ቀጥታ, ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለቀሪዎቹ የተኩስ አቁሙ ቀናት መከፈቱን አስታወቀች

የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለቀረው የተኩስ አቁም ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ክፍት እንዲሆን መታወጁን” ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አስታወቁ። ለኢራን ውሳኔ ምላሽ የሰጡት አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አመሰግናለሁ” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለቀሪዎቹ የተኩስ አቁሙ ቀናት መከፈቱን አስታወቀች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለቀረው የተኩስ አቁም ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ክፍት” እንደሚሆን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አስታወቁ።

    አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ሊባኖስ ውስጥ በተደረሰው ተኩስ አቁም መሰረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የሁሉም የንግድ መርከቦች ጉዞ ለቀሪው የተኩስ አቁሙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን ታውጇል” ብለዋል።

    ለ40 ቀናት የተዋጉት አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን አሸማጋይነት የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም መፈጸማቸው ይታወሳል። ይህ ተኩስ አቁም በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ይጠናቀቃል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የመርከቦቹ ጉዞ የሚካሄደው “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የወደብ እና ማሪታይም ድርጅት አስቀድሞ ባሳወቀው የተቀናጀ መስመር” በኩል እንደሆነም ገልጸዋል።

    ለኢራን ውሳኔ ምላሽ የሰጡት አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አመሰግናለሁ” ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    ትራምፕ፤ “ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ክፍት መሆኑን እና ለሙሉ ጉዞ ዝግጁ መሆኑን አሁን አስታውቃለች። አመሰግናለሁ!" ብለዋል።

    የካቲት ላይ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ብዙ ከዓለም ነዳጅ ማጓጓዣ መስመሮች መካከል በርካታ መርከቦችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታ ቆይታለች።

    ለዚህ እገዳ ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ ደግሞ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በወሽመጡ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች ጉዞ እንዳይደረግ ከልክላለች።

  2. የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ሄዝቦላህ ላይ የተከፈተው ዘመቻ “አሁንም አልተጠናቀቀም” አሉ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    እስራኤል፤ ዳግም ውጊያ የሚጀመር ከሆነ ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ላይ ያሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ሊባኖሳውያን በድጋሚ ከደቡብ ሊባኖስ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቋን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ዘገበ።

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው፤ ሊባኖስ ውስጥ የተፈጸሙ ጥቃቶች “በርካታ ግቦችን ማሳካታቸውን” ተናግረዋል። ቢሆንም ግን ሄዝቦላህ ላይ የተከፈተው ዘመቻ “አሁንም እንዳልተጠናቀቀ” ገልጸዋል።

    “ዳግም ውጊያ ከተጀመረ ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ እንዲቻል ወደ ደኅንነት ዞኑ የተመለሱት እነዛ ነዋሪዎች ለቅቀው መውጣት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

    የእስራኤል ጦር "አፅድቶ የተቆጣጠራቸውን" ቦታዎች በሙሉ ይዞ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ በሰጠው አስተያየት “"ማንኛውም የተኩስ አቁም በመላው የሊባኖስ ግዛት ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት፤ ለጠላት እስራኤል ምንም ዓይነት የእንቅስቃሴ ነፃነት ሊፈቅድ አይገባም" ብሏል።

  3. የሄዝቦላህ አመራር ቡድኑ “መቼም ትጥቅ እንደማይፈታ” ለቢቢሲ ተናገሩ

    የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ዋፊቅ ሳፋ

    ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱት የ10 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከቢቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራር ዋፊቅ ሳፋ ቡድን “መቼም፣ ጭራሽ” ትጥቅ እንደማይፈታ ገለጹ።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት በቀጣይ ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር የተቀመጠ መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።

    ስለ ትጥቅ መፍታት የተጠየቁት ሳፋ ግን “ተገቢ ተኩስ አቁም፣ ትክክለኛ የሆነ እስከሚደረስ አይደረግም" ብለዋል።

    "እስራኤል ለቅቃ እስካልወጣች ድረስ አይሆንም። እስረኞች ከመመለሳቸው፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው ከመመለሳቸው እና መልሶ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ትጥቅ መፍታት አይኖርም። እስከዚያው ድረስ ስለ ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ ማውራት አይቻልም” ሲሉ ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን ዘርዝረዋል።

    ቤይሩት ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ የተደረገው ይህ ቃለ መጠይቅ በሄዝቦላህ እና በቀጣናዊ አጋሩ ኢራን መካከል ያለውን ቅንጅት ያሳያል። “ሄዝቦላህ እና ኢራን በአንድ ሰውነት ውስጥ ያሉ ሁለት ነፍሶች ናቸው” ብለዋል።

    “ያለ ኢራን ሄዝቦላህ ሊኖር አይችልም። ያለ ሄዝቦላህም አራን አትኖርም” ሲሉ በሁለቱ አካላት መካከል ስላለው “ሃይማኖታዊ፣ ሕጋዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ” ግንኙነት ገልጸዋል።

    የሺዓ እስልምና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቡድን የሆነው ሄዝቦላህ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ እስራኤል እና በርካታ የዓለም አገራት በሽብርተኛ ድርጅትነት ተፈርጇል።

    ቡድኑ የአሁኑን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተቀላቀለው የካቲት ላይ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ከተኮሰ በኋላ ነበር።

    ሄዝቦላህ ይህንን ጥቃት የፈጸመው በኢራን ጠቅላይ መሪ ላይ ለተፈጸመው ግድያ እንዲሁም ከህዳር 2016 ዓ.ም. አንስቶ እስራኤል በየቀኑ በሚባል ደረጃ ሊባኖስ ላይ ስትፈጽም ለነበረው ጥቃት በአጸፋ ምላሽነት መሆኑን ገልጿል።

    እስራኤልም ከፍተኛ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም እና ደቡባዊ ሊባኖስን በእግረኛ ወታደሮች በመውረር ምላሽ ሰጥታለች። ሄዝቦላህ ትጥቅ እስከሚፈታ ድረስም ይህንን ዘመቻ እንደምትቀጥል ተናግራለች።

    ሄዝቦላህ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሊባኖስ ጥቅም ወይስ ለኢራን የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሳፋ፤ “ያለ ምንም ጥርጥር ሄዝቦላህ የሚመለከተው የሊባኖስን ጥቅም ነው” ብለዋል።

    ኢራን ተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ያሳደረችውን ግፊት ጨምሮ የምታደርጋቸው ድጋፎች ሊባኖስን ማገዛቸውን ጠቅሰዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸውን ጨምሮ በርካታ ሊባኖሳውያን ግን ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ይፈልጋሉ። አገሪቱን ግጭት ውስጥ ከትቷል ሲሉም ይወቅሳሉ።

    ሄዝቦላህ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እና ሰፋ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጡ እንዲሁም እስራኤል የደኅንነት ጥያቄዎቿን አጥብቃ በመያዟ የተነሳ በሊባኖስ ተግባራዊ የሚሆን ማንኛውም ተኩስ አቁም ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ግጭት ለጊዜው ከመግታት ያለፈ ጥቅም ላይኖረው ይችላል።

  4. ኢራን የሊባኖስ ተኩስ አቁምን በበጎ እንደምትቀበለው ገልጻ ሄዝቦላህ ያደረገውን “ተጋድሎ” አወደሰች

    የሄዝቦላህን ባንዲራ የያዘ ታዳጊ ሌላ አዋቂ ሰው በሚነዳው ሞተር ላይ ተሳፍሮ

    የፎቶው ባለመብት, Adnan Abidi / Reuters

    ኢራን በሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እና የሄዝቦላህ “ተጋድሎ” ውጤት እንደሆነ ገለጸች።

    ቴህራን የተኩስ አቁሙን የምትመለከተው በፓኪስታን አሸማጋይነት ከአሜሪካ ጋር የተደረሰው ሠፊ መግባባት አካል አድርጋ እንደሆነ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባቃኢ ተናግረዋል።

    ኢራን ሰፊ ቀጣናዊ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ያለ ማቋረጥ ግፊት ስታደርግ መቆየቷንም በአጽንኦት አንስተዋል።

    የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተኩስ አቁም ላይ ለመደረሱ ለሄዝቦላህ እውቅና ሰጥተዋል። የፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ኤክስ ገጻቸው ላይ በአረብኛ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ስምምነቱ “የሄዝቦላህ የጽናት እና የአክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ የአንድነት ውጤት እንጂ ሌላ አይደለም” ብለዋል።

    አፈ ጉባኤው የጠቀሱት ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ኢራን በቀጣናው ከሚገኙ አጋር ታጣቂ ቡድኖች ጋር የፈጠረችውን መረብ ለመግለጽ የምትጠቀምበት ስያሜ ነው።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ የኩስድ ኃይሎች አዛዥ የሆኑት ኢስማኢል ቃኒ በበኩላቸው ሄዝቦላህን “ባለ ድል” ሲሉ ጠርተዋል። ስምምነቱ የሊባኖስ የትግል ኃይሎች የጽናት እና የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ድጋፍ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃንም የሊባኖስ ተኩስ አቁምን በተመለከቱ ዘገባዎቻቸው ያስተጋቡት የሄዝቦላህ “ተጋድሎ” እና የቴህራን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ውጤት ነው የሚለውን የከፍተኛ ባለሥልጣናቱን አገላለጽ ነው።

  5. ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ጥሰቶች ከተፈጸሙ ‘ጣቴ ቃታ ላይ ነው’ አለ

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ለስድስት ሳምንታት ባካሄደችው የኤር ድብደባ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው
    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ለስድስት ሳምንታት ባካሄደችው የኤር ድብደባ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው

    ሄዝቦላህ በሊባኖስ እየተካሄደ ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት እስራኤል "ክህደት" ከፈጸመች "ጣቴ ቃታ ላይ ነው" ሲሉ አስታወቀ።

    በኢራን የሚደገፈው ቡድን በቴሌግራም ላይ ባወጣው መግለጫ እስካሁን ድረስ በግጭቱ ወቅት ያከናወናቸውን ተግባራት ሲገልጽ እአአ ከመጋቢት 2 እስከ ሚያዝያ 16 ባለው ጊዜ ውስጥ በእስራኤል ላይ 2 ሺህ 184 ዘመቻዎችን እንደፈጸመ ተናግሯል።

    እንግሊዝ እና አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ አገሮች በሽብርተኛ ድርጅትነት የፈረጁት ሄዝቦላህ በተኩስ አቁም ድርድሩ ውስጥ አልተሳተፉም። ድርድሩ በእስራኤል እና በሊባኖስ መንግሥታት መካከል የተከናወነ ነው።

    ሐሙስ ዕለት ስለተገለጸው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሹን የሰጠው ሄዝቦላህ፤ "ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት በመላው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ ተፈጻሚ መሆን አለበት። ጠላት የሆነችው እስራኤል የመንቀሳቀስ ነፃነት ሊፈቀድላት አይገባም” ብሏል።

    እስራኤል ለ10 ቀናት የሚቆይ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ብትስማም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ወታደሮች እስከ የተኩስ አቁም መጨረሻ ድረስ በሊባኖስ ግዛት "የደህንነት ቀጠና" ውስጥ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

  6. ፓኪስታን በሊባኖስ የተደረሰውን የተኩስ አቁም አወድሳ የትራምፕን “ብልሃት” የተሞላበት ዲፕሎማሲ አደነቀች

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል ለአስር ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት በመደረጉ መደሰታቸውን ገልጸው፣ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን "ደፋር እና ብልህ የዲፕሎማሲ ጥረቶች" አወድሰዋል።

    ሸሪፍ አገራቸው "ለሊባኖስ ሉዓላዊነት እና ለግዛት አንድነት ያላትን የማይናወጥ ድጋፍ" አጽንኦት ሰጥተዋል።

    በዚህ ሳምንት በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል በዋሺንግተን ውይይት የተደረገ ሲሆን ይህም በጎረቤት አገራቱ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ታሪካዊ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

    ይህ የሆነው ባለፈው ሳምነት መጨረሻ በፓኪስታን አስተናጋጅነት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተደረገው ድርድር ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ነው።

    ኢዝላማባድ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ተግባራዊ የሆነውን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በማደራደር ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ ሐሙስ ዕለት የተኩስ አቁሙን ለማራዘም በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ለመነጋገር በቴህራን ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር እንደተገናኙ የሚገልጹ ዘገባዎች ወጥተዋል።

  7. ዩኬ እና ፈረንሳይ 40 አገራት የሚሳተፉበት በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ የሚመክር ጉባዔ ዛሬ ያካሄዳሉ

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን (በስተግራ) የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመርን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዩኬ እና ፈረንሳይ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቦችን እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ ስለሚኖረው የጋራ ጥረት ለመወያየት ከአጋሮቻቸው ጋር ስብሰባ ሊያደርጉ ነው።

    ቴህራን ለአሜሪካ እና ለእስራኤል ጥቃቶች ምላሽ በመስጠት የኢራን ወሳኝ የሆነውን የውሃ መስመር ዘግታለች።

    አሜሪካ በበኩሏ የኢራን ወደቦችን በመዝጋቷ ምክንያት ለዓለም አቀፍ የኃይል ዋጋ መጨመር ምክንያት ሆኗል።

    ወደ 40 የሚጠጉ አገሮች ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ሲል የኪር ስታርመር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

    መሪዎቹ "በቀጣናው ውስጥ ያለውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመደገፍ እና የመርከብ መንገዶች ለረዥም ጊዜ በኩል በድጋሚ እንዲከፈቱ እና እንዲጠበቁ በማድረግ ላይ ያተኩራሉ" ሲል አክሏል።

    ስታርመር ወሽመጡ “ያለ ቅድመ ሁኔታ እና በፍጥነት እንደገና መከፈቱ ዓለም አቀፍ ኃላፊነት ነው" በማለት ለተሰብሳቢዎቹ እንደሚገልጹ ዳውኒንግ ስትሪት አስታውቋል።

    በተጨማሪም "የመርከብ ነፃነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮ" ሊሰማራ እንደሚችል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

  8. ትራምፕ ኢራን ያበለጸገችውን ዩራኒየም ለማስረከብ ተስማምታለች አሉ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ያበለጸገችውን ዩራኒየም ለማስረከብ መስማማቷን ተናገሩ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል እየተካሄደ በነበረው የሰላም ድርድር ላይ ካላግባቡ ነጥቦች መካከል ቴህራን ያበለጸገችው ዩራኒየም አንዱ ነበር።

    ፕሬዚዳንቱ በሳምንቱ መጨረሻ በዋሺንግተን እና በቴህራን መካከል ንግግር ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረው፤ ከስምምነት ልንደርስ “በጣም ተቃርበናል” ብለዋል።

    ትራምፕ በላስቬጋስ በአሜሪካ ምጣኔ ኃብት ላይ ባተኮረ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ጦርነቱ “ያለምንም እንከን” እየሄደ እንደሆነ ተናግረው በቅርቡ ማብቃት አለበት ብለዋል።

    ቀደም ሲል ዋይት ሐውስ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይኖራት መስማማቷን ገልጾ ነበር።

    አክሎም ባለፈው ዓመት እስራኤል እና አሜሪካ የፈጸሙትን ድብደባ ተከትሎ ከመሬት በታች እንደተቀበረ የሚታመነውን የበለጸገ ዩራኒየም “የኒውክሌር አቧራ” አራግፈው ቆፍረው እንደሚያወጡ ተናግረው ነበር።

    ትራምፕ በቀጣይ ዙር በሚደረገው የሁለቱ አገራት ድርድር እርግጠኛ ሆነው ታይተዋል።

    ነገር ግን ከአምስት ቀናት በኋላ የሚያበቃው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ስለመራዘሙ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

  9. በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ምን ምን ነጥቦችን ይዟል?

    የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ድንበር አቅራቢያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእስራኤልና የሊባኖስ መሪዎች በመካከላቸው የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደስታ ተቀብለውታል።

    ኔታንያሁም “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ለማድረግ እድል” እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

    የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአስር ቀናት የሚቆይ ሲሆን የሚደረጉ ድርድሮች የለውጥ ምልክቶችን ካሳዩ "በጋራ ስምምነት" ሊራዘም ይችላል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ዝርዝር መረጃ መሰረት ስምምነቱ የሚከተሉትን ነጥቦች ይዟል።

    • እስራኤል "በማንኛውም ጊዜ፣ በታቀዱ፣ በተጨባጭ ወይም በቀጣይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ የመውሰድ” መብት ይኖራታል።
    • ሊባኖስ፣ ሄዝቦላህ እና ሌሎች "ከመንግሥት ውጭ የሆኑ የታጠቁ ቡድኖች" በእስራኤል ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ለመከላከል "ትርጉም ያላቸውን እርምጃዎች" መውሰድ አለባት።
    • በስምምነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሊባኖስ የጸጥታ ኃይሎች ለሊባኖስ ደህንነት ብቸኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ።
    • እስራኤል እና ሊባኖስ "ቀሪ ጉዳዮችን ሁሉ ለመፍታት" አሜሪካ ተጨማሪ ቀጥተኛ ውይይቶችን እንድታመቻች ጠይቀዋል።

    መግለጫው አክሎም የተኩስ አቁም ስምምነቱ እስራኤል በሁለቱ ወገኖች መካከል "በቀና ልቦና ዘላቂ የጸጥታ እና የሰላም ስምምነት ለመድረስ የሚደረግ ድርድር" ለማስቻል “መልካም ፈቃደኝነቷን” ያሳየችበት እንደሆነ ገልጿል።

    ሄዝቦላህ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ያሳየ ቢሆንም፣ በሊባኖስ ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን “ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ” እና "የእስራኤል ኃይሎች የመንቀሳቀስ ነፃነት እንደሌላቸው" የሚሉ ሃሳቦች መካተት እንዳለበት ተናግሯል።

  10. በእስራኤል አየር ድብደባ ተፈናቅለው የነበሩ ሊባኖሳውያን ወደ ቤታቸው መመለስ ጀመሩ

    ወደ ቤታቸው ለመመለስ እየተሰናዱ ያሉ ሊባኖሳውያን እቃቸውን በመኪና ላይ ሲጭኑ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ወደ ቤታቸው ለመመለስ እየተሰናዱ ያሉ ሊባኖሳውያን እቃቸውን በመኪና ላይ ሲጭኑ ታይተዋል

    በሊባኖስ ላለፉት ስድስት ሳምንታት እስራኤል ስታካሄድ የነበረው የአየር ድብደባ በተኩስ አቁም እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ቀያቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ሊባኖሳውያን መመለስ ጀመረዋል።

    አንዳንድ ነዋሪዎች እቃቸውን በመኪና ጭነው ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ሲያመሩ ታይተዋል።

    የእስራኤል እና የሊባኖስ መሪዎች የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን አወድሰውዋል።

    ኔታንያሁ “የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ታሪካዊ ዕድል” መኖሩን ተናግረዋል።

    የተኩስ አቁሙ ለአስር ቀን የሚቆይ ሲሆን የሚደረጉ ድርድሮች ለውጥ ካሳዩ “በጋራ ስምምነት ሊራዘም እንደሚችል” ተገልጿል።

    አሻንጉሊት እና ቀሪ ቁሳቁሶቻቸውን የያዙ ሁለት ሴቶች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እየተመለሱ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አምስት ሰዎች በአንዲት አነስተኛ ሞተር ላይ ተጭነው ወደ ሲዶን በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, አምስት ሰዎች በአንዲት አነስተኛ ሞተር ላይ ተጭነው ወደ ሲዶን በሚወስደው ዋና መንገድ ላይ ሲጓዙ ይታያሉ
  11. የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ የእስራኤልን እና ሊባኖስን የተኩስ አቁም ስምምነት አወደሱ

    የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነትን በደስታ እንደሚቀበሉ እና አሜሪካን ስላደረገችው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

    "ይህ ለግጭቱ የረዥም ጊዜ መፍትሄ ለማግኘት ለሚደረገው ድርድር መንገድ እንደሚጠርግ እና በቀጣናው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት ለሚደረጉ ቀጣይ ጥረቶች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ጉቴሬዝ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

    ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እና "ሁልጊዜም ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ" አሳስበዋል።

  12. ትራምፕ የኢራን ጦርነት “በጣም በቅርቡ ማብቃት አለበት” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኔቫዳ ለተሰበሰቡ ሰዎች የኢራን ጦርነት “በቅርቡ ማብቃት አለበት” ሲሉ ተናገሩ።

    ትራምፕ “በኢራን የሚካሄደው ጦርነት ያለምንም እንከን እየተካሄደ ነው” ካሉ በኋላ “በቅርቡ መጠናቀቅ አለበት” ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ባያብራሩም የአሜሪካ ጦር ሮኬቶችን መትቶ ሲጥል ግን ብቃት እንዳለው ተናግረዋል።

    ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በፓኪስታን ኢዝላማባድ የተካሄደው የሰላም ድርድር ያለምንም ውጤት ተበትኗል።

    ዋሺንግተን በሁለቱ አገራት መካከል ቀጣይ ድርድር ለማድረግ ንግግሮች መኖራቸውን ቢገልጽም መቼ እና የት ይካሄዳል የሚለውን ግን ይፋ ማድረግ አልፈለገም።

  13. በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀመረ

    የእስራኤል ጦር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የአስር ቀን የተኩስ አቁም ከእኩለ ለሊ ት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአስር ቀን ብቻ የተደረሰ ቢሆንም ሊራዘም እንደሚችል ጠቁመዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሊባኖስ ጋር “ታሪካዊ የሰላም ስምምነት” ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን እንደሚያከብር ጠቅሶ በኋላ ላይ “በሁሉም የሊባኖስ ግዛቶች የተሟላ ጥቃቶችን ማቆም” እንዲያካትት እና “የእስራኤል ጦር በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ” ጠይቋል።

    ኔታንያሁ ጦራቸው በደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ 10 ኪሜ ያሀል ዘልቆ በመግባት “የደህንነት ቀጣና” ውስጥ እንደሚቆዩ የተናገሩ ሲሆን ይህ ግን ከሄዝቦላህ ፍላጎት ውጭ ነው።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በስምምነቱ መሠረት የሊባኖስ መንግሥት ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም ለማድረግ “ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ” ይኖርበታል ብሏል።

    አክሎም የሊባኖስ የጸጥታ ኃይል ለሊባኖስ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ መከላከያ “ሙሉ ኃላፊነት” እንዳለበት አስታውቋል።

    የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ የእስራኤል መከላከያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ከ380 በላይ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጿል።

    ዒላማ ከሆኑት መካከል የሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ዋና መስሪያ ቤቱን እና የሄዝቦላህ አባላት ይገኙበታል።

    ትራምፕ የሊባኖስ እና የእስራኤል መሪዎች በዋሺንግተን ተገናኝተው በቀጣይ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ መጋበዛቸውን ተናግረዋል። እስካሁን ግን ከየትኛውም ወገን ስለግብዣው ማረጋገጫ አልተገኘም።

    ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ዛሬ ለሊባኖስ “ታሪካዊ” ቀን ነው ሲሉ ጽፈዋል።

    “መልካም ነገሮች እየሆኑ ነው” ያሉት ትራምፕ በሌላ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው “ሄዝቦላህ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ተገቢውን እና የተረጋጋ ባህሪውን እንደሚያሳይ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

    በቤይሩት ሰማይላይ የርችት ተኩስ የፈጠረው ብርሃን ታይቷል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ ለቤይሩት ነዋሪዎች ርችት ተኩሰዋል
  14. ትራምፕ በሰዓታት ውስጥ እስራኤል እና ሊባኖስ የ10 ቀን የተኩስ አቁም እንደሚጀምሩ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ዶናልድ ትራምፕ የሊባኖሱን ፕሬዚዳንት እና የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ማነጋገራቸውን እና የተኩስ አቁም በጥቂት ሰዓት ውስጥ እንደሚጀመር ተናገሩ።

    ትራምፕ በመግለጫቸው ላይ በኢራን የሚደገፈውን እና ከእስራኤል ጋር ውጊያ እያካሄደ ያለውን ሄዝቦላህን አልጠቀሱም።

    “ከሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢቢ ኔታንያሁ ጋር ጥሩ ውይይት አድርጌያለሁ” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    “እነዚህ ሁለቱ መሪዎች በአገራቸው መካከል ሰላም ማስፈን እንዲቻል የ10 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ከ7:00 (ሌሊት) ጀምሮ ይጀምራሉ።”

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ከእስራኤል ጋር የተደረሰውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም መቀበላቸውን አስታውቀዋል።

    ማክሰኞ ዕለት ከ34 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሁለቱ አገራት ልዑካን በዋሺንግተን መገናኘታቸውን ያስታወሱት ትራምፕ ኃላፊዎቻቸውን “ዘላቂ ሰላም” ማምጣት እንዲቻል ከእስራኤል እና ሊባኖስ ጋር እንዲሰሩ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

    "ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ፣ የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ራዚን ኬን፣ ከእስራኤል እና ሊባኖስ ጋር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንዲሰሩ መመሪያ ሰጥቻለሁ።”

    “በመላው ዓለም ዘጠኝ ጦርነቶችን መፍታት በመቻሌ ክብር ይሰማኛል እና ይህ ደግሞ 10ኛው ይሆናል” ሲሉ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን እና የሊባኖስን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን በዋይት ሐውስ ለተጨማሪ ንግግር መጋበዛቸውን አስታውቀዋል።

    “ሁለቱም ወገኖች ሰላም ይፈልጋሉ እና በፍጥነት ይሆናል" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ግብዣውን ስለመቀበላቸው የታወቀ ነገር የለም።

  15. የአሜሪካ እና የሊባኖስ ፕሬዚዳንቶች በስልክ ተወያዩ -ቤይሩት

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን እና ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ዛሬ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ መወያየታቸውን ጽህፈት ቤታቸው ገለጸ።

    ጽህፈት ቤቱ በኤክስ ገጹ ላይ ኦውን ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እንዲሁም “ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ” ስለሚያደርጉት ጥረት አመስግነዋል ብሏል።

    አውን በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል “በተቻለ ፍጥነት በቀረበ ጊዜ” የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ በድጋሚ ጠይቀዋል።

    ትራምፕ ለፕሬዚዳንት ኦውን እና ሊባኖስ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸውን ጽህፈት ቤቱ አክሎ ገልጿል።

    ዛሬ የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይወያያሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ይህ ግን መሰረዙን ቢቢሲ ከሊባኖስ ባለሥልጣናት ምንጮቹ አረጋግጧል።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ ቀጥላለች።

    አንድ ከፍተኛ የሊባኖስ ባለሥልጣን የእስራኤል የአየር ድብደባ ደቡባዊ ሊባኖስን ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል የሚያገናኝ ቁልፍ ድልድይን ማውደሙን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

  16. የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ኢራን ላይ 'ከዚህም በላይ የከፉ' ጥቃቶች እንደሚፈጸም ዛቱ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ ኢራን ከአሜሪካ ጋር የጀመረችው ድርድር ላይ ከስምምነት የማትደርስ ከሆነ ‘ከዚህም በላይ የከፋ’ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ።

    “ኢራን ታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። ይህ ወደ ወደፊቱ ድልድይ እና ወደ መገለል እና ውድመት ምርጫ የሚያደርጉበት ቅጽበት ነው።”

    ኢራን መነጠል እና ውድመትን የምትመርጥ ከሆነ እስራኤል እስካሁን ያልደበደበቻቸውን ዒላማዎች “በጣም በፍጥነት በመለየት” “እስካሁን ከተፈጸሙት የከፋ” ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።

    “ምርጫው በእጃቸው ነው እና ውጤቱም የራሳቸው ነው” ሲሉ አስተያያታቸውን አጠናቅቀዋል።

    ቀደም ሲል የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ኢራን ከስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ጦራቸው ጥቃቱን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን በመናገር “በብልሃት እንድትመርጥ” አስጠንቅቀው ነበር።

  17. የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እንደማይነጋገሩ ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ

    የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር እና የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት መካከል ዛሬ ምንም ዓይነት ንግግር እንደማይኖር የሊባኖስ ባለሥልጣናት ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዩ ዛሬ መነጋገር እንደማይችሉ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

    የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሊደረግ የነበረው ንግግር መሰረዙን የሚገልጽ መግለጫ ማውጣት አለመፈለጉን ቢቢሲ ከምንጮቸ ሰምቷል።

    ፕሬዚዳንት አውን ከሄዝቦላህ እና ከአብዛኛው የሊባኖስ ሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት እስራኤል ጥቃት መቀጠሉን ተከትሎ ደፍርሷል።

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ንግግር እንዲደረግ የሚፈልጉ ሲሆን የተኩስ አቁም ግን ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

    እስራኤል በበኩሏ የወታደራዊ ዘመቻዋን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።

    ዶናልድ ትራምፕ የሊባኖሱ ፕሬዚዳነት ጆሴፍ ኦውን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዛሬ እንደሚነጋገሩ ገልጸው ነበር’

    ይህንን የትራምፕ ሃሳብ የእስራል ሚኒስትርም አረጋግጠውት ነበር።

  18. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት የሚያወጡ 'አምባገነኖች'ን ተቹ

    ሊቀ ጳጳስ ሊዮ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዛሬ በካሜሩን ባደረጉት ንግግር በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለጦርነት የሚያወጡ መሪዎችን ባልተለመደ ሁኔታ በግልጽ ተችተዋል።

    ይህ የሆነው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያላይ እንደገና ከተቿቸው በኋላ ነው።

    ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በካሜሮን ባሜንዳ ባደረጉት ንግግር፣ “ለራሳቸው ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ ሃይማኖትንና የእግዚአብሔርን ስም የሚጠቀሙ” ሰዎችን አውግዘዋል።

    ጳጳሱ ይህ ዓመፅን ለማጽደቅ እምነትን መጠቀም መሆኑን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

    ለአስር ዓመታት ያህል በዘለቀው ግጭት ለተጎዳው የአካበቢው ማኅበረሰብ ባደረጉት ንግግር “ሰላምን ለማወጅ” ብመጣም ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች “ለእኔም ሆነ ለመላው ዓለም ሰላምን እያወጁ” እንደሆነ ተረድቻለሁ ብለዋል።

    ሊዮ ጦርነት የሰው ልጅ እንደሚቀጥፍ ሲያስረዱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ አለመመጣጠን መኖሩን በመግለጽ ተችተዋል።

    “የጦርነት ጌቶች ለማውደም የሚፈጀው ቅጽበት እንደሆነ የማያውቁ ለመምሰል ይሞክራሉ፤ ነገር ግን መልሶ ለመገንባት የሕይወት ዘመን በቂ አይደለም” ብለዋል።

    አክለውም “በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለግድያና ለውድመት ይውላል፤ ነገር ግን ለፈውስ፣ ለትምህርትና ለማደስ የሚያስፈልጉ ሀብቶች የትም አይገኙም” ብለዋል።

    ሊቀ ጳጳሱ የጦርነት ጌቶች ሲሉ የጠሯቸውን “ወሳኝ የሆነ የተግባር ለውጥ” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው ወደ “ሰብአዊ ወንድማማችነት የበለፀገ እና ዘላቂ መንገድ” እንዲሸጋገሩ አሳስበዋል።

    “ዓለም በጥቂት አምባገነኖች እየተናጠች” እያለ “በብዙ አቃፊ እና ደጋፊ ወንድሞችና እህቶች ተይዛ ትገኛለች” በማለት ተስፋን ፈንጥቀዋል።

  19. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን የማትስማማ ከሆነ ዳግም ጥቃት እንደሚጀመር አስጠነቀቁ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን ከስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የማጥቃት ዘመቻ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ “በብልሃት እንድትመርጥ” አስጠነቀቁ።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት እና የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን እንዲሁም የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

    ሄግሴት ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር “በብልሃት እንድትመርጥ” አስጠንቅቀዋል። ሚኒስትሩ ጦሩ ማንኛውንም ትዕዛዝ መሣሪያውን “አቀባብሎ” እና “ለመሄድ ዝግጁ ሆኖ" እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

    ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት እንደምታረጋግጥ የገለጹት ሄግሴት ይህም “በጥሩ መንገድ” ወይም “በከባድ ሁኔታ” እንደሚከናወን ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣሉትን እገዳ የአሜሪካ ጦር “ከ10 በመቶ ባነሰ አቅሙ” ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

    አክለውም ኢራን የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ለመፈጸም መዛቷን ጠቅሰው ይህ ቁጥጥር ሳይሆን “የባህር ላይ ውንብድና” ነው ብለዋል።

    ጄነራል ኬን ሚኒስትሩ ያሉትን አጠናክረው የአሜሪካ ጦር የማጥቃት ዘመቻውን ለመቀጠል “በቅጽበቶች ትዕዛዝ” ውስጥ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ በጣለችው የእንቅስቃሴ ገደብ እስካሁን ድረስ 13 መርከቦች እንዲመለሱ ሲነገራቸው በመመለስ “ብልህ ውሳኔ” መወሰናቸውን ተናግረዋል።

    አሜሪካ ተጨማሪ የባሕር ኃይል መርከቦችን ማሰማራት እንደማያስፈልጋት ጠቅሰዋል።

    አድሚራል ኩፐር በበኩላቸው አሜሪካ የተኩስ አቁም ጊዜውን ስልቶቿን እና ብልሃቶቿን ለማስተካከል እየተጠቀመችበት መሆኑን ተናግረው ከእስራኤል የተሻለ ወዳጅ በቀጠናው ላይ የለም ብለዋል።

  20. በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ቀጥሎ ምን ሊከሰት ይችላል?

    ባለፈው ሳምንት ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም መስማማታቸውን ተከትሎ የቴህራን ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልጸዋል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ሳምንት ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም መስማማታቸውን ተከትሎ የቴህራን ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልጸዋል

    የፓኪስታን ልዑካን ቴህራን ሲገቡ አሜሪካ ከኢራን ጋር ለሁለተኛ ዙር ድርድር ለመቀመጥ እየተነጋገረች መሆኑ ተሰምቷል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለ40 ቀናት ከተካሄደ በኋላ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሷል።

    ነገር ግን ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በፓኪስታን ለሃያ ሰዓታት ያህል የተደረገው ውይይት ያለ ምንም ስምምነት ተቋጭቷል።

    መጀመርያው ዙር ንግግር ያለምንም ስምምነት መጠናቀቁን እንዴት ልናየው እንችላለን? ቀጣይ ዙር ንግግርስ ፍሬ ያፈራ ይሆን? አሜሪካ እና ኢራን የተጠና እና የተመጠነ ግጭት ውስጥ ይቆያሉ ወይስ መከላከል ወደማይቻል ሰፊ ጦርነት ያመራሉ?

    ቀጣዮቹ አራትን ቢሆኖች በመጪው ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።