ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእንግሊዝ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ለአዕምሮ ሕክምና እንደተላኩ ሪፖርት አመለከተ
በእንግሊዝ የአዕምሮ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚላኩ ሕፃናት ቁጥር በዚህ ዓመት በ10 በመቶ ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱን ሪፖርት አመለከተ።
ከአውሮፓውያኑ 2024 እስከ 2025 ያለውን ጊዜ የሸፈነው ሪፖርት እንዳመለከተው ቁጥሩ ከ2018 እስከ 2019 ከነበረው ወደ እጥፍ ገደማ ጨምሯል።
ጭንቀት ከተጠቀሱት የአዕምሮ ጤና እክሎች ውስጥ በብዛት የታየ ሲሆን የአዕምሮ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ከተላኩት የሕፃናት ቁጥር 16 በመቶውን ይይዛል።
የኦቲዝም ተጠቂ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ኬዞች ቁጥርም በአንድ ዓመት ውስጥ በ50 በመቶ ጨምሮ ከ96 ሺህ በላይ ደርሷል።
እንደ 'ኤዲኤችዲ' እና ያለፈቃድ የሚያጋጥም የአካል እንቅስቃሴ እና ድምጽ ማውጣት ወይም 'ቶርቲስ ሲንድረም' ያሉ ሌሎች የነርቭ እና የአንጎል እድገት ችግሮችም በሩብ ያህል ጨምረዋል።
የሕፃናት ኮሚሽነር ዳሜ ሬቸል ዲ ሳውዛ ከ2024 እስከ 2025 ያለውን ጊዜ በሚሸፍነው የሕፃናት እና ታዳጊዎች የአዕምሮ ጤና አገልግሎት ዓመታዊ ሪፖርታቸው የቁጥሩ መጨመር የጤና አገልግሎት ለማግኘት የሚደረገውን ጥበቃ እንደሚያረዝመው አስጠንቅቀዋል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከሲሶ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት እስካሁን እየተጠባበቁ ሲሆን ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑት እርዳታ ለማግኘት ከሁለት ዓመት በላይ እየተጠባበቁ ነው። ይህ ቁጥር በቀደመው ዓመት ከነበረው 44 ሺህ ጨምሯል።
ከ2024 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ኦቲዝም ወይም የነርቭ እና የአንጎል እድገት ችግር እንዳለባቸው ከተጠረጠሩ አምስት ሕፃናት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የቻሉት ከአንድ የሚያንሱት ብቻ እንደሆኑም ሪፖርቱ አመልክቷል።
እነዚህ ሕፃናት አገልግሎቱን ለማግኘት በአማካይ ለአንድ ዓመት ገደማ ጠብቀዋል።
"ቁጥሩ ከፍተኛ ነው" ያሉት ዳሜ ራቸል፣ ምንም እንኳን የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም ያለው ፍላጎት ያለው የጤና ሥርዓት እና የገንዘብ አቅም ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ስለሚጨምር የአዕምሮ ጤና ሕክምና ለማግኘት ሊያጋጥም የሚችለውን ተግዳሮት ችላ ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህንን ለመለወጥ የሚያስችል ዘዴ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።
"ሕፃናት በትምህርት ቤታቸው እና በማኅበረሰቡ ውስጥ እርዳታ ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ በጤና፣ በትምህርት እና በማኅበራዊ እንክብካቤ የተቀናጀ አገልግሎት በመፍጠር ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ግብረሰናይ ድርጅቱ 'ያንግማይንድስ' በበኩሉ በተለይ ጥቁሮች እና በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም በኦቲዝም ወይም በሌላ የነርቭ እና የአንጎል እድገት ችግር የተጠረጠሩ ሕፃናት እና ታዳጊዎች እያጋጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶች እና አገልግሎት ለማግኘት የሚደረገው ጥበቃ እጅግ እንዳሳሰበው ገልጿል።
አሃዞቹ እንደሚያሳዩት የጤና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሕክምና የሚላኩ ጥቁር እና እስያዊ ሕፃናት ቁጥር ጥቂት ሲሆን፣ ሲላኩ ግን ከባድ ጭንቀት ወይም ቀውስ ውስጥ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ወደ ሕፃናት እና ታዳጊዎች የአእምሮ ጤና አገልግሎት ከሚላኩ አራት ጥቁር ሕፃናት አንዳቸው ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙም ሪፖርቱ አመልክቷል። አሃዙ ከነጭ ሕጻናት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ነው።
ይህም በቁጥር አናሳ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀደም ብለው ለምን እርዳታ አያገኙም የሚል ጥያቄን አስነስቷል።