ፈረንሳይ ዛሬ ለመካሄድ በታቀደው ሠልፍ ላይ ሁከትን ለመከላከል 70,000 ፖሊሶችን ልታሰማራ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ ቅዳሜ ዕለት በመላ አገሪቱ ለመካሄድ የታቀደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ሁከትን ለማስወገድ ወደ 70,000 የሚጠጉ ፖሊሶችን ልታሰማራ መሆኑን አስታወቀች።
ይህ እርምጃ የተወሰደው፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት በመቃወም በተደረጉ ሠልፎች ወቅት፣ ከበርካታ ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የከፋ የጎዳና ላይ ሁከት ከተከሰተ በኋላ ነው።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ላውረንት ኑኔዝ አርብ ዕለት እንደተናገሩት አሸባሪዎችን ለመከላከል ከመደበኛ የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ልዩ ኮማንዶዎች ይሰማራሉ።
በተጨማሪም “ግራ ዘመም” ቡድኖች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ለጥቃት ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመሩት እና የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትሮች በተሳተፉበት ስብሰባ ማብቂያ ላይ ኑኔዝ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “በሰላማዊ መንገድ ስለሚካሄድ የተቃውሞ ሠልፍ አይደለም እያወራን ያለነው” በማለት “ነገ [ቅዳሜ] እጅግ ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል፤ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃትም አንታገስም” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በነበረ የተቃውሞ ሠልፍ ወቅት ጥቁር ልብስ የለበሱና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ አንዳንድ በሁከት የተሳተፉ ቡድኖች፣ በፓሪስ፣ ማርሴይ እና በሌሎች ከተሞች መኪኖችንና ሕንፃዎችን ሲያቃጥሉ እንዲሁም የንግድ ተቋማትን ሲዘርፉ ታይተዋል።
በማዕከላዊዋ የፈረንሳይ ከተማ ሊሞዥ፣ ቅዳሜ ዕለት ሁከት ፈጣሪዎች ባስነሱት እሳት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውና ባማሩ ጌጣጌጦች የተዋበው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት በእሳት ወድሟል። እሳቱ እየተስፋፋ ሄዶ የሕንፃው የሰዓት ማማና ጣሪያ ፈርሰው እንዲወድቁ አድርጓል።
ሉቭርን፣ኦርሴ ሙዚየምን፣ ፒካሶ ሙዚየምን እና ግራንድ ፓሌን ጨምሮ ዋና ዋና ሙዚየሞች ቅዳሜ ዕለት ዝግ ይሆናሉ።
ከዓለም ቀዳሚ የዘመናዊ ጥበብ ትርኢቶች አንዱ የሆነው “አርት ባዝል” (Art Basel) አርብ ዕለት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የነበረ ቢሆንም፣ አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል ከሚል ስጋት የተነሳ ቅዳሜና እሁድ ዝግ ሆኖ ይቆያል።
በፓሪስ የሚገኙ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ለመከላከል ሲሉ ሳምንቱን ሙሉ መከላከያዎችን ሲገነቡ ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሁከት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ‘ፕላስ ደ ላ ሪፑብሊክ’ አቅራቢያ፣ አንድ ባንክ እና ሌሎች የንግድ ተቋማት ዘረፋን ለመከላከል ሲሉ መስኮቶቻቸውን በእንጨት ሰሌዳዎች ሸፍነዋል።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና መንግሥታቸው የፕሬዚዳንት ምርጫ ለመካሄድ ስድስት ወራት ብቻ ሲቀሩት በድንገት የተከሰተውን ይህንን ቀውስ ለመቆጣጠር እየታገሉ ይገኛሉ።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት የነበረውን ሁከት ተከትሎ መንግሥት “ሁኔታውን መቆጣጠር አቅቶት እንደነበር” አምኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images




















