ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት የውሳኔ ሃሳቡ አዲስ ሁኔታን የሚፈረር ሳይሆን፣ በሆርሙዝ ላይ ኢራን የፈጠረችውን ተደጋጋሚ ችግር ለማስቆም አስፈላጊ በመሆኑ የቀረበ ነው ሲሉ አስረድተው ነበር።

    የውሳኔ ሃሳቡ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ ወሳኝ የባሕር መተላለፊያ መስመሮችን በመሳሪያነት መጠቀምን በማበረታታት ከሆርሙዝ ባሻገር በሌሎችም ቦታዎች እንዲደገም በማድረግ ዓለምን ወደ ሕግ አልነባት ያሸጋግራታል ብለዋል።

    ውሳኔውን ድምጽን በድምጽ በመሻር ውድቅ ያደረጉት ቻይና እና ሩሲያ በሆርሙዝ መዘጋት እምብዛም ችግር እንዳልገጠማቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

    ቻይና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መርከቦቻቸው ያለችግር መተላለፍ ከቻሉ አገራት መከካል እንዷ ስትሆን፣ ሩሲያ ደግሞ ተጥሎባት የነበረው የነዳጅ ሽያጭ ማዕቀብ በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት ላልቶላታል።

  15. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአገራቸው የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ እየቀረበባቸው ነው

    የአሜሪካ ምክር ቤት ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዳንት ትራምፕ ኢራን ከተቀመጠላት የጊዜ ገደብን በፊት ስምምነት ላይ ካልሰደረች “ሥልጣኔዋ በአንድ ሌሊት ያከትማል” ማለታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

    በተለይ የትራምፕ ፓርቲ ተቀናቃኝ የሆኑት የዲሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴዎች በቶሎ መፍትሄ እንዲፈለግ እየጠየቁ ነው።

    በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የዲሞክራቶች መሪ የሆኑት ቸክ ሹመር "ይህ ግለሰብ በጣሙን የታመመ ሰው ነው። ይህንን የግድየለሽነት ጦርነት ለመቃወም ፈቃደኛ ያልሆኑ እያንዳንዳቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ለትኛውም ዓይነት አስከፊ ዳፋ ኃላፊነት አለባቸው" ሲሉ ሪፐብሊካንን ወቅሰዋል።

    የዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪው ሐኪን ጄፍሪስ በበኩላቸው "ዶናልድ ትራምፕ በግዴለሽነት የገባበት የኢራን ጦርነት ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ሳያስገባን በፊት ምክር ቤቱ ማስቆም አለበት። ይህንን እብደት በማስቆም በኩል ሁሉም ሪፐብሊካኖች ብሔራዊ ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።

    የምክር ቤት አባሉ ጄሰን ክሮው ደግሞ የአንድን አገር "ሥልጣኔን ለማጥፋት መዛት የጦር ወንጀል ነው። በተደጋጋሚ እንዳልኩት ጦር ሠራዊታችን ሕጋዊ ትዕዛዞችን ብቻ ነው መከተል ያለበት። መልካም ህሊና ያላቸው ሁሉም አሜሪካውያን ይህንን ድርጊት መቃወም አለባቸው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

    ሌላኛው የምክር ቤት አባል ጂም ማክጋቨርን “ይህ የለየለት ክፋት ነው። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የጦር ወንጀል ለመፈጸም የሚሰነዝረው የዘር ማጥፋት ዛቻ በፌደራል እና በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ነው" በማለት የፕሬዝዳንቱን ንግግር ነቅፈዋል።

  16. ትራምፕ አስካሁን ምን ያህል ጊዜ ለኢራን የጊዜ ገደብ አስቀመጡ?

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የኢራኑ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የኢራኑ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃት ከተጀመረበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።

    ጦርነቱ በጀመረ በመጀመሪያው ሳምንት ኢራን እጅ የማትሰጥ ከሆነ ከባድ ውድመት እንደሚደርስባት በመገልጽ ፕሬዝዳንቱ ከማስጠንቀቅ አልፈው ከስድስት ሳምንት በኋላ የኢራንን ሥልጣኔ በአንድ ሌሊት ዶግ ዓመት እንደሚያደርጉት እየዛቱ ነው።

    ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያወጧቸው ማስጠንቀቂያዎች እና የጊዜ ገደቦች እየተራዘሙ አሁን ዛሬ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የሚጠናቀቀው የመጨረሻው የኢራን መሪዎች ያላቸው ዕድል መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

    ለመሆኑ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለምን ያህል ጊዜ ማስጠንቀቂያ እና የጊዜ ገደብን አስቀመጡ?

    • መጀመሪያ፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም. ኢራን በ48 ሰዓታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥን ካልከፈተች “ከትልቁ ጀምሮ ያሏት የኃይል ማመንጫዎች ፍረስርሳቸው ይወጣል” ብለው ዝተው ነበር።
    • ሁለተኛው፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ከኢራን ጋር “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ ንግግር’ መደረጉን በመግለጽ የጥቃቱን ቀነ ገደብ በአምስት ቀናት አራዘሙት።
    • ሦስተኛው፡ መጋቢት 18/2018 ዓ.ም. ደግሞ “በኢራን መንግሥት ጥያቄ መሠረት” የኃይል መሠረተ ልማቶችን የማጥቃት ቀነ ገደባቸውን በ10 ቀናት ማራዘማቸውን ሰኞ መጋቢት 28ን የመጨረሻው ቀን አደረጉት።
    • የ48 ሰዓታት ማስጠንቀቂያ፡ የሰኞው ቀነ ገደብ በተቃረበበት ጊዜ ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ላይ “መአት” ከማዝነቸባው በፊት “48 ሰዓታት” እንደቀሩ አስጠንቅቀው ነበር።
    • ባለፈው ዕሁድ፡ አስነዋሪ ቃላትን በመጠቀም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ በሰዓታት ውስጥ የማይከፈት ከነሆ ኢራን ‘ሲኦል” እንደምትሆን ዝተዋል።
    • የማክሰኞው ማስጠንቀቂያ፡ ዛሬ ማክሰኞ አስከ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ኢራን የቀረበላትን የድርድር ሃሳብ የማትቀበ ከሆነ "ሥልጣኔዋ ተመልሶ እንዳይመጣ ሆኖ ይሞታል" ሲሉ ዝተዋል።
  17. ስለ ነዳጅ ልናውቃቸው የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች

    ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባትን ጦርነት ተከትሎ ዋነኛው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ነዳጅ ምርት መተላለፊያ የሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል።

    በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የነዳጅ አቅርቦት የቀነሰ ሲሆን፣ ዋጋውም ጭምሯል።

    ለመሆኑ ነዳጅ ስንል ምን ማለታችን ነው? ኢትዮጵያ ከየትኞቹ አገራት ነው ነዳጅ የምታገኘው? በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ እንዴት ይወሰናል?

    ብሬንት ነዳጅ የሚባለው ምንድን ነው? የትኞቹ አገራት ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት አላቸው? ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ቁልፍ ጉዳዮችን ከስር ካሉት ሰሌዳዎች ላይ ይመልከቱ።

  18. ዛሬ ሌሊት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ. . . ያበቃለታል” - ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኢራን የቀረበላትን ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ተግባራዊ የማታደርግ ከሆነ "ሙሉ ስልጣኔዋ ዛሬ ሌሊት ይሞታል" ሲሉ በጠንካራ ቃላት አስጠነቀቁ።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ሌሊት የሚጠናቀቀውን ለኢራን ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ባለፉት ቀናት ሲሰጡ የነበረውን ማስጠንቀቂያ አዘል ዛቻን አጠናክረው ደግመውታል።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ባሰፈሩት መልዕክት “ሥልጣኔ ተመልሶ በማይመጣበት ሁኔታ ዛሬ ምሽት ያበቃለታል” ሲሉ በኢራን ላይ ዝተዋል።

    ትራምፕ ጨምረውም:

    "ያ እንዲሆን አልፈልግም፣ ነገር ግን ሳይከሰት አይቀርም። ቢሆንም ግን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ እና አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥ አለ፤ የተለዩ ብልህ እና ብዙም ጽንፈኛ ያልሆኑ የበላይነትን ይይዛሉ፤ ምናልባትም የሚያስደንቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤ ማን ያውቃል?" በማለት ጽሁፋቸው ላይ የጠየቁት ትራምፕ ዛሬ ሌሊት ሊከሰት የሚችለውን አመልክተዋል።

    "በዓለም ረጅም እና ውስብስብ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆነውን ነገር ዛሬ ማታ የምናየው ይሆናል። የ47 ዓመታት ጭቆና፣ ሙስና እና ሞት በመጨረሻም ያበቃል። እግዚአብሔር ታላቁን የኢራን ሕዝብ ይባርክ!”

    ትራም ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመክፈት የተኩስ አቁም ሃሳብን እንድትቀበል ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ማክሰኞ ሌሊት ለረቡዕ አጥቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ያበቃል።

    ኢራን የተኩስ አቁም ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ጦርነቱ እንዲቆም፣ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት እና የሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች መሟላትን በመጠየቅ የራሷን ቅድመ ሁኔታዎች አቅርባለች።

    በሌላ በኩል ደግሞ በፓኪስታን መሪነት ዲፕማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ በቀሩት ሰዓታት አንዳች ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ለስድስት ሳምንታት የተካሄደው ጦርነት ወደ አደገኛ ደረጃ ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

  19. የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሳዑዲ ፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

    ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሳዑዲ አረቢያን የፔትሮኬሚካል ፋብሪካዎችን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ከፍተኛ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ።

    በጥቃቱ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአሜሪካ የፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ በመካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎች እና በአጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች “የተሳካ ጥቃት” መፈጸሙን አመለክቷል።

    ዘቡ እንዳለው ከተቋማቱ በተጨማሪ “በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጥቅሞች እና ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲሁም እስራኤል ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ የዕዝ እና የቁጥጥር ማዕከላት” ዒላማ መሆናቸውን ገልጿል።

    በመግለጫው ላይ ኢራን ይህንን እርምጃ የወሰደችው ሰኞ ዕለት “በአሳሉዬህ የፔትሮኬሚካል ማዕከል” ላይ የተፈጸመባትን ጥቃት ለመበቀል መሆኑ ተጠቅሷል።

    አብዮታዊ ዘቡ አሜሪካ “ቀይ መስመራችንን የምታልፍ ከሆነ ምላሻችን ከመካከለኛው ምሥራቅም የሚያልፍ ይሆናል” በማለት አስጠንቅቋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ እና አጋሮቿ ኢራን ዒላማ የምታደርጋቸው ቦታዎች ውስን ሆነው ቆይተው” የነበረ መሆኑን ገልጿል።

    ይህ ለመልካም ጉርብትና ሲባል ኢራን አሳይታው የነበረው “ቁጥብነት” ዒላማዎችን እንድትለይ አድርጓት መቆየቱን፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ “ይህ ቁጥብነት እንደማይኖር” በመጥቀስ አስፈላጊ በተባሉ ዒላማዎች ላይ “ያለማወላወል” እርምጃ ይወሰዳል ብሏል።

  20. በቱርክ ኢስታንቡል የእስራኤል ቆንስላ አካባቢ "ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው" ተገደሉ

    በእስራኤል ቆንስላአካባቢ የቱርክ ፖሊስ በብዛት ይገኛል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በቱርክ ኢስታንቡል በሚገኘው የእስራኤል ቆንስላ አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    በተኩሱ ሁለት ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸውም የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    መገናኛ ብዙኃኑ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች “እርምጃ ተወስዶባቸዋል’ ያሉ ሲሆን ቢያንስ ሁለቱ መገደላቸውን አስታውቀዋል።

    የቱርክ የአገር ውስጥ ሚኒስትር በፖሊስ ጋር ተኩስ የከፈቱት ሦስት ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

    የኢስታንቡል አስተዳዳሪ ከአጥቂዎቹ ውስጥ አንዱ መገደሉን እና ሁለቱ ላይ ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ለሲኤንኤን ተርክ ተናግረዋል።

    "በፖሊስ ኃይላችን ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። ሁለቱ ፖሊሶቻችን ቆስለዋል። ከአሸባሪዎች ውስጥ አንዱ ተገድሏል። ሁለቱ ደግሞ በተወሰደባቸው እርምጃ ቆስለዋል" ያሉት ገዢው ጥቃቱ ትልቅ ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አነስተኛ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

    በቱርክ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የእስራኤል ዲፕሎማት አለመኖሩን ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ምንጮችን ጠቅሰው ዘግበዋል።

    የእስራኤል ኤምባሲ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የሚገኝ ሲሆን በኢስታንቡል ያለው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ነው።

    የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር በቆንስላው አካባቢ ስለተከፈተው ተኩስ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

    በርካታ የፖሊስ አባላት በቆንስላው አካባቢ ታይተዋል። ቆንስላው የሚገኘው በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል ሰሜናዊ ክፍል ነው።

    ጥቃቱ የተፈጸመው በቀጣናው እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ውጥረቶች በተባባሱበት ወቅት ነው።