እናት እና ልጅን ጨምሮ ከ30 በላይ ሰዎች የተገደሉበት የመተከል ጥቃት እና ያሳደረው ስጋት

ግልገል በለስ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Gilgel Beles Town Administration

የምስሉ መግለጫ, የመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማክሰኞ ግንቦት 4/2018 ዓ.ም. በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከ30 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ይህ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት እና ጉዳት የደረሰባቸው ጥቃት የተፈጸመው ከክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ መንገደኞችን ባሳፈሩ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ነው።

በጥቃቱ እስከ 35 የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው፣ ከ50 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና የሟች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከአካባቢው ተመርጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ ጥቃቱን በቅርብ ጊዜ ከተፈፀሙ ሁሉ "አስከፊው ነው" ብለውታል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ወደ መተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ እየተጓዙ በነበሩ አራት ተሽከርካሪዎች ላይ በዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች መካከል ላይ አይሲድ ቀበሌ ወይም አፍሪካ እርሻ ልማት በተባለ ስፍራ ላይ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።

ታጣቂዎች ጥቃቱን የደረሰው በተለምዶ 'ቅጥቅጥ' በሚባሉ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ሲጓዙ የነበሩ ተሳፋሪዎችን አስወርደው ዘረፋ ከፈጸሙ በኋላ የተኩስ እሩምታ ከፍተው ግድያውን መፈጸማቸውን አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ መካከል ዳይመንድ ዮሐንስ የተባለ የአራት ዓመት ሕፃን እና ፀሐይነሽ አሚሳ የተባለች እናቱ እንደሚገኙበት ቤተሰባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በ20ዎቹ መጨረሻ የምትገኘው እናት ፀሐይነሽ ሳዑዲ አረቢያ ለስምንት ዓመታት ሠርታ የተለመለሰች እና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራች የአሶሳ ከተማ ነዋሪ መሆኗን ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

ፀሐይነሽ ህመም ላይ ያሉ እናቷን ለመጠየቅ ሕጻን ልጇን ይዛ ወደ ቡለን ወረዳ እየተጓዘች በነበረችበት ጊዜ ነው ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት ከነ ልጇ የተገደለችው።

"ከዚህ ቀደም አባቷን ሳታይ ስለሞቱባት፤ እናቷን 'ሳላያት እንዳትሞት' በማለት ከ13 ዓመታት በኋላ እናቷን ልታይ እየሄደች ነበር" ሲሉ አንድ የቤተሰብ አባል እናት ከልጇ ጋር እንደወጣች የቀረችበትን አጋጣሚ አስረድተዋል።

የቤተሰብ አጋዥ እና ወንድሞቿን የምታስተምር እንደሆነች የተናገሩት ቤተሰቡ፤ "ያላለቀሰ ሕዝብ የለም" በማለት የእናት እና ልጅ ግድያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ሐዘን እና ድንጋጤን መፍጠሩን ገልጸዋል።

ሚስቱ እና ልጁ በታጣቂዎች የተገደሉበት በባለቤቷ በከፍተኛ ሐዘን ምክንያት በመረበሹ ራሱን እና ሌሎችን እንዳይጎዳ በሚል "ታስሮ" እንደሚገኝ የቤተሰብ አባሉ ተናግረዋል።

የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ ተቃጥለዋል የተባሉ ተሽከርካሪዎች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁሉም ነዋሪዎች እና እማኞች የሟቾች በስፍራው ያለው ሁኔታ ሟቾችን ወደ መኖሪያ አካባቢ ለማጓጓዝ አመቺ ባለመሆኑ ቀብራቸው ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ቤተሰቦቻው እና ዘመዶቻቸው ሳይገኙ መፈጸሙን ገልጸዋል።

በአካባቢው ባለው የፀጥታ ስጋት ምክንያት "አልተረጋጋም፤ መስመሩ አያሳልፍም" በማለት ያለውን ሁኔታ የገለፁ አንድ ነዋሪ የሟቾቹ ቀብር ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ "በአንድ ላይ" መፈጸሙን ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪ በጥቃቱ ከተገደሉት ከ30 በላይ ሰዎች በተጨማሪ 57 የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውን ከጥቃቱ ከተረፈ የቤተሰባቸው አባል ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፓዊ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ነመራ ኢቲቻ በጥቃቱ የቆሰሉ ሁለት ሰዎች በሆስፒታላቸው ድንገተኛ ሕክምና እንደተደረገላቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሁለት ዘመዶቻቸው ከጥቃቱ መትረፋቸውን የተናገሩ የግልገል በለስ ነዋሪ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈውን ጥቃት ሲገልጹ "ምንም ምክንያት የለውም። መዝረፍ እና መግደል ነው ዓላማቸው" ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እና እማኞች ጥቃቱን የፈጸሙት ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው የነበሩ እና "አቶ መኩሪያው ቢሳ" በተባለ ግለሰብ የሚመሩ የጉሙዝ ታጣቂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ በበኩላቸው የጥቃቱ ፈጻሚዎች ራሳቸውን "የጉሙዝ አንድነት ኃይል" ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ሳይሆኑ አይቀሩም ብለዋል።

የሕዝብ እንደራሴው እንደሚሉት ታጣቂዎቹ "ወደ ሰላም ተመልሰው ነበረ። አሁን የራሳቸውን ጦር አደራጅተው ወደ ሱዳንም ገባ ወጣ የሚሉ [ናቸው]" ብለዋል።

ይህ ቡድን ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም በግልገል በለስ ከተማ የሚገኝ ማረሚያ ቤትን ለመስበር የሞከረ ታጣቂ ኃይል መሆኑም ተነግሯል።

ታጣቂዎቹ "አባሎቻቸውን ለማስመለጥ" ሞከሩት በተባለበት የማረሚያ ቤት ጥቃት ከመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ከሳምንታት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅት በመተከል ዞን ስጋት ዳግም ማንጃበቡን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፤ አንድ ነዋሪ የማክሰኞው ጥቃት ያሳደረውን መረበሽ ሲገልጹ "[ሕዝቡ] በጣም ስጋት ውስጥ ነው።...ሠራተኞች ሁሉ ጥለው ወጥተው ፖሊስ ነበር ቢሮዎችን ሲጠብቅ የነበረው። ሥራ ላይ አልነበሩም። ስጋት አለ በጣም" ብለዋል።

መተከል ዳግም ወደ ስጋት መግባቷን የተናገሩት የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶ/ር መብራቱ፤ ከጥቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በመስመሩ በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ማለፋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የፀጥታው ሁኔታ አሁን ከሞላ ጎደል ተሻሽሏል በሚል እጀባዎች እየቀሩ፤ መኪናዎች ያለ ወታደራዊ አጀብ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ አለ።"

በቅርቡ ባለሀብቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አስታውሰዋል።

የሕዝቡ ደኅንነት እና ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን የጠቆሙ አንድ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው "የተደራጁ" ያሏቸው ኃይሎች አካባቢውን መረጋጋት እንደነሱት ገልፀዋል።

"ጉባ እና ግልገል [በለስ] መሀል ላይ ብዙ የተደራጁ ሽፍቶች አሉ" በማለት መንግሥት የተጠናከረ ጥበቃ እንዲያደርግ አቤቱታ አቅርበዋል።

"በቀጣይ መኪና መግባት አይችልም። አሁንም መንገዱ ዝግ ነው። ጥንቃቄ የሚያስፈልግ ነው" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ በርካታ ሰዎች የተገደሉበት እና የቆሰሉበትን የታጣቂዎችን ጥቃት በተመለከተ ከክልሉ እና ከዞኑ ባለሥልጣናት አስተያየት ለማግኘት ለቀናት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ጉዳዩን ብናስረዳቸውም የክልሉ መንግሥትን አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

____

*ለዚህ ዘገባ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል።