ትራምፕ በኢራን ላይ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተናገሩ
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓርብ ዕለት አሜሪካ በኢራን ላይ ሌላ ወታደራዊ ዘመቻ ልታካሂድ እንደምትችል ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት የኢራን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን ለመያዝ በተቃረበበት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ባለበት ወቅት ነው።
ትራምፕ በፍሎሪዳ በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ “ሌላ ትንሽ ‘ኢፒክ ፊውሪ’ ልናካሂድ እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።
“ኢፒክ ፊውሪ” የአሜሪካ ጦር በኢራን ጦርነት ለሚያካሄደው ዘመቻ የተሰጠው ስም ነው። ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ስለ ዘመቻው ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።
ትራምፕ ቀደም ሲል ጦርነቱን በፍጥነት ማስቆም እንደሚቻል ቢናገሩም፣ ዋሽንግተን ፈጣን መቋጫ መፈለግ ወይስ ግጭቱ ቀስ በቀስ እንዲቆም መፍቀድ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ስለ ጦርነቱ ዓላማና የጊዜ ሰሌዳ የተለያዩ አቋሞችን ሲያቀርቡ የቆዩት ትራምፕ፣ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር “ጦርነቱ በአንድ መንገድ ወይም በሌላው በቅርቡ ያበቃል” ብለዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ትራምፕ አሜሪካ ከአንድ ሳምንት በኋላ በምታካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት በኢራን ላይ ጥቃት እንደማትፈጽም ተናግረው ነበር።
አሜሪካና እስራኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በጋራ በመሆን ኢራንን ሲያጠቁ ቴህራን በምላሹ በእስራኤልና የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች በሚገኙባቸው የባህረ ሰላጤ አገራት ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
የኢራን ባለሥልጣናት ጦርነቱ እንደገና የሚቀሰቀስ ከሆነ ቴህራን ይበልጥ ሰፊ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
ሁለት ከፍተኛ የኢራን የደህንነት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ አሜሪካና እስራኤል እንደገና ጥቃት ከፈጸሙ ቴህራን በባህረ ሰላጤው ውቅያኖስ ስር የሚገኙ የኢንተርኔት ኬብሎችን ለማጥቃት ዝርዝር ዕቅድ አዘጋጅታለች።