ቀጥታ, ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ ከሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማሸማገል ወደ ጠየቀችው ሞስኮ አቀኑ

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትራቸው ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ በተጓዳኝ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ይወያያሉ ተብሏል። በጉባዔው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ሩሲያ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲነጋገሩ መድረክ ለማመቻቸት መጠየቋ ይታወሳል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዮርዳኖስ ባለፈው ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በሶሪያ ላይ የአፀፋ እርምጃ ወሰደች

    ዮርዳኖስ ባለፈው ሳምንት ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በሶሪያ ላይ የአፀፋ እርምጃ ወሰደች።

    ባለፈው ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ቀብር ላይ በተፈፀመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

    የዮርዳኖስ ጦር በሶሪያ “የሽብር ድርጅቶች” በተባሉት ዒላማዎች ላይ የአፀፋ እርምጃ ወስዷል።

    የሶሪያ የጤና ባለሥልጣናት ጥቃቱ በተፈፀመበት ዳራ ግዛት ሴቶች፣ ሕፃናትን እና አረጋዊያንን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

    ዮርዳኖስ ዝርዝር መጃ ሳትሰጥ የጦር አውሮፕላኖቿ “በርካታ አሸባሪዎችን” መግደላቸውን እና ማቁሰላቸውን አስታውቃለች።

    አገሪቱ ጥቃቱን ስትፈፅም ከሶሪያ ባመንግሥት ጋር መተባበሯን ገልፃለች። ይሁን እንጂ ሶሪያ የሰኞው ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ እንዳውቅ አልተደረገም ብላለች።

    ይህ ጥቃት የተፈፀመው ባለፈው አርብ በዮርዳኖስ ካራክ አካባቢ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈፀመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ከተገደሉ እና 34 ሰዎች ደግሞ ከቆሰሉ በኋላ ነው።

    ሶሪያ ለተፈፀመባት ጥቃት ከዮርዳኖስ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር መዝጋቷን አስታውቃለች።

    የጥቃቱን ሙሉ ሁኔታ ለማረጋገጥም ምርመራ መጀመሩን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

  2. የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ሞስኮ ተጓዙ

    የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ወደ ሞስኮ ማቅናታቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትራቸው ገለጹ።

    ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በየዓመቱ የምታካሂደው ጉባዔ ሦስተኛው ዙር ረቡዕ እና ሐሙስ ጥቅምት 18 እና 19/2019 ዓ. ም. በዋና ከተማዋ ውስጥ ይደረጋል።

    የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ እንዳመለከቱት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጋር የተጓዙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በጉባዔው ላይ ከመሳተፋቸው በተጨማሪ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ።

    በዚህ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

    በቅርቡ ሕንድ ውስጥ በተካሄደው የብሪክስ አባል አገራት ስብሰባ ወቅት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባዔው እንዲሳተፉ ያቀረቡላቸውን ጥሪ መቀበላቸው ተገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሳምንታት በፊት የሩሲያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር አሊሞቭ አገራቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የአሸማጋይነት ሚና ለመጫወት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸው ይታወሳል።

    ሚኒስትሩ ለአንድ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ አገራት ፈቃደኞች ከሆኑ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት ንግግር እንዲያካሂዱ መድረክ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆናቸውን እና ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዕድሉን እንደሚጠቀሙበት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው ነበር።

    አሊሞቭ የአገራቸው “የረዥም ጊዜ ታማኝ አጋሮች” ባሏቸው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ለሩሲያ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

    በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውዝግብ በተካረረበት ጊዜ የአገራቱ ወዳጅ የሆነችው ሩሲያ ሁለቱም ከግጭት በመቆጠብ የመተማመን እርምጃዎችን እንዲያጠናክሩ እና በንግግር ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ ቀደም ሲል ጥሪ አቅርባለች።

  3. ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በዩክሬኗ ከተማ ያሸማገሉት የተኩስ አቁም ተጀመረ

    በሩሲያ ቁጥጥር ሥር በሆነችው ኦለሽኪ ከተማ በአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የተኩስ አቁም ተጀመረ።

    የተኩስ አቁሙ የሰብአዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ እና ንጹኃንን ከአካባቢው ለማውጣት ያለመ ነው።

    የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ለሰብአዊ እርዳታ ዝግጅት ሲል ወደ ከተማዋ መተኮስ ማቆሙን አስታውቋል።

    ኦለሽኪ ሩሲያ እ.አ.አ የካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ወረራ ስትጀምር በመጀመሪያዎቹ ቀናት በሞስኮ እጅ ወድቃለች።

    በጦር ግንባር ላይ የምትገኘው ኦለሽኪ ከተማ በጦርነቱ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን፤ የምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች እጥረት ገጥሟታል።

    የተኩስ አቁሙ መጀመሩን የዩክሬን ባለሥልጣናት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

    የከተማዋ ነዋሪዎች በተፋላሚ ኃይሎች መሀል ተይዘው መውጫ አጥተው ቆይተዋል።

    ኦለሽኪ ከጦርነቱ በፊት የ24 ሺህ ሰዎች መኖሪያ የነበረች ሲሆን፤ ዩክሬን አሁን የቀሩት ነዋሪዎች 200 ሕፃናትን ጨምሮ 6 ሺህ እንደሆኑ ትናገራለች።

    ዋይት ሀውስ ባለፈው ሳምንት ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በከተማዋ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማሸማገላቸውን አስታውቋል።

    "ወታደራዊ ያልሆኑ የሁለቱም አገራት ሲቪል መሪዎች የኦለሽኪ ነዋሪዎችን በቤታቸው በመጎብኘት እና የሚያስፈልጋቸው እርዳታ መጠንን ለመወሰን በጋራ ይሠራሉ” ሲል ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

    የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት በፖለቲካ እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው ቢሆኑም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ለተከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት ግን ይንቀሳቀሳሉ።

  4. ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ እና ቱርክ የቀጣናውን ደኅንነት “ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት” ለማስጠበቅ መስማማታቸው ተገለጸ

    የኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴህራን በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

    የኢራን ከፍተኛ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ ሞሼን ራይዚ “ቀጣናዊ ደኅንነት ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት መረጋገጥ አለበት” የሚል ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና ኢራንን እያደራደሩ ያሉት የፓኪስታን ጦር ኃይሎች አዛዥ አሲም ሙኒር፣ የሳዑዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሰልማን እና የቱርክ የደኅንነት ኃላፊ ኢብራሒም ካሊን በቴህራኑ የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተዋል።

    ሞሼን ራይዚ ለኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ እስራኤል ከደቡብ ሊባኖስ፣ ደቡብ ሶሪያ፣ ጋዛ፣ ዌስት ባንክ እና ዮርዳኖስ ወንቅ መውጣት እንዳለባት የውይይቱ ተሳታፊዎች ተስማምተዋል።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺም በውይይቱ ተገኝተዋል።

    የኢራን ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት፤ የፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በቴህራን መገኘታቸው “የአሜሪካ ማስፈራሪያ ውጤታማ እንዳልሆነ እንደሚያሳይ” ገልጿል።

    ውይይቱ ቀጣናዊ አንድነትን ለማረጋገጥ “ተጨባጭ ጅማሮ” እንደሚሆን ተስፋ እንዳለውም አስታውቋል።

    የኢራን፣ ሳዑዲ፣ ቱርክ እና ፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴህራን እንደሚወያዩ ካስታወቁ በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እንዳይባባስ ማድረግ “ወሳኝ ነው” ብለዋል።

  5. ኢራን እና ፓኪስታንን ጨምሮ የአራት አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴህራን በጋራ እየመከሩ ነው

    የኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ከፍተኛ ሹማምንት በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቴህራን ንግግር ጀመሩ።

    አሜሪካ እና ኢራንን እያደራደሩ ያሉት የፓኪስታን ጦር ኃይሎች አዛዥ አሲም ሙኒር፣ የሳዑዲ አረቢያ የመከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሰልማን እና የቱርክ የደኅንነት አለቃ ኢብራሂም ካሊን በቴህራን የጋራ ምክክሩ ላይ ተገኝተዋል።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እና ከፍተኛ የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ፀሐፊ ሞሸን ራዚያ የኢራንን ልዑክ ወክለው በስብሰባው ከተገኙት መሀል ናቸው።

    ሳዑዲ አረቢያ ከስብሰባው ቀደም ብላ ባወጣችው መግለጫ የምክክሩ ግብ ግጭት እንዳይባባስ ማድረግ እና ለስምምነት መንገድ መጥረግ ነው ብላለች።

    ሳዑዲ፣ ፓኪስታን እና ቱርክ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ “የመካ ስምምነት” የተባለ የመከላከያ እና ደኅንነት አጋርነት ፈርመዋል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እንዳይባባስ ማድረግ “ወሳኝ ነው” ብለዋል።

    ዋና ፀሐፊው በካይሮ በሰጡት መግለጫ እየጨመረ ስለመጣው የአሜሪካ ዛቻ እና ከኢራን ጋር ሊኖር ስለሚችል ስምምነት በተመለከተ፤ በኢራን እና በገልፍ አገራት ሊቀሰቀሱ የሚችሉ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃቶችን “በየትኛውም ዋጋ” መከላከል ያስፈልጋል ሲሉ አስምረዋል።

    ጉቴሬዝ ይህን ያሉት የሳዑዲ፣ ቱርክ እና ፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢራን ለመነጋገር ቀን ከቆረጡ በኋላ ነው።

  6. በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለኢቦላ ሕክምና ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ነርስ ተገደሉ

    በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለኢቦላ ሕክምና ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ነርስ በደረሰባቸው ጥቃት ሲገደሉ፤ አንድ ሌላ የሕክምና ባለሙያ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    በሰሜን ምሥራቅ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ምልክት መታየቱ ጥቆማ ከተሰጠ በኋላ ነበር ወደ አካባቢው የተጓዙት።

    ሁለቱ የሕክምና ባለሙያዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው “ውሃ በመበከል ኢቦላ ቫይረስን እያሰራጩ ነው” ባሏቸው የአካባቢው ወጣቶች መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ራድዮ ኦካፒ ዘግቧል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ጥቃቱን አውግዟል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ጥቃቱን አውግዘው “የጤና ባለሙያዎች ደኅንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ ሥራቸውን ማከናወን መቻል አለባቸው” ብለዋል።

    ኡጋንዳ የኢቦላ ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በሚል ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመለሱ ዜጎቿ ለ21 ቀናት ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደሚደረግአስታውቃለች።

    በዴሞክራቲክኮንጎ ታሪክ እጅግ የከፋ የሆነው ኢቦላ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ4,800 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ወረርሽኙ ወደ ሌሎች አገራት የተዛመተ ሲሆን ወደ 10,000 ሰዎች ተይዘዋል።

  7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኦሮሚያ ክልል በምዕመናን ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፤ በቀድሞው የኦሮሚያ ክልል አደረጃጀት በአርሲ ዞን ሥር በሚገኙ ወረዳዎች የደረሰውን ጥቃት “በጽኑ እንደሚያወግዝ” አስታወቀ።

    ጥቅምት 10 እና 14 ቀን 2019 ዓ. ም.፤ በመርቲ ወረዳ፣ አንጋዳ ቀበሌ፣ ጎራ ሲሊንጎ 14 ምዕመናን እና በሸርካ ወረዳ፣ ጠሬታ ጮሌ ቢርቦ 46 ምዕመናን “ግፍን በተሞላ ጭካኔ” መገደላቸውን ገልጿል።

    ቅዳሜ ጥቅምት 14/2019 ዓ. ም. በሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት "46 ሰዎች" በአካባቢው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን "በአንድ ጉድጓድ" መቀበራቸውን ሁለት ነዋሪዎች፣ ቀብሩ የተፈጸመበት ቤተ ክርስቲያን እና የወረዳው የቤተ ክርስቲያን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን በፌስቡክ ገጹ ላይ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ጠቅሶ፤ የ20 ምዕመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን አስታውቋል።

    ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች “ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው” ሆስፒታል መግባታቸውን ከአካባቢው አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ሪፖርት እንደደረሰው አመልክቷል። በዚህም የተሰማውን “ከፍተኛ ሐዘን” ገልጿል።

    በአርሲ አገረ ስብከት እና በሌሎችም አካባቢዎች “ኦርቶዶክሳውያን ንጹኃን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ተከታታይነት ባለው ሁኔታ፣ ያለማቋረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ” መጥቷል ሲልም አትቷል።

    የንጹኃን ግድያ እንዲቆምም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት “ኢ-ሰብዓዊ የሆነውን ተግባር በይፋ እንዲያወግዙ” ጠይቋል።

    አክሎም “በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና በነጻነት የማምለክ መብትን እንዲያስከብሩልን” ሲል ጠይቋል።

    ድርጊቱን የፈጸሙትን “ወንጀለኞች ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ በኋላ እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ” እንዲሰጥ ሲኖዶሱ አሳስቧል።

    ድርጊቱን “በሰብአዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፣ የሃይማኖት ነፃነትና በሕይወት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የጣሰ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕገ ሰብእና የወጣ፣ ተከባብሮ የመኖር ሀገራዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት” ሲልም አውግዞታል።

    በተጨማሪም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር “እንዲወያይ” መወሰኑም ተገልጿል።

    ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታትም “ጥናት የሚያደርጉ አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ እንዲሰየም” መመሪያ መሰጠቱም ተመልክቷል።

    የፀጥታ አካላት ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ “አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉ” እንዲሁም “አደጋዎችን ማስቀረት የሚያስችል ሥራ እንዲሠሩ” የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ አሳስቧል።

  8. የእስራኤል ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት የማድረስ ዕቅድ እንደሌለ ተገለጸ

    የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት እስራኤል ካትዝ በአገራቸው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት የመሰንዘር ዕቅድ እንደሌለ ገለጹ።

    ኢራን ላይ አዲስ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድን በተመለከተ በእስራኤል ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል መባሉን “መሠረተ ቢስ” ሲሉ አጣጥለዋል።

    ቻናል 12 የተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ ማንነታቸውን ያልጠቀሳቸውን ምንጮች ጠቅሶ ትናንት እሑድ እንደዘገበው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መሪ ኢያል ዛሚር መካከለር አለመግባባት ተፈጥሯል።

    አለመግባባቱ አዲስ ትዕዛዝን የተመለከተ እንደሆነ ቢገለጽም ዝርዝር መረጃ አልወጣም። ኔታንያሁ ዘገባውን ሐሰተኛ ሲሉ አጣጥለዋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የዘገባው ዓላማ በምርጫው ዋዜማ የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር የሚያስተላልፈው ውሳኔ ላይ ጥርጣሬ ማጫር ነው።

    የቴሌቭዥን ጣቢያው ዘገባ እንደሚያሳየው ወታደራዊ መሪው ስብስባ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። የተላለፈላቸውን ትዕዛዝ ከመፈጸማቸው በፊት ከፖለቲካ አመራሮች የሕግ ማዕቀፍን በተመለከተ መረጃ ተሰጥቷቸዋል።

    ጥያቄ የተነሳበት ትዕዛዝ ይዘትን በተመለከተ ዘገባው ዝርዝር መረጃ አልሰጠም። ሆኖም ግን በወታደሮች ዘንድ ጦርነት ለፖለቲካዊ ዓላማ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

  9. ኡጋንዳ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚመለሱ ዜጎቿ ለ21 ቀናት ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አዘዘች

    የኢቦላ ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የጣለቻቸውን ገደቦች እያጠበቀች ያለችው ኡጋንዳ፣ ከጎረቤት አገር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመለሱ ዜጎቿ ለ21 ቀናት ለይቶ ማቆያ (ኳረንቲን) እንዲገቡ እንደሚደረግ አስታወቀች።

    በዴሞክራቲክ ኮንጎ ታሪክ እጅግ የከፋ የሆነው ኢቦላ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ግንቦት አንስቶ ከ4,800 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ወረርሽኙም ወደ ሌሎች አገራት ተዛምቷል።

    የኡጋንዳ ጤና ሚኒስቴር አዲሱን እርምጃ ይፋ ያደረገው፣ በአገሪቱ በኩል አቋርጠው የተጓዙ ሁለት ሰዎች በኬንያ እና በናይጄሪያ የኢቦላ ምርመራ ተደርጎላቸው በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡ ጥያቄ ካስነሳ በኋላ ነው።

    ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ከኬንያዊው የኢቦላ ታማሚ ጋር ንክኪ ስላላቸው ክትትል ሥር የነበሩ 60 ሰዎች በሙሉ ነጻ በመሆናቸው መሰናበታቸውን አስታውቋል።

    ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተጉዘው የነበሩ መንገደኞች በኡጋንዳ በኩል አቋርጠው እንዲያልፉ እንደማይፈቀድላቸው ተነግሯል።

    ሚኒስቴሩ አክሎም ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተጉዘው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኡጋንዳውያ “በራሳቸው ወጪ 21 ቀናትን ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚያሳልፉ” ገልጿል።

    ጤና ሚኒስቴሩ “በኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና በሁሉም የየብስ ድንበር ማቋረጫዎች ላይ የሚደረገውን የተጓዦች ፍተሻ የተጠናከረ ሲሆን በተመረጡ የመንገድ ፍተሻ ኬላዎችም ምርመራው ይደረጋል” ብሏል።

    የኡጋንዳ የጤና ሚኒስትር ክሪስ ባርዮሙንሲ ከቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚመጡ ወሳኝ ተጓዦች ብቻ እንዲገቡ እንደሚፈቀድላቸው ተናግረዋል። እነርሱም ቢሆን “ጥብቅ የሕዝብ የጤና እርምጃዎች” እንደሚወሰድባቸው አብራርተዋል።

  10. የሰርቢያው አንጋፋ መሪ ቩቺች በተማሪዎች የአመጽ እንቅስቃሴ በመሸነፋቸው የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን እየገለፁ ነው

    ሰርቢያን ለረጅም ጊዜ የመሩት አሌክሳንደር ቩቺች የተማሪዎችን የተቃውሞ ንቅናቄ ተከትሎ በድንገተኛ የፓርላማ ምርጫ መሸነፋቸውን አምነው ተቀበሉ።

    “የመጨረሻውን ውጤት እስካሁን ባይደርሰንም በምርጫው መሸነፋችን ግን ግልጽ ነው” ሲሉ የቀኝ ዘመሙ ሕዝበኛ መሪ እሁድ ምሽት ሽንፈታቸውን ተቀብለዋል።

    የሰርቢያ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ያደረጋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤቶች፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የመራጮች ተሳትፎ እንደነበረ አመልክተዋል።

    ቩቺች ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሰርቢያ በርካታ አካባቢዎች ሰዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልፀዋል።

    ቩቺች ድንገተኛ ምርጫ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት በኖቪ ሳድ ከተማ የባቡር ጣቢያ ጣሪያ ወድቆ 16 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በአገሪቱ ለሁለት ዓመታት የቀጠሉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከተካሄዱ በኋላ ነው።

    የባቡር ጣቢያው አደጋ በሰርቢያ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና እና የቸልተኝነት ምልክት ተደርጎ በመታየቱ ነው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው።

    የሰርቢያ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ መሪው ቩቺች፣ ለሁለት የፕሬዚደንትነት ዘመናት ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር የማይችሉ በመሆኑ፣ እአአ ከ2017 ጀምሮ ወደለቀቁት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመመለስ ዓላማ ነበራቸው።

    የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ የተመሰረተው እና ምርጫውን ያሸነፈው የ’ስቱደንት ሊስት’ መሪ ኢሊያ ስርዳኖቪች “ነጻ መንግሥት ይመሰረታል” ሲሉ ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግረዋል።

    በመላው ሰርቢያ የሚገኙ የመንግሥት ተቃዋሚ መራጮችን ያሰባሰበው የፀረ ሙስና ንቅናቄ “አገሪቱን ከግፍና ከጭቆ እና አገዛዝ ነጻ ያወጣል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

  11. ሁቲዎች በሳዑዲ አየር ማረፊያ እና ነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹ

    የየመን ሁቲዎች ዛሬ ሰኞ የሪያድ አየር ማረፊያ እና በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙ የድፍድፍ ነዳጅ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታወቁ።

    በየመን የሚገኘው እና በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በበኩሉ ሁቲዎች ዛሬ ጠዋት ወደ ሪያድ የተተኮሰን ሚሳዔል ማክሸፉን እና በየመን ሰንዓ ውስጥ ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን አስታውቋል።

    ሁቲዎች በሳዑዲ መዲና የሚገኘውን የኪንግ ካሊድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ባሊስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፋቸውን እና ጥቃቱ “ዒላማውንም በትክክል መምታቱን” የቡድኑ ቃል አቀባይ ከሁቲ ጋር ግንኙነት ላለው አል ማሲራህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

    ሁቲዎች አየር ማረፊያው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገለጹት በጥቅምት መጀመሪያ በተፈጸመበት እና 13 ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት ምክንያት ያቆመውን አገልግሎት ትናንት እሁድ በከፊል መጀመሩን ባስታወቀ ማግሥት ነው።

    ታጣቂ ቡድኑ ከአየር መንገዱ በተጨማሪ በአገሪቱ የሚገኙ የድፍድፍ ነዳጅ ማውጫ ጣቢያዎችን በድሮን መምታቱን ገልጿል። ሳዑዲ በአየር ማረፊያው ላይም ሆነ በነዳጅ ማውጫዎች ላይ ተፈጽመዋል ስለተባሉን ጥቃቶች እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

    የሳዑዲ ሲቪል መከላከያ በዋና ከተማው ሪያድ ውስጥ አደጋ ሊኖር እንደሚችል የሚገልጽ ማስታወቂያ አውጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ኋላ ላይም ስጋቱ ማለፉን አስታውቋል።

    ሁቲዎች ጥቃት ማድረሳቸውን ያስታወቁት በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን መዲና ሰንዓ የሚገኙ ሁለት የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን ካስታወቀ በኋላ ነው። ከእነዚህ ማስወንጨፊያዎች አንዱ ጥምር ጦር እንዳከሸፈው የገለጸውን እና ወደ ሪያድ የተተኮሰውን ባለስቲክ ሚሳዔል ለማስወንጨፍ ጥቅም ላይ የዋለ እንደነበር ተገልጿል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ሳዑዲ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማጠናከራቸውን ተከትሎ አሜሪካ በአገሪቱ የሚገኙ የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ያልሆኑ ባልደረቦች እና ቤተሰቦቻቸው ከሳዑዲ እንዲወጡ ማዘዟ ይታወሳል።

  12. ጋቦን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ ከስምንት ወራት በኋላ አነሳች

    በማዕከላዊ አፍሪካ የምትገኘው ጋቦን ሰፊ ተቃውሞ እና ትችት አስከትሎባት የነበረውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጣለችውን እገዳ ከስምንት ወራት በኋላ ማንሳቷን አስታወቀች።

    መንግሥት በበይነ መረብ የሚለቀቁ ይዘቶች ግጭትን እያባባሱ እና በአገሪቱ ውስጥ ክፍፍልን እያስፋፉ ነው በሚል ነበር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ እገዳውን የጣለው።

    ይህ እርምጃ ወደ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ጋቦን ውስጥ መነጋገሪያ ሆኗ ቆይቷል። በአገሪቱ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብ እና ኢንስታግራም በተለይ በወጣቶች ዘንድ ለንግድም ሆነ ለመዝናኛ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ነበሩ።

    እገዳው ከተጣለ በኋላ በርካቶቹ የአገሪቱ ዜጎች ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ቪፒኤን የተባለውን በተዘዋዋሪ አገልግሎቱን የማግኛ መንገድን መጠቀም ጀምረው ነበር።

    እገዳው የተጣለው የጋቦን ፕሬዝዳንት ብሪስ ኦሊጊ ንጉኤማ ከተመረጡ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ማኅበራዊ ተቃውሞ ካጋጠመ በኋላ ነበር።

    በወቅቱ መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ እና አመቺ ያልሆነ የሥራ ሁኔታን እንደምክንያት በማቅረብ አድማ አድርገው ነበር።

    የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በመንግሥት የተጣለው የማኅበራዊ ሚዲያው እገዳ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ነው ሲሉ ወቅሰው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ንጉዌማ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ነበር ያሸነፉት። ምርጫው የተካሄደው ፕሬዝዳንቱ የመሩት መፈንቅለ መንግሥት ከሃምሳ ዓመታት በላይ የዘለቀውን የቦንጎ ቤተሰብ አገዛዝን ካበቃ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር።

    በወቅቱ ንጉዌማ በነዳጅ እና በደን ሀብት የበለጸገችውን ትንሿ ጋቦንን ለማሻሻል ቃል ገብተው ነበር።

  13. ለምርጫ አንድ ቀን የቀራቸው የእስራኤሉ መሪ ኔታንያሁ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም አውድመናል አሉ

    ነገ ማክሰኞ ፓርላሜንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፣ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር የማውደሙ ሥራ 90 በመቶው መጠናቀቁን እና የቀረው 10 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ ኔታንያሁን ምረጡ” ሲሉ ለእስራኤላውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ለሦስት ዓመት ከዘለቀው የቀጣናው ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ማክሰኞ የሚካሄደው የእስራኤል ምርጫ እጅግ ተጠባቂ ሆኗል። አርብ ዕለት የወጣ የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳ እንዳመለከተው ከሆነ በአገሪቱ መንግሥት የመሠረተው ጥምረት እና ዋነኛ ተቃዋሚዎችን የያዘው ቡድን አንገት ለአንገት ተናንቀዋል።

    ከግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ ሲሆን፤ በውጭ አገራት የነበሩ 70 ሺህ ገደማ የአገሪቱ ዜጎች ለዚሁ ምርጫ ሲሉ ወደ እስራኤል ገብተዋል።

    ምርጫ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ትናንት እሁድ ለእስራኤሉ ቻናል 14 የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ መጠይቅ የሰጡት ኔታንያሁ፣ የምርጫ ተቀናቃኞቻቸው የኢራንን ኒውክሌር የማውደምን ሥራ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ብቃት እንደሌላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    "እኛ የሥራውን 90 በመቶ አጠናቅቀናል፤ 10 በመቶ ብቻ ቀርቷል። ይህንን ማን ሊያደርገው ይችላል? አይዘንኮት እና የሙስሊም ወንድማማቾች? በፍጹም፣ ይህንን ማድረግ የምችለው እኔ ብቻ ነኝ” ብለዋል።

    ከቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋዲ አይዘንኮት ጋር ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው የመጨረሻ ቀናት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን ጉዳይ በድጋሚ የቅስቀሳቸው ዋነኛ አጀንዳ አድርገውታል።

    ኔታኒያሁ በትናንትናው ዕለትም በቴል አቪቭ ላይ የኒውክሌር ፍንዳታ ሲደርስ የሚያሳይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምሥል በኤክስ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል። ከምሥሉ ጋርም ኢራን ለእስራኤል “የኅልውና ስጋት” መሆኗን የሚገልጽ የአንድ ቀኝ ዘመም እስራኤላዊ የፖለቲካ ተንታኝ ጽሑፍን አያይዘዋል።

    ተፎካካሪያቸው ጋዲ በበኩላቸው፣ ኔታንያሁ የመራጮችን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ከኢራን የሚመነጭን ስጋት መጠቀሚያ እያደረጉ ነው ሲሉ ከስሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢራን ጋር ለተደረገው ጦርነት ራሳቸው ያስቀመጧቸውን ግቦች ማሳካል አለመቻላቸውንም ተናግረዋል።

    በዚህ ተጠባቂ ምርጫ ከኔታንያሁ ጎን የተሰለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም በበኩላቸው በድጋሚ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። አሜሪካ እና እስራኤል ካለፈው ዓመት የካቲት አንስቶ ኢራን ላይ በጋራ ያካሄዷቸውን ወታደራዊ ዘመቻዎች ያስታወሱት ትራምፕ፣ “አብረን የጀመርነውን ሥራ እንድናጠናቅቅ” እስራኤላውያን መራጮች ለኔታንያሁ ድምፃቸውን ስጡ ሲሉ ጠይቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ፣ እርሳቸው እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው እና በተለያዩ ወታደራዊ ዘመቻዎች የጋራ ድሎችን እንደተቀዳጁ ገልጸዋል።

    በ2017 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል የኒውክሌር ተቋማት ላይ በፈጸሙት ድብደባ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዳትሆን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።