ለፓኪስታን ጋዝ የጫነች የኳታር መርከብ በሆርሙዝ በኩል ማለፏ ተገለጸ
አሜሪካ ላቀረበችው የሰላም ዕቅድ የኢራንን ምላሽ እየጠበቀች ሳለ ለፓኪስታን የተፈጥሮ ጋዝ የጫነች የኳታር መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፏ ተገለፀ።
አል ካራይቲያት የተባለችው ይህች መርከብ ከኳታር ራስ ላደፋን ተነስታ ወደ ፓኪስታን ቃሲም ወደብ እያመራች መሆኗ ተገልጿል።
የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኳታር መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ሲያልፍ ይህ የመጀመርያው ነው።
ኳታር የተፈጥሮ ጋዙን አሜሪካን እና ኢራንን በማሸማገል ውስጥ ላለችው ለፓኪስታን የሸጠችው የሁለቱ አገራት መንግሥታት ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ነው ተብሏል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ኢራን የመርከቧን ጉዞ የፈቀደችው በፓኪስታን እና ኳታር ረገድ ያለውን መተማመን ለማጠንከር ነው ብለዋል።
ለሮይተርስ የዜና ወኪል አስተየየታቸውን የሰጡ ምንጮች በጋዝ እጥረት ክፉኛ የተጎዳችው ፓኪስታን፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የተወሰነ የተፈጥሮ ጋዝ የጫኑ መርከቦች እንዲያልፉ ንግግር እያደረገች ትገኛለች።
ኳታር ለፓኪስታን የተፈጥሮ ጋዝ ከሚያቀርቡ አገራት መካከል ቀዳሚዋ ስትሆን ኢራን ደግሞ በወሽመጡ በኩል መርከቡ እንዲያልፍ ለሁለቱ አገራት መንግሥታት ይሁንታዋን መስጠቷ ተገልጿል።
የናካሊት የመርከብ ትራንስፖርት ድርጅት ንብረት የሆነችው መርከቧ፣ የማርሻል ደሴቶችን ባንዲራ የምታውለበልብ ሲሆን 211,986 ኪዩቢክ ሜትር ነዳጅ የመጫን አቅም አላት።
ከአንድ ወር በፊት የኢራን አብዮታዊ ዘብ አል ዳዬን እና ራሼዳ የተሰኙ ሁለት የኳታር ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን እንዳያልፉ ከልክሏል።