ሳዑዲ አረቢያ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን መቅረጽ እና ማጋራት እንደማይቻል አስጠነቀቀች
የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚሳዔሎች እና ድሮኖች ጥቃቶችን ማክሸፍን የሚመለከቱ መረጃዎችን መቅረጽ፣ ማጋራት ወይም ማሰራጨት ሕጋዊ ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ አስጠነቀቀች።
በተጨማሪም፣ የከሸፉ ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች ወይም የእነዚህ መሣሪያዎች ስብርባሪዎች ያረፉባቸውን ቦታዎች መቅረጽ ወይም ስለእነዚህ ቦታዎች መረጃ ማሰራጨትም በዚህ ማስጠንቀቂያ ውስጥ እንደሚካተት ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን በሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የነዳጅ እና ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
በዚህም ግዙፉ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ኩባንያ የአራምኮ ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ በሪያድ የሚገኝ የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዒላማ ሆኗል።
በቅርቡ ባገረሸው የየመን ግጭት የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር ዳርቻ እና በባብ ኤል-ማንደብ አቅራቢያ የሚገኙ ስልታዊ ቦታዎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል ቦታዎቹን ለማስለቀቅ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
“ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን ስለመመከት እንዲሁም ስለሚመቱባቸው ቦታዎች መረጃን መቅረጽ፣ መለጠፍ ወይም ማጋራት ለሕግ ተጠያቂነት ይዳርጋል” ሲል የሳዑዲ አገር ውስጥ ሚኒስቴሩ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ላይ ገልጿል።
መግለጫው በአየር ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመመከት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ከተጎዱ አካባቢዎች ጋር የተያያዙ ምስሎችን፣ ቪዲዮዎችን ወይም ሌሎች መረጃዎችን ማሰራጨት ላይ ያሉ ገደቦችን አጽንኦት ሰጥቶታል።
ይህንን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች ላይ ስለሚጣለው ቅጣት ሚኒስቴሩ ምንም አላለም።
ማስጠንቀቂያው የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃትን እንዲሁም የማክሸፍ ጥረትን ባለመቅረጽ እና ባለማሰራጨት ላይ የተጣለውን ገደብ ማኅበረሰቡ እንዲያከብር ጥሪ አቅርቧል።