የአሜሪካ ልዑካን ለድርድር ወደ ፓኪስታን ተመለሱ፤ ትራምፕ የኢራንን መሠረተ ልማት እንደሚያወድሙ ዝተዋል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ልዑክ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ወደ ፓኪስታን ማቅናቱን ገለጹ። በአሁኑ ድርድር አሜሪካ የምታቀርበውን ስምምነት ኢራን የማትቀበል ከሆነ በአገሪቱ የሚገኙ “የኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮችን እንደሚመቱ” ዝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ልዑካቸው ለድርድር ወደ ፓኪስታን መጓዙን ገልጸው ንግግሩ ካልተሳካ የኢራንን ኃይል ማመንጫዎች እንደሚያወድሙ ዛቱ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ልዑክ ከኢራን ጋር ለሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ወደ ፓኪስታን ማቅናቱን ገለጹ። በአሁኑ ድርድር አሜሪካ የምታቀርበውን ስምምነት ኢራን የማትቀበል ከሆነ በአገሪቱ የሚገኙ “የኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮችን እንደሚመቱ” ዝተዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኀበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “የእኔ ተወካዮች ወደ ኢስላማባድ፣ ፓኪስታን እየሄዱ ነው። ነገ ማታ ለድርድር እዚያ ይሆናሉ” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን አሸማጋይነት ባለፈው ሳምንት ድርድር አድርገው የነበረ ቢሆንም ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። በመጀመሪያው ዙር ድርድር የአሜሪካ ልዑክ የተመራው በምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ ሲሆን የኢራን ተደራዳሪ ቡድን ደግሞ በአፈ ጉባኤው ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ተመርቷል።

    ትራምፕ በዛሬው ጽሑፋቸው፤ “እጅግ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ስምምነት አቅርበናል፤ እንደሚቀበሉት ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

    አክለውም ግን “የማይቀበሉት ከሆነ አሜሪካ ኢራን ውስጥ ያሉትን እያንዳንዱን የኃይል ማመንጫ እና ድልድይ ትመታለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ንግግሮቹ የማይሳኩ ከሆነ “ከእንግዲህ ጥሩ ሰው አልሆንም” ያሉት ትራምፕ፤ የአገሪቱ ድልድዮች እና የኃይል ማመንጫዎች “በፍጥነት ይወድቃሉ፣ በቀላሉ ይወድማሉ” ሲሉም ጽፈዋል።

    ሁለተኛ ዙር ድርድር ሊደረግ ስለመሆኑ እስካሁን ከኢራን በኩል አልተሰማም። የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ለቀጣይ ዙር ድርድር የተቆረጠ ቀን አለመቀመጡን መናገራቸውን ሮይተርስ ዛሬ ዘግቦ ነበር።

    ሌላኛው የዜና ወኪል ኤፒ ያወጣው ዘገባ ደግሞ ድርድሩ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቅበት ኢስላማባድ ከተማ የደኅንነት እና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረገ መሆኑን ያመለክታል።

  2. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን መርከቦች ላይ በመተኮስ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት ፈጽማለች አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን “በትናንትናው ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ጥይት ለመተኮስ ከወሰነች” በኋላ “የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች” ሲሉ ከሰሱ።

    “ይህ ጥሩ ነገር አልነበረም፤ ነበር ወይ?” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የጻፉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ የተተኮሰው ጥይት “ያነጣጠረው የፈረንሳይ መርከብ እና ከዩናይትድ ኪንግደም በተነሳ ጭነት” ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

    አሜሪካ “ቀድሞውንም” ሆርሙዝን “መዝጋቷን” በመጥቀስም ኢራን በወሽመጡ የሚደረግ ጉዞን ለማገድ ያሳለፈችውን ውሳኔ “እንግዳ” ሲሉ ጠርተውታል።

    “ሳያውቁት እኛን እየረዱን ነው፤ መተላለፊያው በመዘጋቱ የሚያጡት እነርሱ ናቸው፤ በቀን 500 ሚሊዮን ዶላር! አሜሪካ ምንም ነገር አታጣም” በማለት ጽፈዋል።

    ኢራን ጦርነት ከተጀመረባት በኋላ የዘጋችውን ሆርሙዝ አርብ ዕለት ከፍታው ነበር። ይሁን እንጂ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚጓዙ መርከቦች ላይ የጣለችው እገዳ እንደሚቀጥል ከገለጸች በኋላ በትናንትናው ዕለት መልሳ ዘግታዋለች።

    ከዚህ ውሳኔ በኋላ ለማለፍ የሞከሩ መርከቦች ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልጸዋል። በዛሬው ዕለት በወሽመጡ በኩል መርከቦች አለማለፋቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

    ኢራንም በአንጻሩ አሜሪካ ወደ ወደቦቹ የሚደረጉ ጉዞዎችን በማገድ የተኩስ አቁም ጥሰት ፈጽማለች ስትል ከስሳለች።

  3. ኢራን የሚሳዔል እና ድሮን ክምችቷን ከጦርነቱ በፊት ከነበረው በበለጠ ፍጥነት እየሞላች መሆኑን አስታወቀች

    የኢራን ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የኤሮስፔስ ኃይል አዛዥ የአገሪቱ የሚሳዔል እና ድሮን ክምችት በፍጥነት መልሶ እየተገነባ መሆኑን እንዲሁም ወደ ሁለተኛ ሳምንቱ እየተጠጋ ባለው ተኩስ አቁም ጊዜ ውስጥ “የኦፕሬሽናል ዝግጁነትን መጨመሩን” ተናገሩ።

    አብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ የሚሳኤል እና የድሮን ክምችቱ እየተሞላ ያለበት ፍጥነት ከጦርነቱ በፊት ከነበረውም በላይ እንደሆነ አዛዡ ብርጋዴር ጄነራል ማጂድ ሙሳቪ ተናግረዋል።

    አዛዡ፤ "በተኩስ አቁም ወቅት የሚሳኤል እና የድሮን ማስወንጨፊያዎችን እያሳደግን እና እየሞላን ያለበት ፍጥነት ከጦርነቱ በፊት ከነበረውም የላቀ ነው” ማለታቸው ተዘግቧል።

    “ጠላት ለራሱ እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን መፍጠር እንደማይችል እና ተተኳሾችን ከሌላው የዓለም ክፍል በጠብታ መልክ ለማምጣት ስለመገደዱ መረጃ አለን" ብለዋል።

    ይህ የኤሮስፔስ ኃይል አዛዡ መግለጫ የተላለፈው ስፍራው የት እንደሆነ ባልተገለጸ የመሬት ስር የሚሳዔል ተቋም ውስጥ ሆነው መሣሪያዎች እየተመለከተ ከሚያሳይ ቪዲዮ ጋር መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የቪዲዮ ምስሉ ላይ መሬት ስር ባሉ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ድሮኖች፣ ሚሳዔሎች እና ማስወንጨፊያዎች ታይተዋል።

  4. ፓኪስታን በቀጣዮቹ ቀናት ሊካሄድ ለሚችል ድርድር ዝግጅት እያደረገች ነው

    ፓኪስታን ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያው ዙር ሲካሄድ ለሁለት ቀናተ ሥራ እና ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ አድርጋ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ፓኪስታን ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያው ዙር ሲካሄድ ለሁለት ቀናተ ሥራ እና ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ አድርጋ ነበር

    የፓኪስታን ባለሥልጣናት አሜሪካ እና ኢራን ሊያደርጉት ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር የተኩስ አቁም ንግግር ከመጀመሩ አስቀድሞ የዋና ከተማዋ ኢስላማባድን የደኅንነት ቁጥጥር ማጥበቅ መጀመራቸውን የዜና ወኪሉ ኤፒ ዘገበ።

    መንገዶች ላይ በተቋቋሙ የፍተሻ ኬላዎች ወታደሮች የተሰማሩ ሲሆን የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችም ተዘግተዋል።

    ዋና ዋና ሆቴሎች ለደንበኞች የያዙትን ቦታ እንዲሰርዙ እና ክፍሎቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ መስጠታቸውን ዘገባው ያመለክታል።

    እንደ ኤፒ ዘገባ፤ ነዋሪዎች በመጀመሪያው ዙር እንደታየው አይነት የመንገድ መዘጋት እንዳያጋጥማቸው በመስጋት ከቤታቸው ባለመውጣታቸው የኢስላማባድ ጎዳናዎች ጭር ብለዋል።

    እነዚህ እንቅስቃሴዎች ቢታዩም እስካሁን ድረስ ድርድሩ መቼ እንደሚካሄድ በይፋ አልተገለጸም። የፓኪስታን ባለሥልጣናት ግን በሚቀጥሉት ቀናት ንግግር ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን እንደተናገሩ ዘገባው ጠቅሷል።

    የማደራደር ጥረቱ ውስጥ የተሳተፉ አንድ የቀጣናው ባለሥልጣን ለኤፒ እንደተናገሩት፤ አሸማጋዮቹ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው። የአሜሪካ የደኅንነት ቡድኖችም ወደ ስፍራው መድረሳቸውን ምንጩ ተናግረዋል ተብሏል።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ለቀጣይ ዙር ድርድር የተቆረጠ ቀን አለመቀመጡን መናገራቸውን ሮይተርዝ ዛሬ ዘግቦ ነበር።

  5. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ሊያልፉ የነበሩ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መመለሷ ተዘገበ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዙ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሆርሙዝ በኩል የሚደረግ ጉዞ ላይ ትናንት በድጋሚ የጣለችው እገዳ ቀጥሎ፤ የአገሪቱ “ጦር ኃይሎች በዛሬው ዕለት ሁለት ተጨማሪ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች” በወሽመጡ እንዳያልፉ መመለሳቸውን ታስኒም የዜና ወኪል ዘገበ።

    ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው የዜና ወኪል ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ሁለቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች “የቦትስዋና እና አንጎላ ባንዲራን አድርገው እየቀዘፉ” ነበር።

    በሆርሙዝ በኩል ለማለፍ ፈልገው የነበረ ቢሆንም “የኢራን ጦር ኃይሎች በወሰዱት ጊዜውን የጠበቀ እርምጃ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ እና እንዲያፈገፍጉ” መደረጉንም ገልጿል።

    ኢራን ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ ዘግታው የነበረውን ሆርሙዝ አርብ ዕለት ከፍታ የነበረ ቢሆንም አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እገዳ መጣሏን እንደምትቀጥል መግለጿን ተከትሎ ወሽመጡን በድጋሚ ዘግታለች።

    በትናንናው ዕለት በድጋሚ እገዳው ከተጣለ በኋላ ለማለፍ የሞከሩ መርከቦች ከኢራን ኃይሎች ተኩስ እንደተከፈተባቸው ገልጸዋል።

    የመርከቦች ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ የሆነው ‘ማሪን ትራፊክ’ መረጃ እንደሚያመለክተው አንድም መርከብ በወሽመጡ በኩል አላለፈም።

    በርካታ መርከቦች በኦማን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የባሕር ዳርቻዎች መልህቃቸው ጥለው እንደሚገኙም መረጃው ያሳያል።

    ትናንት በወሳኙ መተላለፊያ በኩል የተወሰነ ጉዞ ተስተውሎ የነበረ ቢሆንም ኢራን ወሽመጡን መዝጋቷን ካስታወቀች በኋላ በከፍተኛ መጠን ቀንሷል።

  6. በአሁኑ ሰዓት ተግባራዊ እየሆኑ ያሉት የተኩስ አቁሞች የትኛዎቹ ናቸው?

    የሄዝቦላህን ባንዲራ የያዙ ሰዎች መንገድ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የካቲት ላይ ከጀመረው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተግባራዊ እየሆኑ ነው። ስለ ስምምነቶቹ መታወቅ ያለባቸው ነጥቦችን እነሆ፦

    አሜሪካ እና ኢራን

    • ለ40 ቀናት ሲዋጉ የቆዩት የሁለቱ አገራት ተኩስ አቁም የተጀመረው መጋቢት 30/2018 ዓ.ም. ነው
    • ተኩስ አቁሙ ለሁለት ሳምንት ወይም 14 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በመጪው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ 14 ይጠናቀቃል

    ኢራን እና አሜሪካን እዚህ ላይ ያደረሰውን ንግግር ያሸማገለችው ፓኪስታን፤ ተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጻለች። ኢራን ይህንን ሀሳብ የደገፈችው ቢሆንም አሜሪካ እና እስራኤል ተቃርነውታል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ

    • ለኢራን ድጋፉን ለመግለጽ ሮኬቶችን ባስወነጨፈው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና ዘመቻ በከፈተችው እስራኤል መካከል ተኩስ አቁም የተደረሰው በዚህ ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 8 ነው
    • ለ10 ቀናት የሚቆየው ይህ ተኩስ አቁም የዛሬ ሳምንት እሁድ ይጠናቀቃል

    የሊባኖስ እና እስራኤል ባለሥልጣናት ካደረጉት ንግግር በኋላ የተደረሰው ይህ ስምምነት ይፋ የተደረገው በአሜሪካ ነው።

    የእስራኤል እና ሊባኖስ አመራሮች ተኩስ አቁሙን እንደሚቀበሉት ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ለስምምነቱ እንዲገዛ አሳስበዋል።

    ሄዝቦላህ በበኩሉ ተኩስ አቁሙ ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ቢጠቁምም፤ ስምምነቱ በመላው ሊባኖስ የሚተገበር "ሁሉን አቀፍ የሆነ የጥቃት ማቆም" እርምጃን ማካተት እንዳለበት ገልጿል።

    "የእስራኤል ኃይሎች [ሊባኖስ ውስጥ] ምንም አይነት የመንቀሳቀስ ነፃነት ሊሰጣቸው እንደማይገባም" አሳስቧል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ተኩስ አቁሙ ቢኖርም የአገሪቱ ወታደሮች የሊባኖስ ግዛት ውስጥ 10 ኪሎ ሜትር ገብተው በያዙት መሬት ላይ ሰፍረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

  7. ኢራን የኒውክሌር መብት እንደማይገፈፍ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, IRANIAN PRESIDENCY / HANDOUT via Getty Images

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን የኒውክሌር መብት ለመግፈፍ የሚያስችል ምንም አይነት ምክንያት እንደሌላቸው መናገራቸውን ኢስና የተሰኘው የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    ፔዜሽኪያን “ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር መብቷን መጠቀም የለባትም ይላል፤ ነገር ግን በምን ወንጀል የተነሳ እንደሆነ መልስ አይሰጥም” ብለዋል። “አንድ አገር ያለውን መብት የሚግፍፈው እርሱ ማነው?” ሲሉም ጠይቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ “እኛ ጦርነት ጎሳሚዎች እንደሆንን ተደርጎ እንዳይወሰድ ሁኔታዎችን ማስተዳደር አለብን፤ እኛ ራሳችንን እየተከላከለን ነው” ብለዋል።

    “ጦርነቱን በክብር ለመቋጨት እየሞከርን ነው” ማለታቸውንም የኢራን የተማሪዎች ዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህንን አስተያየት የሰጡ በቴህራን እና ዋሽንግተን መካከል በሚደረገው ድርድር ውስጥ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዋነኛ የቅራኔ ምንጭ ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ነው።

    ባለፈው ሳምንት ፓኪስታን ውስጥ በተደረገው ንግግር ሁለቱን አካላት ያላስማማው ይኸው ጉዳይ እንደሆነ ተገልጾ ነበር።

    ምንም እንኳ ኢራን ዩራኒየም የምታበለጽገው ለሰላማዊ ዓላማ እንደሆነ ብትናገርም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቴህራን የኒውክሌር መሣሪያ እንድትታጠቅ እንደማይፈቅዱ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

    ኢራን በበኩሏ አሜሪካ በድርድሩ ሁሉንም ማግኘት አለብኝ የሚል አቋም እንደያዘች በመግለጽ ወቅሳለች።

  8. በሊባኖስ የተኩስ አቁም ቢደረግም የሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ ክስተቶች እየተመዘገቡ ነው

    ታንክ ላይ የቆሙ የእስራኤል ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን የገቡትም ሆነ እስራኤል እና ሊባኖስ የደረሱበት የተኩስ አቁም ስምምነት እየተከበረ ይመስለል። ሊባኖስ ውስጥ ግን ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ክስተቶች ተፈጥረዋል።

    ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ሁለት ወታደሮች መሞታቸውን የእስእራኤል መከለከያ ሠራዊት ገልጿል።

    የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው አንዱ ወታደር ሕይወቱ ያለፈው ሕንጻዎች በሚያጸዱበት ሰዓት በደረሰ ፍንዳታ ነው። በዚህ ክስተት ሌሎች ሦስት ሰዎች ቆስለዋል።

    ሌላኛው የእስራኤል ወታደር በተገደለበት ክስተት ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ወታደሮቹ የነበሩበት መሣሪያ የታጠቀ ተሽከርካሪ በሚጓዝበት ወቅት የተቀበረ ፈንጂ ረግጧል። እስራኤል ፈንጂው መቼ እንደተቀበረ እና የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጥሰት ይሆን እንደሆነ ለማረጋገጥ ምርመራ እንደምታካሂድ ተዘግቧል።

    በሌላ ክስተት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የሊባኖስ ጊዜያዊ ኃይል አባል የሆነ ፈረንሳዊ ሰላም አስከባሪ ሊባኖስ ውስጥ ተገድሏል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለጥቃቱ ሄዝቦላህን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ታጣቂ ቡድኑ ግን ከክስተቱ ጋር “ምንም ግንኙነት እንደሌለው” በመግለጽ አስተባብሏል።

  9. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ቀጣይ ዙር ድርድር ለማድረግ የተቀመጠ ቀን እንደሌለ ገለጸች

    የኢራንን ባንዲራ የያዘች ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

    ኢራን እና አሜሪካ ለሚያደርጉት ቀጣይ ዙር ድርድር የተቆረጠ ቀን አለመቀመጡን እና ከንግግሩ በፊት የመግባቢያ ማዕቀፍ ላይ ስምምነት ሊደረስ እንደሚገባ የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    በአውሮፓውያኑ 1979 የኢራን እስላማዊው አብዮት ከፈነዳ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓኪስታን ውስጥ የተደረገው የባለፈው ሳምንት የአሜሪካ እና ኢራን ንግግር ያለ ስምምነት መቋጨቱ ይታወሳል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ቀጥተኛ ንግግር ሊደረግ እንደሚችል ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።

    ዲፕሎማቶች ግን ንግግሩ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅባት የፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማድ ውስጥ ድርድር ለማድረግ ከሚያስፈልገው ሎጂስቲክስ አንጻር የመደረግ እድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

    ቱርክ ውስጥ እየተካሄደ ባለ የዲፕሎማሲ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ያሉት የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳኢድ ኻቲብዛዴህ ከዝግጀቱ ጎን ለጎን ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።

    "አሁን ትኩረታችን በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የመግባቢያ ማዕቀፍ ማጠናቀቅ ላይ ነው። ከጅምሩ እንዲከሽፍ ወደተፈረደበት እና ለሌላ ዙር ግጭት ምክንያት ሊሆን ወደሚችል ማንኛውም ድርድር ወይም ስብሰባ መግባት አንፈልግም" ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

    “ማዕቀፉ ላይ እስካልተስማማን ድረስ ቀኑን ማስቀመጥ አንችልም” ያሉት ሳኢድ፤ ከዚህ ቀደም በተደረገው ንግግር ውጤት ላይ ያልተደረሰው አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ባቀረበችው ጥያቄ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

    በድርድሩ “ከፍተኛ መሻሻል ታይቶ ነበር። ነገር ግን ሌላኛው ወገን ኢራንን ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጪ ለማድረግ በመሞከር የተከተለው ሁሉንም ማግኘት አለብኝ የሚል አካሄድ ስምምነት ላይ ከመድረስ አግዶናል” ብለዋል።

  10. የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ወታደር ሊባኖስ ውስጥ ተገደለ

    የተመድ ሰላም አስከባሪ ተሽከርካሪ እና ወታደሮች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተከፈተበት ጥቃት አንድ ፈረንሳዊ ወታደር ሲገደል፤ ሦስት ሰዎች ቆሰሉ። ባለሥልጣናት ጥቃቱ የተፈጸመው ሆነ ተብሎ እንደሆነ በመግለጽ ከስሰዋል።

    ፈረንሳዊው ወታደር ሲያገለግልበት የነበረው የተባበሩት መንግሥታት የሊባኖስ ጊዜያዊ ኃይል፤ የሰላም አስከባሪ አባሉ መገደሉን አረጋግጧል። የሰላም አስከባሪው ኃይል ተሽከርካሪ በተከፈተበት ተኩስ ከቆሰሉት ሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።

    የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለተፈጸመው ጥቃት ሄዝቦላህን ተጠያቂ አድርገዋል። በኢራን የሚደገፈው ታጣቂ ቡድን በበኩሉ ከክስተቱ ጋር “ምንም አይነት ግንኙነት” እንደሌለው በመግለጽ አስተባብሏል።

    ሄዝቦላህ ባወጣው መግለጫ የቀረበበትን ውንጀላ “የተጣደፈ” እና “መሠረት የለሽ ክስ” ሲል ጠርቶታል። “የሊባኖስ ጦር ምርመራ ሙሉ ሁኔታውን እስከሚገልጽ ድረስ ክስተቱን በተመለከተ የሚደረግ ፍርድ ማስተላለፍ እና ተጠያቂነት መስጠት ላይ” ጥንቃቄ እንዲወሰድ ጠይቋል።

    በደቡባዊ ሊባኖስ ይህ ጥቃት የተፈጸመው በሄዝቦላህ እና እስራኤል መካከል ባገረሸው ግጭት የተነሳ የሰላም አስከባሪ አባላት ላይ የተጋረጠው ስጋት በጨመረበት ሰዓት ነው።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የደረሱት የ10 ቀናት የተኩስ አቁም ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን ስምምነቱን ይፋ ያደረገችው አሜሪካ ሄዝቦላህ ለተኩስ አቁሙ እንዲገዛ እያሳሰበች ነው።

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳን ማክሮን “ሁሉም ነገር የሚጠቁመው የጥቃቱ ኃላፊነት ሄዝቦላህ ላይ እንደሚወድቅ ነው” ብለዋል። የሊባኖስ ባለሥልጣናት “በአስቸኳይ ጥቃት ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ” ጠይቀዋል።

    የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይም ጥቃቱን አውግዘዋል። ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ተኩስ የተከፈተበት የሄዝቦላህ አባላት እንደሆነ በተገመቱ “መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት” መሆኑን ተናግተዋል።

    ሁሉም አካላት የተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ እና ግጭቶችን እንዲያቆሙም አሳስበዋል።

    የሊባኖስ ጦር ኃይል በበኩሉ ከታጠቁ ግለሰቦች ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደተካሄደ ገልጿል። አገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር በደረጉት ስልክ ንግግር ጥቃቱን አውግዘዋል፤ ተጠያቂዎቹ አካላት ለፍትሕ እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

  11. የቀድሞ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ትራምፕ ወደ ጦርነት “ተጎትተው” የገቡት በኔታንያሁ ነው አሉ

    የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ፤ ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ “ተጎትተው” ከኢራን ጋር የሚደረገው ጦርነት ውስጥ ገብተዋል ሲሉ ተናገሩ።

    ካማላ ይህንን አስተያየታቸውን ያሰሙት ትናንት ቅዳሜ በተካሄደ አንድ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

    “ወደ ጦርነት ገብቷል፤ የገባውም በቢቢ ኔታንያሁ ተጎትቶ ነው፤ ስለዚህ ጉዳይ ግልጽ መሆን አለብን። አሜሪካውያን የማይፈልጉት ጦርነት ውስጥ ነው የገባው፣ የአሜሪካ የሠራዊት አባላትን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለካማላ ሃሪስ ንግግር በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም እስራኤል “ታላቅ አጋር” መሆኗን የሚገልጽ ጽሑፍ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

    “ሰዎች እስራኤልን ወደዱም አልወደዱ የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ታላቅ አጋር መሆኗን አስመስክራለች። ደፋር፣ ቆራጥ፣ ታማኝ እና ብልህ ናቸው” ሲሉ አወድሰዋል።

    ትራምፕ አክለውም፤ “በግጭት እና ውጥረት ሰዓት ላይ ከሌሎች በተቃራኒ እውነተኛ ቀለማቸውን አሳይተዋል። እስራኤል በጥንካሬ ትዋጋለች፤ እንዴት እንደምታሸንፍም ታውቃለች” ብለዋል።

  12. የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ የዘጋችው ኢራን የሰላም ስምምነት ላይ የመድረስ ጉዳይ “ሩቅ” መሆኑን ገለጸች

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሐማድ ባገር ጋሊባፍ ከአሜሪካ ጋር የሚካሄደውን ጦርነት ለመቋጨት በሚደረገው ድርድር “መሻሻሎች ቢመዘገቡም” ሁለቱ ወገኖች “ለመጨረሻ ውይይት ሩቅ” መሆናቸውን ተናገሩ።

    የኢራንን ተደራዳሪ ቡድን የመሩት ጋሊባፍ ባለፈው ሳምንት በፓኪስታን ተገኝተው ከምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን እና ሌሎች የአሜሪካ ልዑካን ጋር ንግግር አድርገው ነበር። ይህ ንግግር ያለ ስምምነት የተቋጨ ሲሆን ቀጣዩ ዙር ድርድር መቼ እንደሚካሄድ እስካሁን ቁርጥ ቀን አልተቀመጠም።

    ከዚህ ንግግር በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን አግደዋል። ኢራን ከጦርነቱ መጀመር ወዲህ ዘግታው የቆየችውን ወሳኙን የባሕር መተላላፊያ ከከፈተች በኋላም የአሜሪካ እግድ ጸንቶ እንደሚቆይ ትራምፕ ተናግረዋል።

    በዚህ ያልተደሰተችው ኢራን ትናንት በድጋሚ ወሽመጡን ዘግታለች።

    የኢራኑ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ ትናንት በመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ ንግግራቸው አሜሪካ የጣለችውን እግድ “የተሳሳተ ግምገማ እና ውሳኔ” ሲሉ ጠርተውታል።

    "እገዳውን የማያነሱ ከሆነ በወሽመጡ በኩል የሚደረግ ጉዞ በእርግጠኝነት እንደሚገደብ ተናግሬ ነበር" ብለዋል። አሁንም ቢሆን ወሽመጡ በኢራን “ቁጥጥር ስር” እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    “ለሁለት ወይም ሦስት ቀናት ያህል [አሜሪካ] ሆነ ብላ ከበባ ፈጽማለች። ከበባ ምን ማለት ነው? ሁሉም ሰው ይመጣል፣ ይሄዳል፤ ኢራን ግን አትጓዝም ማለት ነው። እንዴት ያለ የሞኝ እና የድንቁርና ውሳኔ ነው” ሲሉ በጠንካራ ቃላት ተችተዋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎችን የማጽዳት ዘመቻ ማካሄድ እንደምትፈልግ የተናገሩት ጋሊባፍ፤ ኢራን "በጽናት በመቆም አሜሪካን ተጋፍጣለች" ብለዋል።

    "ይህንን እቅድ እንደ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት ነው የቆጠርነው፤ እንዲህ አይነት እርምጃ የሚወስዱ ከሆነም ጥቃት እንደምንፈጽም ተናግረናል" ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።

    ጋሊባፍ፤ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከኢራን መንግሥት ውስጥ መዋቅር ውስጥ ቁልፍ ሰው ሆነው የወጡ ፖለቲከኛ ናቸው። ባለፈው ሳምንት ኢራን እና አሜሪካ በኢስላማባድ ባደረጉት ንግግር ላይም የቴህራንን ልዑክ መርተዋል።

  13. ትራምፕ ኢራን “ልታስፈራራን አትችልም” አሉ

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን ጦር የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግመኛ መዝጋቱን ካስታወቀ በኋላ በሰጡት ምላሽ ቴህራን “ልታስፈራራን አትችልም” አሉ።

    “ለረዥም ዓመታት እንዳደረጉት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት ይፈልጋሉ” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ትራምፕ “ሊያስፈራሩን አይችሉም” ብለዋል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር “በጣም ጥሩ ውይይት እየተካሄደ ነው” በማለት ቴህራን “ላለፉት 47 ዓመታት እንደነበሩት ለማታለል እየሞከሩ ነው” ብለዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት ይፈልጋሉ ያሉት ትራምፕ፣ አሜሪካን “እንድታስፈራራ” አንፈቅድም ብለዋል።

    አሜሪካ ጠንካራ አቋም ትወስዳለች ሲሉም አክለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ አክለውም ኢራንን በሚመለከት “በቀኑ መጨረሻ ላይ ተጨማሪ መረጃ” እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መዝጋቷን ካስታወቀች በኋላ የኢራን አብዮታዊ ዘብ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ተኩስ መክፈቱ ተሰምቷል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ መሳሪያ የታጠቁ ጀልባዎች ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ ተኩስ መክፈታቸውን የገለጸው የዩኬ የባሕር ትራንስፖረት ማዕከል ነው።

    አብዮታዊ ዘቡ በነዳጅ ጫኝ መርከቡ ላይ የተኮሰ ቢሆንም የመርከቢቷ ሠራተኞች በደህና ሁኔታ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

  14. ኢራን ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመቆጣጠር “ቁርጠኛ’ መሆኑን የደህንነት ምክር ቤቱ አስታወቀ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የምታልፍ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን “ጦርነቱ እስኪያበቃ እና በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ለመቆጣጠር እና ለመከታተል ቁርጠኛ ነች” አለ።

    የአገሪቱ ደህንነት በበላይነት የሚቆጣጠረው ምክር ቤቱ ክትትሉን እና ቁጥጥሩን የሚያደርገው በወሽመጡ የሚተላለፉ መርከቦችን መረጃ በመሰብሰብ እና የይለፍ ወረቀት በመስጠት እንዲሁም ለተገቢው አገልግሎት ክፍያን በመቀበል መሆኑን አስታውቋል።

    የደህንነት ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጠው መግለጫ "ጠላት የመርከቦችን መተላለፊያ ለማስተጓጎል እና የባህር ላይ እገዳን ተግባራዊ ማድረግ እስከቀጠለ ድረስ ኢራን ይህንን የተኩስ አቁም ጥሰት አድርጋ ትቆጥረዋለች” ብሏል።

    በተጨማሪም “የሆርሙዝ ወሽመጥን በሁኔታዎች እና ውሱን በሆነ መልኩ እንዳይከፈት ታደርጋለች" ሲል አክሏል።

    ጦርነቱን ለማቆም ስለሚደረገው ድርድር ምክር ቤቱ ቴህራን አሜሪካ ያቀረበችውን ምክረ ሃሳብ "እየገመገመች ሲሆን እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም" ብሏል።

  15. የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ዛሬ በሊባኖስ አንድ ፈረንሳዊ ወታደር መገደሉን ተናገሩ

    ኢማኑኤል ማርኮን

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑዔል ማርኮን በኤክስ ገጻቸው ላይ በሊባኖስ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ አባል የሆነ ፈረንሳዊ ዛሬ ማለዳ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል መገደሉን አስታወቁ።

    የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም ማስጠበቅ ተልዕኮ አባል የሆኑ ሌሎች ሦስት ወታደሮች መጎዳታቸውን እና ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ጨምረው አስታውቀዋል።

    ማርኮን አሁን ባለው መረጃ ለጥቃቱ ተጠያቂው ሄዝቦላህ ነው ብለዋል።

    አክለውም የሊባኖስ ባለሥልጣናት ጥቃቱን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት ሰዎች በፍጥነት በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ ጠይቀዋል።

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም በፈረንሳይ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

    "የዚህን ጥቃት ሁኔታ ለማወቅ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ አፋጣኝ ምርመራ እንዲደረግ ጥብቅ መመሪያ አውጥቻለሁ" ሲሉ በኤክስ ፈገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕከት ላይ ተናግረዋል።

    “ይህ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት በሊባኖስ እና በሚደግፏት ወዳጅ የዓለም አገራት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ሳልገልጽ ማለፍ አልፈልግም።”

    ሳላም ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው አልገለጹም።

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  16. በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች በኢራን ጦር ተኩስ ተከፈተባቸው

    ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ

    የፎቶው ባለመብት, UKMTO

    አንድ መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ ሲያልፍ በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሚመሩ ሁለት መሣሪያ የታጠቁ ጀልባዎች ተኩስ እንደተከፈተበት የዩኬ የባሕር ላይ ትራንስፖርት ሥራዎች አስታወቀ።

    ክስተቱ የተፈጠረው በኦማን ሰሜን ምሥራቅ ግዛት 40 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ መሆኑ ታውቋል።

    መርከቡ እና ሠራተኞች ደኅና መሆናቸውን ዩኬ ማሪታይም ንግድ ሥራዎች ገልጿል።።

    ከዚህ ውጭ ቢያንስ ሁለት የንግድ መርከቦች ወሽመጡን ለመሻገር ሲሞክሩ የጥይት ሩምታ እንደተከፈተባቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ሦስት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    ሮይተርስ መርከቦች ከኢራን ባሕር ኃይል ወሽመጡ መዘጋቱን የሚያሳውቅ የራዲዮ መልዕክት እንደደረሳቸውም ዘግቧል።

    የኢራን ባሕር ኃይል አንድም መርከብ በወሽመጡ እንዲያልፍ አልተፈቀደለትም ማለታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

  17. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የወሰደችው እርምጃ ትራምፕ ጦርነቱ በቅርብ በስምምነት እንደሚፈታ መናገራቸውን አጠራጣሪ አደረገ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚንቀሳቀስ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ በእርጠኝነት መናገር ከባድ ሆኗል።

    በብሔራዊ መገናኛ ብዙኃኑ የተላለፈው የኢራን ወቅታዊ መልዕክት አሜሪካ በወደቦች ላይ የጣለችው እግድ ተፈፃሚነቱ በመቀጠሉ ምክንያት የሆርሙዝ ወሽመጥ በድጋሚ ተዘግቷል የሚል ነው።

    እንደ ቴህራን ከሆነ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች በሚገቡ እና በሚወጡ መርከቦች ላይ የጣለችው እግድ አሁንም ተፈፃሚ ነው ማለት ነው።

    ኢራናዊያን ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ነበርንበት እንመለሳለን እያሉ ሲሆን፤ ይህም ወሽመጡ በኢራን ጦር ቁጥጥር ስር ተመልሷል ማለት ነው።

    እስካሁን ከዋይት ሐውስ የተሰጠ ምላሽ አልተሰማም። በዋሽንግተን ዲሲ ሌሊቱ ተገባዶ አዲስ ቀን ሲጀመር መስማታችን ግን አይቀሬ ነው።

    ትናንት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ ለሙሉ እንደተከፈተ እና ለንግድ መርከቦች መተላለፊያነት ዝግጁ መሆኑን ያበሰሩትን ዜና ማየት አልተቻለም።

    በተመሳሳይ ጊዜ የተከማቸውን የበለፀገ ዩራኒየም አሳልፎ መስጠትን ጨምሮ ኢራን ያቀረቧቸውን መደራደሪያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቀብላ መስማማቷን ገልፀዋል። ይህን ስምምነት ግን ኢራን ሐሰት ነው ብላለች።

    ትራምፕ ከቴህራን ጋር ትልቅ ስምምነት መፈፀማቸው የማይቀር እንደሆነ ጠቁመዋል።

    በኢራን የተወሰደው እርምጃ ይህን ስምምነት እውን የሚያደርግ አይመስልም።

    አሁንም ድረስ በሁለቱም ወገኖች የሚወጡ የሚዲያ መልዕክቶች ከትዕይንቱ በስተጀርባ ጸጥ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያካተተ ስለመሆኑ ማወቅ ከባድ ነው።

    ባለፈው ሳምንት በፓኪስታን ያለ ውጤት የተጠናቀቀውን ንግግር ተከትሎ ሁለቱ ወገኖች ሁለተኛ ዙር ንግግር ያደርጋሉ የሚል የተወሰነ ተስፋ አለ።

  18. የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል የሚሉ ዘገባዎች ከወጡ በኋላ መርከቦች አቅጣጫ እየቀየሩ ነው

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቦች እንቅስቃሴ

    የፎቶው ባለመብት, MarineTraffic

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ከአንድ ሰዓት በፊት የቴህራን ጦር የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቱን ከዘገበ በኋላ በርካታ መርከቦች አቅጣጫቸውን እየቀየሩ መሆናቸው ታይቷል።

    ነዳጅ የጫነው እና የግሪክን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልበው ሚኒርቫ ኤቨሮፒ የተሰኘ አንድ መርከብ መጀመሪያ ወደተነሳበት አቅጣጫ ሲመለስ ታይቷል።

  19. የኢራን ጦር የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መዝጋቱን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

    የኢራን ጦር ጀልባ

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty images

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ ጦር የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መቆጣጠር እንደጀመረ መግለጹን ዘገቡ።

    ፋርስ የዜና ወኪል፣ የኢራን የተማሪዎች ዜና ወኪል እንዲሁም ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃኑ ኢሪብ አብዮታዊ ዘቡን ጠቅሰው የወሽመጡ አካባቢን ጦሩ ተቆጣጥሮ “በቀደመ ሁኔታው ላይ” መመለሱን ዘግበዋል።

    የተወሰኑ የጭነት መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፍ ችለው ነበር።

    አብዮታዊ ዘቡ በመግለጫው አሜሪካን “በባሕር ላይ ውንብድና” ወንጅሎ “እገዳ የምትለው” ከባሕር ላይ ዘረፋ አይተናነስም ብሏል።

    ኢራን ቀደም ሲል ወደቦቿ ተዘግተው የሚቆዩ ከሆነ ወሽመጡን እንደምትዘጋ ዝታ ነበር።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን በስተደቡብ የሚገኝ ጠባብ መተላለፊያ ሲሆን የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ይጓጓዝበታል።

    ኢረን ከአሜሪካ ያደረገችው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር ወደ ኢራን ወደቦች መርከቦች እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ ለማድረግ እገዳ ጥሏል።

    የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን እገዳው ካልተነሳ ሆርሙዝን እንደሚዘጉ ሲያስጠነቀቅቁ ቆይተዋል።

  20. ኢራን በከፊል የአየር ክልሏን ከፈተች- የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን

    የኢራን አየር ክልል እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ አንስቶ ለማንኛውም በረራ ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን አየር ክልል እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ አንስቶ ለማንኛውም በረራ ዝግ ሆኖ ቆይቷል

    ኢራን በከፊል የአየር ክልሏን ለዓለም አቀፍ በረራዎች ክፍት ማድረጓን የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ኢርና ዘገበ።

    የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የአገሪቱ የአየር ክልል እና ክፍት የሆኑ አውሮፕላን ማረፊያዎችን አስታውቋል።

    በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከ7፡00 (ምሽት 12:30) ጀምሮ የአየር ክልሏ በከፊል ክፍት እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ቀስ በቀስ በረራዎች ይጀምራሉ ሲል ኢርና ዘግቧል።

    በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኙ የበረራ መስመሮች ለዓለም አቀፍ በረራዎች ክፍት መሆናቸውንም መገናኛ ብዙኃኑ አስታውቋል።

    የኢራን አየር ክልል እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ አንስቶ ለማንኛውም በረራ ዝግ ሆኖ ቆይቷል።