ኪም ጆንግ ኡን ለ12 ዓመታት ሥራ ላይ ሳይውል በቆየው ድልድይ በኩል ወደ ቻይና ገቡ
የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን በቅርቡ በተከፈተው አዲስ ድልድይ አማካኝነት ቻይና መድረሳቸውን የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘገበ።
የዜና ወኪሉ ስማቸውን ያልገለጻቸው የደቡብ ኮሪያ ምንጭ “ኪም ጆንግ ኡን በአዲሱ የያሉ ወንዝ ድልድይ አማካኝነት ወደ ቻይናዋ ዳንዶንግ ከተማ ገብተዋል” ማለታቸውን ጠቅሷል።
አራት መኪኖችን ማሳለፍ የሚችለው ይህ ድልድይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ቢጠናቀቅም፣ በሰሜን ኮሪያ በኩል የመንገድና የጉምሩክ ተቋማት ባለመሟላታቸው ለ12 ዓመታት ሥራ ላይ ሳይውል ቆይቷል።
ድልድዩ ከሳምንት ገደማ በፊት በይፋ የተከፈተ ሲሆን፣ ይህም በጎረቤት አገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር የተወሰደ ጉልህ እርምጃ ተብሎ ተቆጥሯል።
ቻይና የሰሜን ኮሪያ ትልቋ የንግድ አጋር ስትሆን፣ ለተገለለችውና የኒውክሌር መሣሪያ ላላት አገር ዋነኛ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ድጋፍ ምንጭ ነች።
ቤጂንግም ሆነ ፒዮንግያንግ የኪም ጉብኝትን በይፋ አላረጋገጡም።
ኪም የቻይናውን ጠቅላይ ሚኒስትር ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዜና ወኪል እንደዘገበው፣ ኪም ጆንግ ኡን ከቅዳሜው ጉብኝት በኋላ ወደ ሰሜን ኮሪያ ይመለሳሉ።
ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደገለጹት፣ ከሰኞ ጀምሮ በሚካሄደው ከፍተኛ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ስብሰባ በፊት ኪም ወደ ቤይጂንግ የማምራታቸው ዕድል ዝቅተኛ ነው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ስለ ጉዳዩ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።
ቻይናና ሰሜን ኮሪያ በዚህ ወር መጀመሪያ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን አዲሱን የያሉ ወንዝ ድልድይ በይፋ ከፍተዋል።