የቻይናው ኤአይ ባዮሎጂካል ጦር መሣሪያ እንዴት መስራት እንደሚችሉ ለተመራማሪዎች ማብራራቱ ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቻይና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ፈጣሪ የሆነው 'ሙንሾት' ተመራማሪዎች፣ ሁለት ዝነኛ የኪሚ ሞዴሎቻቸውን ባይሎጂካዊ ጦር መሣሪያ ማዘጋጀት እና ግድያዎች እንዴት መፈጸም እንደሚቻል እንዲነግራቸው ጠይቀው በማሳመናቸው ዳግም ፍተሻ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን ደኅንነት የሚፈትሸው 'ማይንድጋርድ'፣ 'ኪሚ ኬ2.6' እና 'ኬ3 ስዋርም' የተባሉት ሥርዓቶች የተቀመጡትን የደኅንነት ገደቦች ማለፍ እንደሚችሉ በሐምሌ ወር ማሳወቁን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህ የተከሰተው "ጄይል ብሬኪንግ" በተባለ የፍተሻ ሂደት ወቅት ሲሆን ተመራማሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሳሪያዎች የጥበቃ መንገዶችን ችላ ይሉ እንደሆነ ለማየት ተከታታይ ውስብስብ መመሪያዎችን ተጠቅመዋል።

ማይንድጋርድ፣ ኪሚ በተመራማሪዎቹ ስለቀረቡለት ርዕሰ ጉዳዮች ከመወያየት ሊያግዳቸው ይገባ ነበር ብሏል።

ሙንሾት ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ "የተሻለ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ግንባታን ለማካሄድ ቁልፍ" በመሆኑ ከሦስተኛ ወገን የቀረበለትን አስተያየት በደስታ መቀበሉን ገልጿል።

ኩባንያው ስለግኝቶቹ ከሚንጋርድ ጋር እየተወያየ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የማይንድጋርድ መስራች የሆነው ፒተር ጋርጋሃን ለቢቢሲ ቴክላይፍ፣ ኪም ኬ2.6 እና ኬ3 ስዋርም ያገኛቸው አሳሳቢ መሆናቸውን ተናግሯል።

"ጄይልብሬክ መስራት ከጀመረ በኋላ ስለማንኛውም ርዕስ ያወራል፣ እንዲሁም ስለሌሎች ጎጂ ርዕሶችም ጭምር ምክሮችን በነፃነት ያቀርባል፣ ፈጠራም ይኖረዋል" ብሏል።

ጄይልብሬክ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ክስተቶች ላይ ከታዩት የተለየ አደጋን ያስከትላል።

እነዚህ እንደ ኦፕንኤአይ፣ ሜታ እና አንትሮፒክ ባሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች የተገነቡት ኤጀንቶች አንዳንድ የኦንላየን አገልግሎቶችን ሲመዘብሩ ተስተውለዋል።

የጄይልብሬክ ሂደቶች ውስብስብ ሲሆኑ ብዙ ጊዜና ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ቢሆኑም፣ አንዳንድ ባለሙያዎች መረጃ መንታፊዎች እና ሌሎች አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸው አካላት ጉዳት ለማድረስ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ይሰጋሉ።

አንትሮፒክ በቅርቡ እንዳስታወቀው፣ የባዮሎጂካል የጦር መሳሪያዎችን መስራት ሊደግፍ የሚችል "ጎጂ እንቅስቃሴ"ን የኤአይ ሞዴሉን ለመጠቀም የሚደረገውን ሙከራ ለይቶ ማስቆሙን ገልጿል።

ማይንድጋርድ፣ ኪሚ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የሰጣቸው መልሶች ውጤታማ መሆናቸውን አላረጋገጠም።

ነገር ግን የመከላከያ መንገዶቹ በጥያቄ ውስጥ ያሉት ሞዴሎች ከተጠቃሚዎች ጋር በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዳያደርጉ መከላከል ነበረባቸው ሲል ተከራክሯል።

ጋራጋሃን ማይንድጋርድ የሙንሾት ስርዓቶች ችግር እንዳለባቸው ማሳወቁን ገልጾ፣ የኩባንያው ሞዴሎች የጥበቃ መንገዶችን እንዴት ችላ እንዲሉ እንዳደረጋቸው ቁልፍ ዝርዝሮችን ግን ይፋ አለማድረጋቸውን ተናግረዋል።