በምሥራቅ ኮንጎ በተከሰተ የኢቦላ ወረርሽን 65 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Universal Images Group via Getty Images
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ኢቱሪ ግዛት የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን አስታወቀ።
ሲዲሲ አፍሪካ በዋናነት የወርቅ ማዕድን በሚወጣባቸው ሞንግዋሉ እና ሩዋምፓራ ከተሞች 246 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን እና 65 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።
ማዕከሉ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከኡጋንዳ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ስለሚወሰዱ እርምጃዎች እና መደረግ ያለበትን ድንበር ተሻጋሪ ክትትል ለመወያየት ስብሰባ መጥራቱን አስታውቋል።
ኢቦላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው አሁን ዲሞክራቲክ ኮንጎ በመባል በምትታወቀው ግዛት ውስጥ እአአ በ1976 ነው።
ኢቦላ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በሌሊት ወፎች አማካኝነት እንደሆነ ይታሰባል። ይህ በአገሪቱ ውስጥ ለ17ኛው ጊዜ የተከሰተ ወረርሽኝ ነው።
ከሰውነት በሚወጣ ፈሳሽ ጋር በሚኖር ቀጥታ ግንኙነት የሚተላለፈው በሽታው ከባድ የደም መፍሰስ እና የአካል ክፍሎች ሥራ መቆምን ያስከትላል።
ትኩሳት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ድካም፣ ራስ ምታት እና የጉሮሮ ሕመም የበሽታው ምልክቶች ናቸው። በኢቦላ ለተያዘ ሰው የሚሰጥ ምንም ዓይነት መድኃኒት የለም።
ከ65ቱ በበሽታው ተይዘው ከሞቱ ሰዎች መካከል የአራቱ የሞት መንስዔ በላብራቶሪ መረጋገጡን ሲዲሲ አፍሪካ አስታውቋል።
የኢቱሪ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ቡኒያ ተጨማሪ በበሽታው መያዛቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን የምርመራ ውጤታቸው እየተጠበቀ ነው።
የኮንጎ መንግሥት እስካሁን በይፋ ወረርሽኙ መከሰቱን አላወጀም።
ባለፉት 50 ዓመታት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ወደ 50,000 የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ሞተዋል።
ወረርሽኙ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተው እአአ ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን በዚህ ወቅት ወደ 2,300 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል።
ባለፈው ዓመት የኢቦላ ወረርሽኝ በማዕከላዊ ካሳይ ግዛት ተከስቶ 45 ሰዎች ሞተዋል።






















