በዩርዳኖስ በአንድ ቤተ ክርስትያን ለቀብር የተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ሰባት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩርዳኖስ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስትያን ቀብር ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
አርብ ዕለት በካራግ ግዛት ህሙድ በሚባል አካባቢ በምትገኝ ቤተክርስቲያን ላይ ታጣቂዎች ተኩስ በመክፈታቸው ቢያንስ 34 ሌሎች ሰዎች ቆስለዋል።
ማንነታቸውያልታወቁት ታጣቂዎች በመኪና ወደ ቤተክርስቲያኗ በመምጣት ለቀብር የተገኙ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍተው መሸሻቸው ታውቋል።
ጥቃቱን በሚመለከት ማንም ኃላፊነት አልወሰደም።
ካራክ በርካታ ሙስሊሞች በሚገኙባት ዮርዳኖስ ውስጥ የክርስትያን ማኅበረሰብ የሚኖርባት ግዛት ናት።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማዘን አል-ፋራያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የአገሪቱ ፖሊስ "የአክራሪዎች ቡድን" ሲሉ የገለጿቸውን ወንጀለኞች ለመያዝ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ በበኩላው "ካራክ ላይ ያነጣጠረውን የሽብር ተግባር የፈጸሙ እጅግ ከባድቅጣት ይጠብቃቸዋል" ብለዋል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ ባደረጉት መረጃ በጥቃቱ መገደላቸው የተረጋገጠው እስካሁን ሰባት ሰዎች ብቻ ናቸው። የመንግሥት ቃል አቀባይ መጀመርያ ላይ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን የሟቾችን ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ብሏል።
በካራክ በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ሰዎች በሚታከሙበት ሆስፒታል ዋይታ እና ለቅሶ የሚሰማ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የፖሊስ ጥበቃም አለ።
በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እና የተጎዱባቸው ሰዎች “መንግሥት በአሸባሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አልቻለም” በሚል በከፍተኛ ቁጣ ውስጥ መሆናቸው ተነግሯል።
ወደ ሆስፒታሉ የሚወስዱ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን መኪኖችንም ማቆም የተፈቀደው ራቅ ባለ ስፍራ ነው።
የደህንነት ሁኔታው የተጠናከረው ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ የተጎዱትን ሰዎች ለመጎብኘት እንደሚመጡ ከተገለጸ በኋላ መሆኑም ተሰምቷል።
የሊባኖስፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የተፈጸመው "አሰቃቂ የሽብር ጥቃት"፣ "የሞትንና ለሟች የሚያዝኑ ሰዎችን ክብር የጣሰ እንዲሁም ከማንኛውም ሃይማኖታዊና ሰብአዊ እሴቶች ጋር የሚቃረን ነው" ሲሉ መናገራቸውን የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።




















