ቀጥታ, ትራምፕ ቻይና ለኢራን ወታደራዊ መሣሪያ እንደማታቀርብ ዢ እንዳረጋገጡላቸው ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይት ቤይጂንግ ለኢራን ጦር መሣሪያ እንደማታቀርብ መናገራቸውን ገለጹ። “ጦር መሣሪያ እንደማይሰጡ ገልጸውልኛል። ይህ በጣም ትልቅ ንግግር ነው” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ቤይጂንግ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈቱን እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Fox News

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሐሙስ ዕለት ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር ስለ ኢራን ጦርነት ከተነጋገሩ በኋላ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ትዕግሥታቸው እየተሟጠጠ መሆኑን ነው የገለጹት።

    በትናንትናው ዕለት ከተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ የባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የኢራን ወታደሮች መርከብን ማገታቸው ተሰምቷል።

    ዋይት ሐውስ ትራምፕ እና ዢ በውይይታቸው ወቅት የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት እንዲሆን መስማማታቸውን ገልጿል።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጦርነት ከከፈቱባት በኋላ ኢራን የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።

    ይህም የዓለም የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ፍሰትን እንዲሁም ንግድን አስተጓጉሏል።

    ቻይና የኢራን የቅርብ አጋር ስትሆን ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ዘይትም የምትገዛው ከእርሷ ነው።

    አሜሪካ በቴህራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ባለፈው ወር ያቋረጠችው ኢዝላማባድ ካደራደረች በኋላ ሲሆን ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ የመርከብ እንቅስቃሴዎችን ግን ሙሉ በሙሉ አግዳለች።

    ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማቋረጥ እና የበለጸገው ዩራኒየሟን ለማስረከብ ባለማስማማቷ በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው ንግግር ተቋርጧል።

    ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ወቅት “ከዚህ በላይ ትዕግሥት አይኖረኝም” ብለዋል።

    አክለውም “መስማማት አለባቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ኢራን ያከማቸችው የበለጸገ ዩራኒየም ከደህንነት አንጻር ያን ያህል አሳሳቢ እንደማይሆን ገልጸው ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ ግን በአሜሪካ ቁጥጥር ስር መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል።

    “ከሕዝብ ግንኙነት ሥራ በስተቀር አስፈላጊ የሚሆን አይመስለኝም” ሲሉ በቃለ ምልልሱ ላይ ተናግረዋል።

    “በእኔ ቁጥጥር ሥር ቢኖር የበለጠ ጥሩ ይሰማኛል። ነገር ግን እንደማስበው ከሌላ ነገር ይልቅ የበለጠ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ነው።”

  2. ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ለኢራን የጦር መሣሪያ ላለመስጠት መስማማቷን ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reu

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይት ቤይጂንግ ለኢራን ጦር መሣሪያ እንደማታቀርብ መናገራቸውን ገለጹ።

    “ጦር መሣሪያ እንደማይሰጡ ገልጸውልኛል። ይህ በጣም ትልቅ ንግግር ነው” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ቤይጂንግ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈቱን እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት “ድጋፍ ሲባል ከእኛ ጋር ጦርነት ላይ ይሳተፋሉ ወይንም ሌላ ማለት አይደለም” ካሉ በኋላ “የጦር መሣሪያ እንደማይሰጡ ነግረውኛል፤ ይህ ትልቅ ነገር ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ በተጨማሪም ዢ ቻይና የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ዳግም እንዲከፈት እንደምትፈልግ እንደነገሯቸው ገልጸው ምክንያቱም ቤይጂንግ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ዘይት የምትገዛው ከቀጣናው አገራት ነው ብለዋል።

    "ብዙ የነዳጅ ዘይታቸውን የሚገዙት ከዚያ ነው፤ እናም ያንን ማድረጋቸውን መቀጠል ይፈልጋሉ" ብለዋል ትራምፕ፤ አክለውም ዢ "የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ሆኖ ማየት ይፈልጋል" ብለዋል።

    “ፕሬዚዳንት ዢ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ማየት ይፈልጋል። ‘በማንኛውም መንገድ መርዳት የምችል ከሆነ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ’ ብሏል። ያን ያህል የነዳጅ ዘይት የሚገዛ ማንኛውም አካል የሆነ ግንኙነት እንደሚኖረው እርግጥ ነው። ነገር ግን የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ሆኖ ማየት ይፈልጋል” ሲሉ አክለዋል።

    የቻይና ባለሥልጣናት ትራምፕ በሰጡት አስተያየት ዙሪያ እስካሁን ድረስ ያሉት ነገር የለም።

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ስለተነጋገሩባቸው ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ ላይ ኢራንም ሆነች የሆርሙዝ ወሽመጥ አልተጠቀሱም።

    መግለጫው ሁለቱ መሪዎች “በዋና ዋና ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች -የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ፣ የዩክሬን ቀውስ እና በኮሪያ ባህረ ገብ ዙሪያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል” ይላል።

    ፎክስ ኒውስ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ካደረገው እና ቀንጭቦ ባስተላለፈው ቃለ ምልልሰ ላይ ትራምፕ የቻይናው መሪ ሰፊ የምጣኔ ሃብት ትብብር ከአሜሪካ ጋር ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

    ይህም የአሜሪካ አኩሪ አተርን፣ የአሜሪካን ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝን እንዲሁም ቦይንግ አውሮፕላን መግዛት ያካትታል።

    “200 አውሮፕላኖችን ሊያዝ ነው፤ ያ ትልቅ ነገር ነው. . . ቦይንግ 150 ነበር የፈለገው ሁለት መቶ አግኝቷል” ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል። “ይህ ቁርጠኝነት ይመስለኛል። ከመግለጫ በላይ ይመስላል፤ . . .እውነተኛ ቁርጠኝነት ይመስለኛል።”

    ፎክስ ኒውስ ቀደም ብሎ ባስተላለፈው ዜና ላይ የቻይናው መሪ ዢ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት መስማማታቸውን ትራምፕ አንደተናገሩ ዘግቧል።

  3. ኢራን ጎረቤቶቿ ላይ ሥጋት የመሆን አቅሟ በከፍተኛ መጠን መውረዱን የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዥ ተናገሩ

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዡ አድሚራል ብራድ ኩፐር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን ጎረቤቶቿን እና የአሜሪካ ጥቅም ያለባቸው ስፍራዎችን ስጋት ውስጥ ለመክተት ያላት አቅም በዋሽንግተን ጥቃት ምክንያት በከፍተኛ መጠን እንደቀነሰ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዡ አድሚራል ብራድ ኩፐር፤ በተፈጸሙት ጥቃቶች ምክንያት የኢራን የመከላከያ ኢንዱስትሪ 90 በመቶ ወደ ኋላ መመለሱን ገልጸዋል።

    ወታደራዊ አዛዡ ይህንን ያሉት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የአሜሪካ የስለላ መረጃን መሠረት አድርገው ባወጡት ዘገባ የኢራን የሚሳዔል ክምችት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚገልጹት ደረጃ ጉዳት እንዳልደረሰበት ከዘገቡ በኋላ ነው።

    የአሜሪካው ጋዜጣ ዋሽንግተን ፖስት፤ ኢራን አሁንም ከፍተኛ የባለስቲክ ሚሳዔል አቅም እንዳላት የሲአይኤ ሪፖርትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ አስነብቦ ነበር።

    ኢራን ከጦርነቱ በፊት ከነበሯት ተንቀሳቃሽ ሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች ውስጥ 75 በመቶውን እንዲሁም ከሚሳዔል ክምችቷ 70 በመቶውን አሁንም እንደያዘች ተገልጿል።

    የዜና ወኪሉ ሮይተርስም፤ ኢራን ከምድር ስር ባሉ ተቋማት ከፍተኛ የሚሳዔል እና የድሮን ክምችት እንዳላት ዘግቦ ነበር።

    ሮይተርስ ዛሬ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አዛዡ አድሚራል ብራድ ኩፐር እነዚህ ዘገባዎችን በቀጥታ ጠቅሰው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

    ይሁን እንጂ በሴኔት ኮሚቴ በነበረው ስብሰባ ላይ “ኢራን በከፍተኛ ደረጃ የወረደች ስጋት ነን። ከአሁን ወዲህም ከዚህ ቀደም ማድረግ ይችሉት በነበረው መንገድ፤ በሁሉም ዘርፍ ቀጣናዊ አጋሮች ወይም አሜሪካ ላይ ስጋት አይጥሉም” ብለዋል።

    ወራደራዊ አዛዡ አክለውም ከአሁን በኋላ ኢራን በቀጣናው የሚገኙ ዋነኛ አጋሮቿ ለሆኑት ሄዝቦላህ፣ ሁቲ እና ሐማስ መሣሪያ እንዲሁም ሌሎች ሀብቶችን ማስተላለፍ እንደማትችል መናገራቸውን ዘገባው ያሳያል።

    “እነዚያ የማስተላለፊያ መንገዶች እና ዘዴዎች ተቆርጠዋል” ብለዋል።

  4. በሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች ላይ አዲስ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

    ካርታ

    በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መልሕቁን ጥሎ የነበረ መርከብ ተይዞ ወደ ኢራን መወሰዱን እና ሌላ መርከብ በተፈጸመበት ጥቃት መስመጡ ተገለጸ።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዙ መርከቦችን በተመለከተ የተፈጠረው ውጥረት እንዲባባስ ላደረጉት እነዚህ ክስተቶች እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።

    ቫንጋርድ የተሰኘው የማሪታይም አደጋ አተስዳደር ኩባንያ እንደገለጸው ከሆነ ግን መርከቡ በኦማን ባሕረ ሰላጤ የተያዘው በኢራን ወታደሮች ነው።

    የዩናይትድ ኪንግደም የማሪታይም ንግድ ኦፕሬሽን ድርጅት በበኩሉ በአሁኑ ሰዓት መርከቡ “ወደ ኢራን ግዛት ውስጥ ወደ ሚገኘው የውሃ ክፍል እየተጓዘ” ነው።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ፤ ‘ማሪንትራፊክ’ ከተሰኘው የባሕር ጉዞ መከታተያ ድረ ገጽ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው መርከቡ ረዕቡ ዕለት መርከቡ ከሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ ከኤምሬቶች ፉጃይራህ ወደብ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር።

    ‘ሁዊ ቹዋን’ የተባለው ይህ መርከብ አስተዳዳሪዎች ለቫንጋርድ እንደገለጹት፤ መርከቡ የንግድ መርከቦችን ከባሕር ወንበዴዎች ለሚከላከሉ የደኅንነት ተቋማት የጦር መሣሪያዎች ማከማቻ ሆኖ ያገለግል ነበር።

    ቢቢሲ በመርከቡ ላይ ምን እንደነበረ ወይም በማን ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ማረጋገጥ አልቻለም።

    የአሶሺዬትድ ፕሬስ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ክስተቱ የተፈጸመው አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ቴህራን በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ላይ ያላትን ቁጥጥር በድጋሚ ከገለጹ በኋላ ነው። ሌላ ባለሥልጣን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የነዳጅ ጫኝ መርከቦች የመያዝ መብት አለን ብለው ነበር።

    ይህ መርከብ መያዙ የተሰማው የሕንድን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ መርከብ ረቡዕ ዕለት በኦማን የባሕር ዳርቻ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመበት ከተገለጸ በኋላ ነው።

    ሃጂ አሊ የተባለው መርከብ በኦማን ባሕር ዳርቻ “እንደሰመጠ” ተገልጿል። መርከቡ የሰመጠው "በድሮን ወይም በሚሳዔል" እንደተፈጸመ በተጠረጠረ ጥቃት ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ መሆኑን የቫንጋርድ መረጃ ያሳያል።

    የሕንድ ባለሥልጣናት ዛሬ ባወጡት መግለጫ፤ "በመርከቡ ላይ የነበሩ የሕንድ ዜግነት ያላቸው ሠራተኞች በሙሉ ደኅንነታቸው ተጠብቋል፤ የኦማን ባለሥልጣናት ላከናወኑት የነፍስ አድን ሥራ እናመሰግናለን" ብለዋል።

    መርከቡ ላይ የነበሩ 14 ሠራተኞች በኦማን ባሕር ዳርቻ ዘብ አባላት አማካኝነት ወደ አገሪቱ ዲባ ወደብ መወሰዳቸውን የሕንድ ባለሥልጣናት ጠቅሰዋል።

    መርከቡ ከሶማሊያ ተነስቶ ሻርጃ ወደሚገኘው የኤምሬቶች ወደብ እየቀዘፈ እንደነበር የባሕር ጉዞ መከታተያው ‘ማሪን ትራፊክ’ አሳይቷል።

  5. ኢራን እና ኤምሬቶች በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተወዛገቡ

    ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    ሕንድ ውስጥ በሚካሄደው የብሪክስ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢራን ላይ በተከፈተው ወታደራዊ ዘመቻ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳላት በመጥቀስ መክሰሳቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    ውዝግቡ የተነሳው፤ ኤምሬቶች የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በኢራን ጦርነት ወቅት ወደ አገሪቱ መጓዛቸውን በመግለጽ ያወጡትን መግለጫ ባስተባበለች ማግሥት ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከዚያ በኋላ በብሪክስ ስብሰባ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ “መከፋፈልን ለመዝራት ከእስራኤል ጋር የተጣመሩ አካላት ተጠያቂ ይሆናሉ” ማለታቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

    አራግቺ “[በብሪክስ] መግለጫዬ ላይ የኤምሬቶች ስም ያልጠቀስኩት ለአንድነት ስል ነው። እውነታው ግን፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አገሬ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራት። ጥቃቶቹ ሲጀመሩ የውግዘት [መግለጫ] እንኳ አላወጡም” ሲሉ መክሰሳቸውን ሮይተርስ የጠቀሰው የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ለኤምሬቶች ተወካይ ንግግር በሰጡት ምላሽ መሆኑን ይገልጻል። የኤምሬቶች ተወካይ የሰጡት አስተያየት ምን እንደሆነ ግን ዘገባው አልጠቀሰም።

    ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችም ሆኑ ከእስራኤል ጋር ያላት አጋርነት ለኤምሬቶች ደኅንነት አላስገኘላትም ብለዋል። ኢራንን በተመለከተ የምትከተለውን ፖሊስም በድጋሚ እንድታጤን ጠይቀዋል።

    “ጎን ለጎን ሆነን በሰላም መኖር አለብን። ይሄ ደግሞ የሰላማዊ ግንኙነቶችን መኖር እና በሁለቱ አገራት መካከል ሙሉ የሆነ መረዳዳትን ይጠይቃል” ብለዋል።

  6. የናይጄሪያ የቀድሞ ሚኒስትር ባልተለመደ ሁኔታ በሙስና ክስ 75 ዓመት ተፈረደባቸው

    የቀድሞ የናይጄሪያ የኃይል ሚኒስትር ሳለህ ማማን

    የፎቶው ባለመብት, Nigeria's power ministry

    የቀድሞ የናይጄሪያ የኃይል ሚኒስትር ሳለህ ማማን በቀረበባቸው 24.7 ሚሊዮን ዶላር ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ክስ ጥፋተኛ ተብለው የ75 ዓመት እስር ተፈረደባቸው። በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ውስጥ ይህ ዓይነቱ የሙስና ወንጀል ፍርድ ያልተለመደ ነው።

    ማማን፤ በመንግሥት በጀት ከሚገነቡ ኃይል ማመንጫዎች ጋር የተገናኘ ገንዘብን በግል ኩባንያዎች በኩል ማዘዋወርን ጨምሮ በቀረቡባቸው 12 ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ባለፈው ሳምንት ነበር።

    የአገሪቱ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ወንጀሎች ኮሚሽን እንዳስታወቀው፤ የቀድሞው ሚኒስትር የተፈረደባቸው በሌሉበት ነው። ማማን ጥፋተኛ ከተባሉበት ጊዜ አንስቶ "የት እንዳሉ እንደማይታወቅ” ተገልጿል።

    በአቡጃ የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአውሮፓውያኑ ከ2015 እስከ 2021 ድረስ የኃይል ሚኒስትር በነበሩት ማማን ላይ ሰኞ ዕለት የእስር ትዕዛዝ አውጥቷል።

    በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ ዘመን ሚኒስትር የነበሩት ማማን፤ ስለተላለፈባቸው ፍርድ እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጡም።

    ጥፋተኛ ከመባላቸው ጥቂት ሳምንታት አስቀድሞ ግን በ2027 በሚካሄደው ምርጫ ገዢውን ፓርቲ ወክለው ታራባ ለተባለችው ግዛት ገዢነት ለመወዳደር ማቀዳቸውን አስታውቀው ነበር።

    ማማን የኃይል ሚኒስቴር የነበሩበት የፕሬዝዳንት ቡሃሪ አስተዳደር ሙስናን ለመዋጋት ቃል ገብቶ ነበር።

    የቀድሞው ፕሬዝዳንት "ገለልተኛ እና ሂሳዊ ግለ ግምገማ” ካደረጉ በኋላ የካቤኒ ለውጥ ባካሄዱበት ወቅት ማማንን ከሚኒስትርነት አንስተዋቸዋል።

    የቀድሞው ሚኒስትር ላይ የቀረበውን ክስ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማማን 16 ሚሊዮን ዶላር ተመላሽ እንዲያደርጉ አዝዟል።

    ከማማን በተጨማሪ የቀድሞ የፍትሕ እንዲሁም የሰብአዊ ጉዳዮች ሚኒስትሮች የሙስና ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።

  7. ኒው ዮርክ ውስጥ ምሥጢራዊ የቻይና “ፖሊስ ጣቢያ” በማንቀሳቀስ የተከሰሰ አሜሪካዊ ጥፋተኛ ተባለ

    ሉ ጂአንዋንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ሉ ጂአንዋንግ

    የቻይና መንግሥትን በመወከል አሜሪካ ውስጥ ምሥጢራዊ "ፖሊስ ጣቢያ" እንዲከፈት እና እንዲንቀሳቀስ ድጋፍ አድርጓል የተባለ አሜሪካዊ ዜጋ ጥፋተኛ ተባለ።

    ሉ ጂአንዋንግ የተባለው የ64 ዓመት ግለሰብ ኒው ዮርክ ማንሃተን ውስጥ 'ቻይናታውን' በተባለው አካባቢ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ለቻይና የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስቴር ፖሊስ ጣቢያ ከፍቶ እያንቀሳቀሰ በመገኘቱ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎታል።

    ጉዳዩን የሚመሩት የኤፍቢአይ ረዳት ዳይሬክተር ጄምስ ሲ ብራንክሌ ጁኒየር፤ “ሉ ጂአንዋንግ ኒው ዮርክ ውስጥ የሚገኘውን ፖሊስ ጣቢያ ተጠቅሞ የቻይና መንግሥትን ፖለቲካዊ አጀንዳ በማራመድ የቻይና ተቃዋሚዎችን ዒላማ አድርጓል” ብለዋል።

    በ53 የዓለም አገራት ውስጥ ቢያንስ 100 እንደዚህ ዓይነት ጣቢያዎች እንደተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

    የመብት ተሟጋች ቡድኖች፤ የቻይና መንግሥት ውጭ አገር የሚገኙ የቻይና ተወላጆችን ለማስፈራራት እና ለመከታተል እነዚህን ጣቢያዎች ይጠቀማል የሚል ክስ ያሰማሉ።

    ጣቢያዎቹ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የዴሞክራሲ ደጋፊ አክቲቪስቶችን ለመለየት እንደሚውሉም ይናገራሉ።

    ቻይና ስፍራዎቹ ፖሊስ ጣቢያ ናቸው መባላቸውን ታስተባብላለች። እነዚህ “የአገልግሎት ጣቢያዎች” የሚሠሩት ውጭ አገር ለሚገኙ ቻይናውያን “አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ” እንደሆነም በመግለጽ ራሷን ተከላክላለች።

    ፍርድ ቤት የቀረበው ሉ ጂአንዋንግ፤ ከዚህ ዓይነቱ ጣቢያ ጋር በተገናኘ በተከፈቱበት ሕገ ወጥ የቻይና መንግሥት ወኪል ሆኖ መንቀሳቀስ እና ተያያዥ መረጃዎችን በማጥፋት ፍትሕን የማስተጓጎል ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

    የጥፋተኝነት ውሳኔው የተላለፈው የቻይና ሕገ ወጥ ወኪል በመሆን ክስ የተመሠረተባቸው የካሊፎርኒያ ገዢ ሥልጣን በለቀቁ በቀናት ልዩነት ነው።

    የኒው ዮርክ ፌደራል ፍርድ ቤት ውሳኔውን ከማስተላለፉ በፊት ለሳምንት ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቷል። ክስ የቀረበበት የኒው ዮርክ ከተማ ነዋሪ እስከ 30 ዓመት ድረስ ሊፈረድበት እንደሚችል ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

    አብሮት ተከስሶ የነበረው ቼን ጂንፒንግ የተባለ ግለሰብ ከፖሊስ ጣቢያው ጋር በተገናኘ በቀረበበት የቻይና መንግሥት ወኪል ሆኖ የመንቀሳቀስ ክስ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ላይ ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።

  8. ቻይና እና አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት እንዳለበት መስማማታቸው ተገለጸ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር

    የፎቶው ባለመብት, POOL / AFP via Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር ባደረጉት ውይይት “ሁለቱም ወገኖች የሆርሙዝ ወሽመጥ መከፈት እንዳለበት” መስማማታቸው ተገለጸ።

    ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ ላይ ትራምፕ ውይይቱን “መልካም ነበር” ብለው መግለጻቸው ተመልክቷል። በተጨማሪም “ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራት እንደማይገባ ተስማምተዋል” ተብሏል።

    የቻይና እና አሜሪካን የምጣኔ ሃብት ትስስር ለማጠናከር እንደሚተባበሩ ተገልጿል። ይህም የአሜሪካ ኩባንያዎችን ወደ ቻይና ገበያ ማስገባት እና በአሜሪካ የቻይናን ኢንቨስትመንት ማሳደግን ያካትታል ተብሏል።

    በውይይታቸው ላይ ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

    ፕሬዝዳንት ጂፒንግ ከአሜሪካ ነዳጅ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የዋይት ሀውስ መግለጫ ይጠቁማል።

    ሌላው በቤይጂንግ ውይይት የተነሳው ጉዳይ ፌንታኒል የተባለው መድኃኒት ወደ አሜሪካ እንዳይገባ መከላከል ነው።

  9. በኢራን ጉዳይ ላይ የሚነጋገረው ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የብሪክስ ስብሰባ ተጀመረ

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር)

    የፎቶው ባለመብት, MFA

    በኢራን የሚካሄደው ጦርነት ዋነኛ አጀንዳ ይሆንበታል በተባለው የብሪክስ አባል አገራት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) ተሳታፊ እንደሆኑ ተገለጸ።

    በባሕረ ሰላጤው የሚካሄደው ጦርነት ከጀመረ በኋላ የመጀመሪያው የሆነው ኢራን አባል የሆነችበት የብሪክስ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ሕንድ ኒው ዴልሂ ውስጥ ዛሬ ሐሙስ መካሄድ ጀምሯል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ዶ/ር ጌዲዮን “ሁሉንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመገንባት ትብብር እንደሚያስፈልግ” ተናግረዋል።

    አሁን ያለው ዓለም አቀፍ ቀውስ በአፋጣኝ መፍትሔ ካላገኘ አስከፊ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚያስከትል መናገራቸውም ተመልክቷል።

    ብሪክስ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም ፍትሐዊ እና ቋሚ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመዘርጋት ብሪክስ ሚና መጫወት አለበት ሲሉም አክለዋል።

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን አባል የሆነችበት የብሪክስ ስብስብን ከሁለት ዓመት በፊት የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተወክላ ስብሰባውን ትካፈላለች።

    ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ኢራን በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን አባስ አራግቺን ወደ ሕንድ የላከች ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ከስብሰባ ው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል አገራት አቻዎቻቸው ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

    በዚህ የብሪከስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳ ይሆንል ተብሏል።

    የስብሰባው አስተናጋጅ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር እንደተናገሩት ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች እንዲሁም በአባል አገራት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ላይ ውይይት ይደረጋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) በብሪክስ ስብሰባ ወቅት

    የፎቶው ባለመብት, MFA

    የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ብሪክስ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ከጤና እና ከፋይናንስ እንዲሁም እየናረ ካለው የነዳጅ፣ የምግብ እና የማዳበሪያ ዋጋ አንጻር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

    ይህ ስብሰባ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እየተየ ባለበት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ እየተጠናከሩ እና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ብሪክስ የበለጠ “የሚያረጋጋ እና ገንቢ ሚና” እንዲኖረው ይፈልጋሉ።

    በሕንድ ኒው ዴልሂ ዛሬ የተጀመረው የቡድኑ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ አስከ አርብ ድረስ የሚቀጥል ይሆንል።

    የስብሰባው ተሳታፊዎች

    የፎቶው ባለመብት, MFA

  10. የኢራን ጦርነት በዓለም ምጣኔ ሃብት ያስከተለው ቀውስ እንደሚያሰጋ ሕንድ አስታወቀች

    የብሪክስ ጉባዔ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኢራን ጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት ዓለም “ከፍተኛ ቀውስ” ውስጥ መግባቱ አሳሳቢ እንደሆነ ሕንድ ገለጸች።

    የብሪክስ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ ኒው ደልሂ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፤ ግጭቶች የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት እና የኃይል አቅርቦት ቀውስ ማስከተላቸው ተገልጿል።

    ኢትዮጵያ፣ ኢራን እና ሩሲያ አባል በሆኑበት የብሪክስ አገራት የሁለት ቀን የውይይት መድረክ ላይ የኢራን ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።

    የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሀማንያም ጃሺንካር “የተሰበሰብነው ዓለም ከፍተኛ ቀውስ በገጠመው ወቅት ነው። ግጭቶች፣ የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋቶች፣ የንግድ መሰናክሎች፣ ቴክኖሎጂ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እየለወጠ ነው” ብለዋል።

    “ታዳጊ ምጣኔ ሃብት ካላቸው አገራት ብዙ ይጠበቃል። ብሪክስ ነገሮችን ለማርገብ ሚናውን ይወጣል” ሲሉም አክለዋል።

  11. ኔታንያሁ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ዩኤኢን ‘በድብቅ’ መጎብኘታቸውን ተናገሩ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ ገብተው በነበረበት ወቅት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች “ምሥጢራዊ ጉዞ” ማድረጋቸውን እና ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር እንደተገናኙ ገለጹ።

    የኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ መካከል የተደረገው ንግግር “ታሪካዊ እድገት” ማምጣቱን ገልጿል።

    ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ባሉ በአጭር ሰዓት ውስጥ የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “እውነትን መሠረት ያላደረገ ነው” በሚል ኔታንያሁ አደረግኩት ያሉትን ጉብኝት አስተባብሏል።

    ሚኒስቴሩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት “ይፋዊ ባልሆኑ ስምምነቶች” ያልተመሠረተ ነው ሲል ጠንከር ያለ መግለጫ ሰጥቷል።

    ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በኤሚሬትስ ላይ በርካታ ዒላማዎችን የደበደበች ሲሆን፤ ቴህራን አገሪቱ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ባላት የቅርብ ቅንኙነት ትተቻለች።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው በኔታንያሁ እና በኤምሬትሱ ፕሬዝዳንት መካከል የተደረገው ንግግር በኦማን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው አል ዓይን ከተማ የተደረገ እና ለሰዓታት የዘለቀ ነው።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት የአገራቱን ግንኙነት በተለይም የመከላከያ አጋርነትን እንዳጠናከረ ይታመናል።

  12. ኢራናውያን ባለሥልጣናት ለብሪክስ ስብሰባ ወደ ሕንድ ተጓዙ

    የብሪክስ መሥራቾች ሰንደቅ ዓላማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባን ለመታደም የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲን ጨምሮ ኢራናውያን ባለሥልጣናት ወደ ኒው ደልሂ መሄዳቸው ተናገረ።

    የኢራን ባለሥልጣናት ከሕንድ አመራሮች እንደተገናኙም ተዘግቧል።

    ከነገ ሐሙስ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ውይይት የምትመራው ሕንድ ስትሆን የፊታችን መስከረም ላይ ስለሚካሄደው የብሪክስ አባል አገራት የመሪዎች ጉባዔ ማብራሪያም ትሰጣለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባግሂ እንደተናገሩት ቴህራን ከሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን ለማካሄድ አቅዳለች።

    ቃል አቀባዩ ለሕንድ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት እነዚህ ውይይቶች ለኢራን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ናቸው።

    አሜሪካ ኢራን ላይ ሌላ ዙር ጥቃት ልትከፍት የምትችልበት ዕድል ስለመኖሩ ከኢንዲያ ቱደይ ግሎባል ጋዜጣ ተጠይቀው “መከላከያ ኃይላችን ለማንኛውም ሁኔታ ዝግጁ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ። የኢራንን መሬት ለመርገጥ የሚዳፈር ማንኛውም አካል ይጸጸታል” በማለት መልሰዋል።

    ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኢንዶኔዢያ አባል የሆኑበት ስብስብ ነው።

  13. ጣልያን የጦር መርከቦችን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ልትልክ ነው

    የጦር መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, ISNA / AFP via Getty Images

    ጣልያን ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የሚደረስ ከሆነ ሁለት የጦር መርከቦችን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ እንደምትልክ አስታወቀች።

    ወደ ጦርነት ቀጣናው የሚሰማሩት እነዚህ የጦር መርከቦች ባሕር ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎችን በማሰስ የሚያመክኑ ናቸው።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ ጉዲዮ ክርዜቶ በጣሊያን ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች የሚላኩት የሕዝብ እንደራሴዎች ፈቃድ ከሰጡ ብቻ ነው።

    ይህ የሚሆነውም አሁን ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ሳይሆን “ሰላም የሚያሰፍን ዘላቂ፣ አስተማማኝ እና እውነተኛ” የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሲደረስ ነው ብለዋል።

    ከባሕር በታች ፈንጂ አነፍንፈው የሚያመክኑት መርከቦች ወደ ቀጣናው ለመድረስ ሳምንታት እንደሚወስድባቸው ገልጸው፤ አሁን ላይ ጣልያን መርከቦቹን በሜድትራኒያን ባሕር እና ቀይ ባሕር አቅራቢያ ለማሰማራት እያሰናዳች መሆኑን አመልክተዋል።

    ኢራን ጦርነቱ ከተነሳ አንስቶ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ቀውስ አስከትሏል።

    ነዳጅ እና ማዳበሪያን ጨምሮ የሸቀጦች ምርት ከመናሩ ባሻገር ቴህራን በወሽመጡ ፈንጂ ማጥመዷን አሜሪካ አስታውቃለች።

  14. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጉብኝት ቻይና ገቡ፤ የኢራን ጦርነት አንዱ አጀንዳቸው ነው

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቤይጂንግ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ የአሜሪካ ልዑካንን በመምራት በአስር ዓመት ውስጥ በቻይና ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው መሪ በመሆን ቤይጂንግ ገብተዋል።

    ለወራት ሲጠበቅ በነበረው በዚህ የፕሬዝዳንት ትራምፕ የቻይና ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ችግር በገጠመው የሁለቱ አገራት የንግድ ግንኙነት፣ በኢራን በሚካሄደው ጦርነት እና አሜሪካ ለታይዋን ስለምትሸጠው የጦር መሳሪያ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የኒቪዲያ ዋና ሥራ አስጻሚ የንሰን ሁዋንግ እና የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሃብት የሆነውን ኢላን መስክን ጨምሮ ከከፍተኛ የአሜሪካ የንግድ ልዑካን ጋር ወደ ቻይና ያቀኑት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደማቅ መስተንግዶ እንደሚጠበቃቸው ተዘግቧል።

    ትራምፕ ቤይጂንግ ከመድረሳቸው ከሰዓታት በፊት የቻይና እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት አንዳቸው በሌላኛቸው ምርት ላይ የናረ ታሪፍ ላለመጣል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቤይጂንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  15. ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡበትን ጦርነት ለማስቆም ቻይና እንደማታስፈልጋቸው ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡበትን ጦርነት ለማስቆም የቻይናን እርዳታ እንደማይፈልጉ ተናገሩ።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ለሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝት ወደ ቻይና ከማምራታቸው አስቀድሞ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ነው።

    ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር እያጠበቀች የመጣች ሲሆን በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል።

    ወደ ቤይጂንግ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት እየሄዱ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡበትን ጦርነት ለመፍታት የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ድጋፍ ያስፍጋል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም ነዳጅ ዘይት አቅርቦት እና ንግድ ተስተጓጉሏል።

    “ከኢራን ጋር ምንም ዓይነት እርዳታ ያስፍለጋል ብዬ አላስብም። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ፣ በሰላማዊ መንገድም ሆነ በሌላ እናሸንፋለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን በወሽመጡ ላይ ያላትን ቁጥጥር ያጠበቀች ሲሆን ከኢራቅ እና ከፓኪስታን ጋር ከቀጣናው ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዝ እንዲችሉ መስማማቷን ምንጮች ተናግረዋል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ምንጮች ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ ስምምነት ከኢራን ጋር ለመድረስ እየሞከሩ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ይህም ቴህራን በመተላለፊያው ላይ ያላትን ቁጥጥር የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።

    ማክሰኞ ዕለት የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ እና የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ቀጣናው በወሽመጡ በኩል በሚደረግ ጉዞ ወቅት ምንም ዓይነት ቀረጥ እንዳይከፈል መስማማታቸውን ተናግሮ ነበር።

    ከቴህራን ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላት ቻይና ከኢራን ነዳጅ ከሚገዙ ዋነኛ አገራት መካከል አንዷ ናት።

  16. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቬንዙዌላን ለመጠቅለል እያሰቡ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ አገሪቱን ‘51ኛ የአሜሪካ ግዛት’ አድርጎ የሚያሳይ ምስል አጋሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ የትስስር ገፅ ቬንዙዌላ በአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍና የሚያሳይ እና “51ኛ ግዛት” የሚል ጽሑፍ የያዘ ምስል አጋርተዋል።

    ይህ የፕሬዝዳንቱ ልጥፍ የመጣው አገሪቱን ለመጠቅለል እያሰቡ እንደሆነ ከገለፁ እና የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪገዝ ሃሳቡን ውድቅ ካደረጉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

    ሮድሪገዝ “የአገራችንን አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ነፃነት፣ የአገራችን ወንዶች እና ሴቶች ነፃ አገር እንጂ ቅኝ ተገዢ እንዳንሆን ሕይወታቸውን የከፈሉበትን የክብር ታሪካችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

    የጊዜያዊ ፕሬዝዳንቷ አስተያየት የተሰማው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ቬንዙዌላን የአሜሪካ 51ኛ ግዛት ለማድረግ እያሰቡ እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ ነው።

    የቬንዙዌላን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ከካራከስ መኖሪያቸው ተይዘው ባለፈው ታኅሳስ መጨረሻ ወደ አሜሪካ ለፍርድ እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ተከትሎ ትራምፕ ከአገሪቱ ጋር እየተግባቡ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ያጋሩት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Trump / Truth Social

  17. ፔንታጎን የኢራን ጦርነት ስያሜን ‘ኦፕሬሽን ስሌጅሐመር’ በሚል ለመቀየር እያሰበ መሆኑን ኤንቢሲ ዘገበ

    ቴህራን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ጦር ከኢራን ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ዘመቻው የሚቀጥል ከሆነ ስያሜውን ለመቀየር እያሰበ መሆኑን ኤንቢሲ ዘገበ።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱ በድጋሜ እንዲጀመር የሚፈቅዱ ከሆነ የዘመቻው ስያሜ “ኦፕሬሽን ስሌጅሐመር” ተብሎ ሊቀየር እንደሚችል ተናግረዋል።

    አሜሪካ ኢራን ላይ ወታደራዊ ዘመቻዋን የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ከእስራኤል አጋር በመሆን ስትጀምር “ኦፕሬሽን ኢፒክ ፊውሪ” ስትል ሰይማው ነበር።

    ለዘመቻው ኮንግረስ በ60 ቀናት ወስጥ ይሁንታውን ሊሰጥ ስላልቻለ ፔንታጎን በአዲስ ስያሜ ዳግም ጦርነቱን ለመጀመር እያሰበ መሆኑ ተገልጿል።

    የትራምፕ አስተደደር ኦፕሬሽን ኢፒክ ፊውሪ በይፋ ማብቃቱን ያስታወቀ ሲሆን በኢዝላማባድ አደራዳሪነት ከኢራን ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረገ ነው።

    ፔንታጎን ስለ ኢራን ጦርነት መግለጫ በሚሰጥበት ወቅት ‘ኦፕሬሽን ኢፒክ ፊውሪ’ እያለ የሚጠቀም ሲሆን አንድ የመስሪያ ቤቱ ባለሥልጣን የተኩስ አቁሙ ዋና ዋና ማጥቃቶችን ማስቆሙን ብቻ በመናገር ዘመቻው ቀጥሏል ብለዋል።

    ፔንታጎን በጉዳዩ ላይ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

    የኢራን ጦረነት ዳግም የሚጀመር ከሆነ በአዲስ ስያሜ እንደሚሆን ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

  18. ሊባኖስ በእስራኤል ጥቃት ሁለቱ የሕክምና ባለሙያዎች ጨምሮ 13 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀች

    ሊባኖስ ላይ ጥቃት ሲፈፀም

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በእስራኤል እና የሊባኖስ ታጣቂ ቡድን በሆነው ሄዝቦላህ መካከል ግጭትን ማቆም ያላስቻለው የሰላም ስምምነት መክሸፉን ተከትሎ በደቡባዊ ሊባኖስ በእስራኤል አየር ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን አገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገበ።

    እንደ ሊባኖስ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ከሆነ በምሽቱ በአንድ ቤት ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲገደሉ ሰባት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

    ማክሰኞ እለት የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በእስራኤል ጥቃት ሁለት የሕክምና ባለሙያዎች መገደላቸውን እና ሦስተኛ ባለሙያ ደግሞ መቁሰሉን አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር ሪፖርቶችን እየተመለከተ መሆኑን ተናግሯል።

    የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን በሕክምና ባለሙያዎቹ ግድያ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልፀው፤ በእስራኤል የቀጠለው ጥቃት መረጋጋትን ለመመለስ ያለውን ጥረት የሚያደናቅፍ ነው ብለዋል።

    የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር እስራኤል የሕክምና ባለሙያዎችን ሆን ብላ ዒላማ እያደረገች ነው ሲል ከስሷል።

    ሚኒስቴሩ በጦርነቱ 108 የሊባኖስ የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሰጪዎች እና የጤና ባለሙያዎች መገደላቸውን እና 140 እስራኤል ጥቃቶች በአንቡላንሶች እና የጤና ተቋማት ላይ መፈፀማቸውን አስታውቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ እና ሰሜናዊ እስራኤል ባሉ አካባቢዎች ላይ በድሮን ጥቃት መፈፀሙን ተናግሯል።

    ባለፉት ጥቂት ቀናት የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የሚፈጸመውን ጥቃት ጨምሯል።

    የእስራኤል እና ሊባኖስ ባለሥልጣናት ጦርነቱን ለማቆም ሐሙስ በዋሽንግተን ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  19. ትራምፕ የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም ማስቆም ከአሜሪካውን የኢኮኖሚ ፈተና ይበልጣል አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካውያን የፋይናንስ ችግር የኢራንን ጦርነትን ለማስቆም በሚያደርጉት የድርድር ውሳኔ ላይ ምክንያት አለመሆኑን ተናገሩ።

    ትራምፕ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ጋዜጠኞች አሜሪካውያን ጦርነቱን ተከትሎ እየደረሰባቸው ያለው የኢኮኖሚ ጫና ምን ያህል ከስምምነት እንዲደርሱ ግፊት እንደሚያደርግ ሲጠየቁ “ትንሽ እንኳን ተጽዕኖ” አያደርግም ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ቅድሚያ የሚሰጡት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ መሆኑን ተናግረው የአሜሪካውያን የፋይናንስ ችግር ጦርነቱን ከማቆም በሚያሳልፉት ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ተናግረዋል።

    የፕሬዚዳንቱን አስተያየት እንዲያብራሩ የተጠየቁት የዋይት ሐውስ ኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር ስቲቭን ቺዩንግ ትራምፕ “ዋነኛ ኃላፊነታቸው የአሜሪካኖች ሰላም እና ደህንነት ነው። ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይችልም፤ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ እስካሁን ይኖራቸው እና አሜሪካውያንን ያስፈራሩ ነበር” ብለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እና የዋጋ ግሽበት ታይቷል።

  20. ሳዑዲ አረቢያ በኢራን ጦርነት ወቅት ምስጢራዊ ጥቃቶችን መፈጸሟን ሮይተርስ ዘገበ

    የሳዑዲ አረቢያ ተዋጊ ጄት

    የፎቶው ባለመብት, Katsuhiko Tokunaga

    ሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት ይፋ ያልሆኑ በርካታ ጥቃቶችን ኢራን ላይ መፈጸሟን ሁለት ምዕራባውያን እና ሁለት የኢራን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ።

    ሳዑዲ አረቢያ የአየር ድብደባዎቹን የፈጸመችው ለኢራን ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ነው ተብሏል።

    የሳዑዲ ወታደራዊ እርምጃ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ሲሆን ኢራን ላይ በቀጥታ ጥቃት መፈጸሟ በይፋ የታወቀው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    የሳዑዲ አየር ኃይል ጥቃቱን የፈጸመው በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ መሆኑ ሁለት የምዕራባውያን ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ሳዑዲ ኢራን ለፈጸመቻቸው ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ድብደባዎቹን ማካሄዷን ጨምረው ተናግረዋል።

    ሮይተርስ ሳዑዲ አረቢያ ዒላማ ያደረገቻቸው የኢራን ስፍራዎች የትኞቹ እንደሆኑ ማረጋገጥ አልቻለም።

    የሳዑዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ስለጉዳዩ ተጠይቀው በቀጥታ አገራቸው ጥቃት ስለመፈጸሟ ከመናገር ተቆጥበዋል።

    ሮይተርስ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

    ሳዑዲ አረቢያ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ሲሆን ከዚህ ቀደም የዩኤስ ወታደራዊ ከለላ ላይ ትተማመን ነበር።

    ነገር ግን 10 ሳምንት በቆየው የኢራን ጦርነት ወቅት ለጥቃቶች የበለጠ ተጋላጭ መሆኗን አሳይቷል።

    የሳዑዲ ጥቃት በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት መስፋፋቱን አሳይቷል። አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. የጀመሩት ጦርነቱ ለሕዝብ ይፋ ባይደረግም በርካታ አገራትን ማሳተፉን አመላክቷል።

    ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢራን ስድስት የባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮኖች ጥቃት ፈጽማለች።

    በአሜሪካ ጦር ሠፈሮች፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ከመፈጸም አልፋ የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት የዓለም ንግድ እንዲስተጓጎል አድርጋለች።

    ሰኞ ዕለት ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ቴህራን ላይ ጥቃት ፈጽማለች። የሳዑዲ እና የኤሜሬትስ በጦርነቱ ውስጥ መሳተፍ የግጭቱ ትክክለኛ መልክ የተደበቀ መሆኑን አጋልጧል።

    ዩኤኢ ቴህራን ለድርጊቷ ተገቢውን ዋጋ እንድትከፍል የሚል ጠንካራ አቋም ያላት ሲሆን ውስን ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን ከኢራን ጋር አካሄዳለች።

    አንድ የሳዑዲ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ከኢራን ጋር ጦርነቱን የማርገብ ስምምነት ተደርሶ እንደሆን ተጠይቀው ሳይመልሱ ቀርተዋል።

    ነገር ግን “ሳዑዲ አረቢያ ለቀጣናው መረጋጋት፣ ደህንነት፣ ብልጽግና እና ለሕዘብ ደህንንት በሚል ውጥረትን በመቀነስ ላይ ያለንን የማያቋረጥ አቋም ላረጋግጥ እችላለሁ” ብለዋል።

    ለሮይተርስ መረጃውን የሰጡ የኢራን እና ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ሳዑዲ አረቢያ ጥቃት እንደምትፈጸም ቴህራን እንድታውቅ ተደርጓል ብለዋል።