ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፈጸም "እንዳይጣደፉ" አሳሰቡ

አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት የሚያደርጉት ድርድር ወደ ማጠናቀቂያው እንደተቃረበ መነገሩን ተከትሎ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደራዳሪዎቻቸው “በጥድፊያ" ከኢራን ጋር "ስምምነት እንዳይፈጽሙ” አዘዙ። በሁለቱ አገራት ንግግር እየተደረገበት ያለው የስምምነት ዕቅድ ከያዛቸው ነጥቦች መከካከል፤ የተኩስ አቁሙን ለ60 ቀናት ማራዘም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መክፈት እንዲሁም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም በተመለከተ ተጨማሪ ድርድር ማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፈጸም "እንዳይጣደፉ" አሳሰቡ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት የሚያደርጉት ድርድር ወደ ማጠናቀቂያው እንደተቃረበ መነገሩን ተከትሎ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደራዳሪዎቻቸው ከኢራን ጋር “ተጣድፈው ወደ ስምምነት እንዳይገቡ” አዘዙ።

በሁለቱ አገራት ንግግር እየተደረገበት ያለው የስምምነት ዕቅድ ከያዛቸው ነጥቦች መከካከል የተኩስ አቁሙን ለ60 ቀናት ማራዘም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መክፈት እንዲሁም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም በተመለከተ ተጨማሪ ድርድር ማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።

ትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ንግግሩ “ገንቢ” በሆነ ሁኔታ እየተካሄዱ መሆኑን ቢገልጹም፤ አክለው ግን “ሁለቱም ወገኖች ጊዜያቸውን መውሰድ እና በትክክል ማከናወን አለባቸው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት ስምምነቱ “በአብዛኛው ድርድር እንደተደረገበት” መገናራቸው ስምምነት ይፋ መደረጉ አይቀሬ ነው የሚል ግምት ፈጥሮ ነበር።

የኢራን ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ ሀሳብ አመልክተው ነበር። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ለመድረስ “እጅግ ቅርብ እና እጅግ ሩቅ” ናቸው ብለው ነበር።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡ ከሆነ ድርድር የሚካሄድበት እቅድ የመጨረሻው ስምምነት አይደለም። ይልቁንም ሁለቱ አገራት የተወሰኑ አጨቃጫቂ ጉዳዮች በኋላ ድርድር እንዲካሄድባቸው እንደሚፈቅድ ዘግበዋል።

ኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚነሳበት መጠን እና ጊዜ፣ የታገደውን የኢራን ገንዘብን የማስለቀቅ ጉዳይ እንዲሁም አሜሪካ የቴህራንን የኒውክሌር ፍላጎት ለመገደብ ያላት ፍላጎት ለበኋላ ድርድር ከሚተዉ ነጥቦች መካከል ናቸው።

ይህ የስምምነት ዕቅድ ሪፐብሊካኖችን ለሁለት የከፈለ ሲሆን የተወሰኑት ኢራን ላይ ለዘብተኛ አቋም የያዘ እንደሆነ በይፋ እየተናገሩ ነው።

ትራምፕ እሁድ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ልትሰራ እንደማትችል “መረዳት እንዳለባት” በአጽንኦት አንስተዋል። ቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ እንደሚውል በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

አንዳንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ጋር በሚደረሰው ስምምነት አማካኝነት ኢራን የበለጸገ ዩራኒየሟን አሳልፋ እንደምትሰጥ ዘግበዋል።

የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ለአገሪቱ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ቴህራን “ፍላጎቷ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳልሆነ ለዓለም ለማረጋገጥ” ዝግጁ እንደሆነች ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በድርድሩ “ጉልህ” መሻሻል ቢታይም፤ ሂደቱ “የመጨረሻ ደረጃ እንዳልደረሰ” ገልጸው ነበር።