የቀድሞ የኳታር አሚር ሼክ ሐማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
ለ18 ዓመታት ኳታርን የመሩት እና የአሁኑ የአገሪቱ መሪ አባት የሆኑት የቀድሞው አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ በ74 ዓመታቸው ሕይወታቸው ማለፉን የኳታር መንግሥት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቀድሞው መሪ ሕልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
የዘመናዊት ኳታር አርክቴክት ተብለው የሚታወቁት የቀድሞው መሪ ሕይወታቸው ያለፈው ዛሬ እሁድ እንደሆነ የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የቀድሞው መሪ አገሪቱን በመሩበት ከአውሮፓውያኑ 1995 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ኳታር ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት አስመዝግባለች።
አነስተኛ በርሃማ አገር የነበረችው ኳታር ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሁም ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የማሳደር እንቅስቃሴ የጀመረችው በሼክ ሐማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ የሥልጣን ዘመን እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
በእነዚህ ዓመታት ኳታር በባሕረ ሰላጤው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና መውጣት ችላለች። ኳታር የአረብ አብዮት “አረብ ስፕሪንግ” ተብሎ የሚታወቀውን የአረብ አገራት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ስትደግፍ የነበረ ሲሆን በሶሪያ እና ሊቢያም ከአማጺያን ጎን ነበረች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ መገናኛ ብዙኃን የሆነው አልጀዚራም የተቋቋመው በቀድሞው መሪ የሥልጣን ዘመን ነው።
በሥልጣን ዘመናቸው ቋሚ ሕገ መንግሥት እንዲኖር ያደረጉ ሲሆን የአካባቢ ምርጫም ተካሂዷል። ኳታር የ2022 ዓለም ዋንጫን የማዘጋጀት ዕድል ያገኘችው በእርሳቸው የመሪነት ዘመን ነው።
ነጻ አስተሳሰብ የነበራቸው የቀድሞው መሪ፤ ብዙ ጊዜ ከአረብ ጎረቤቶቻቸው እና ምዕራባውያን አጋሮች ጋር ግጭት ውስጥ ይገቡ ነበር።
የወታደራዊ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ብሪታኒያ ውስጥ ሲሆን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ወደ መሪነት ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በሠራዊት አዛዥነት እና በመከላከያ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
ሼክ ሐማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ከ18 ዓመት የሥልጣን ዘመን በኋላ በ61 ዓመታቸው ሥልጣናቸውን ለልጃቸው አስረክበዋል።
የቀድሞው አሚር በዚህ መልኩ ከሥልጣናቸው መውረዳቸው፤ መሪዎች እስከ ሞት ድረስ ሥልጣን ላይ በሚቆዩበት የባሕረ ሰላጤው ፖለቲካ የተለመደ አልነበረም።
የቀድሞውን መሪ ሕልፈት ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ አራት የሐዘን ቀናት የታወጀ ሲሆን ከነገ ሰኞ እስከሚቀጥለው ሳምንት እሁድ ድረስ የመንግሥት ተቋማት እንደሚዘጉ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአረብኛ ቋንቋ በፌስቡክ ባጋሩት ጽሑፍ፤ በአሚሩ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
የብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ትርጉም እንደሚያሳየው “ሼክ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል ታኒ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማስፈን፣ ለውይይትና ለድርድር መሠረት በመጣል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጥበበኛ መሪ እንደነበሩ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጽፈዋል።
ለኢትዮጵያ “ትኩረት ይሰጡ” እንደነበር ያነሱት ዐቢይ፤ የቀድሞው መሪ የኢትዮጵያ ጉብኝት “ለሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነትና ለተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች መሠረት የጣለ እንደነበር” መግለጻቸው ተዘግቧል።