ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለቀሪዎቹ የተኩስ አቁሙ ቀናት መከፈቱን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የሆርሙዝ ወሽመጥ “ለቀረው የተኩስ አቁም ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ክፍት” እንደሚሆን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አስታወቁ።
አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ሊባኖስ ውስጥ በተደረሰው ተኩስ አቁም መሰረት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የሁሉም የንግድ መርከቦች ጉዞ ለቀሪው የተኩስ አቁሙ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን ታውጇል” ብለዋል።
ለ40 ቀናት የተዋጉት አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን አሸማጋይነት የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም መፈጸማቸው ይታወሳል። ይህ ተኩስ አቁም በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ይጠናቀቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የመርከቦቹ ጉዞ የሚካሄደው “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የወደብ እና ማሪታይም ድርጅት አስቀድሞ ባሳወቀው የተቀናጀ መስመር” በኩል እንደሆነም ገልጸዋል።
ለኢራን ውሳኔ ምላሽ የሰጡት አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “አመሰግናለሁ” ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።
ትራምፕ፤ “ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ክፍት መሆኑን እና ለሙሉ ጉዞ ዝግጁ መሆኑን አሁን አስታውቃለች። አመሰግናለሁ!" ብለዋል።
የካቲት ላይ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን ብዙ ከዓለም ነዳጅ ማጓጓዣ መስመሮች መካከል በርካታ መርከቦችን በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግታ ቆይታለች።
ለዚህ እገዳ ምላሽ የሰጠችው አሜሪካ ደግሞ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በወሽመጡ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች ጉዞ እንዳይደረግ ከልክላለች።






















