መውጫ ማጣት

በሌላ አገር ጦርነት ውስጥ ተያዘው መወጫ ያጡ አፍሪካውያን ምርኮኞች

ተጨማሪ ለማግኘት ወደታች ይውረዱ

የቀድሞ የኮንጎ-ብራዛቪል ወታደራዊ ተማሪ የሆነው ለድ ቤቨርሊ የተወሰኑ ጣቶች ያጣውን የተጎዳ እጁን በጥንቃቄ ይዟል።

በምሥራቅ ዩክሬን በሚገኝ የጦር ምርኮኞች ሆስፒታል ውስጥ ተቀምጧል።

በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የሚሳተፉ አፍሪካውያን ቁጥር መጨመሩን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የቢቢሲ ቡድን መጋቢት መባቻ ላይ ሲጎበኘው በማቆያው ውስጥ ሦስት ወራት አሳልፏል።

ከዩክሬን የተገኘው አሐዝ እንደሚያሳየው አምና ከተያዙ የጦር ምርኮኞች መካከል ከስምንቱ አንዱ ከአፍሪካ ነው። ሩሲያ አሏት ተብሎ ከሚገመተው ከ27,000 የሚበልጡ የውጭ አገራት ወታደሮች መካከል 10% የሚሆኑት አፍሪካውያን እንደሆኑ ዩክሬን ታምናለች።

ቤቨርሊ ጥርት ባለ ሩሲያኛ ስለደረሰበት ጉዳት “ውጊያ እያደረግን ሳለ በከፍተኛ ቅዝቃዜ ሳቢያ የሰውነት መሸማቀቅ ደረሰብኝ። በቁጥጥር ሥር ስውል የእጅ ጓንት አልነበረኝም” በማለት ይገልጻል።

"በእግራችን እየሄድን ነበር። እጅግ በጣም ይቀዘቅዝ ነበር።"

"ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የሰውነት መሸማቀቅ ገጠመኝ" ይላል።

ከሰባት ዓመት በፊት ወጣት ወታደር ሳለ ከባሕር ኃይል ተቋም ትምህርት እንዲያገኝ ወደ ሩሲያ ተላከ። ከዚያም ትዳር መሥርቶ ሴት ልጅ ወለደ። የገንዘብ ችግር ሲገጥመው አደንዛዥ ዕፅ መሸጥ ጀመረ። በዚህም ምክንያት ታሰረ። በእስር ላይ ሳለ በጦርነቱ ከተሳተፈ ነጻ እንደሚመጣ ተነገረው።

“ወንጀል መፈጸሜን ለማረም ሩሲያን ለማገልገል ወሰንኩ። ስለዚህም ወደ ጦር ግንባር ላኩኝ” ሲል ነግሮኛል።

ዩክሬን የጦር ምርኮኞች በጥሩ ሁኔታ መያዛቸውን ለማሳየት በምታደርገው ጥረት አማካኝነት በየወሩ በመጨረሻው ሐሙስ ላይ የጦር ምርኮኞች ማቆያዎች ለመገናኛ ብዙኃን ጉብኝት ክፍት ይደረጋሉ።

ቤቨርሊ አያያዙን በተመለከተ ቅሬታ እንደሌለው ይናገራል። ሐኪሞች ደግ ናቸው፤ የካምፕ ሕይወት ወታደር የመሆን ያህል አታካች ነው።

በአውሮፓውያኑ 26/2025፤ በዩክሬን በሚገኝ የጦር ምርኮኞች ማዕከል፤ ጌቲ ኢሜጅስ

ሆኖም በቃለ ምልልሱ ወቅት ከጦርነቱ ገለልተኛ ናት ያላት አገሩ እና ቤተሰቡ ይቅር እንዲሉት ይጠይቃል። ከምንም በላይ የሚፈልገው ግጭቱ እንዲያቆም ነው።

ሁለቱም ወገኖች ብዙ አጥተዋል። አይቼዋለሁ። አስቀያሚ ነው።

ለድ ቤቨርሊ
በዩክሬን የጦር ምርኮኛ

የጦር ምርኮኞቹ

ሊያነጋግሩን ፈቃደኛ የሆኑት የጦር ምርኮኞች በአጠቃላይ በተለያየ መንገድ ነው ግጭቱን የተቀላቀሉት። አብዛኞቹ ወደ ሩሲያ ተመልሰው ደመወዛቸውን መውሰድ ይፈልጋሉ። ማንኛቸውም ወደ ጦር ግንባር መመለስ አይሹም።

መጀመሪያ እዚያ ስንደርስ ደስ የሚል የሾርባ ሽታ ተቀበለን። የወታደር መለያ የለበሱ ምርኮኞች በዝምታ ለምሳ ተሰልፈው አገኘን።

ጉብኝት እያደረጉ ካሉት ጋዜጠኞች ጋር መነጋገር ይፈልጉ እንደሆነ ይጠየቃሉ። አንዳንድ አፍሪካውያን ከመኝታ ክፍሎች ጀርባ ክብ ሠርተው ቆመዋል። ብቸኞቹ ዳር ዳይ ይታያሉ። ጨዋታ ወዳጆች እርስ በርስ እየተቃለዱ ነው። አንዳንዶች ከዕይታ ይሸሻሉ።

ከጎብኚዎቹ መካከል ቢቢሲ እንደሚገኝበት ሲሰማ አንድ ሰው ፈቃደኛ ሆኖ ወደፊት ወጣ። ስሙ ሪቻርድ ካኑ እንደሆነ ተናገረ። የሄደው ከሴራ ሊዮን መዲና ፍሪታውን ነው።

ታሪኩን የሚናገረው ወላጆቹ እና ሦስት ልጆቹ አለመሞቱን እንዲያውቁ ብሎ መሆኑን ይገልጻል።

43 ዓመቱ ነው። በዩክሬን ከተያዘ ሁለት ዓመቱ ሲሆን፣ በካምፑ ውስጥ ደግሞ ለአንድ ዓመት ቆይቷል።

እንደ ቤቨርሊ ሁሉ ወታደር ነበር። ነገር ግን ጥበቃ ለመሆን ሲስማማ ራሱን ጦር ሜዳ እንደሚያገኝ አላወቀም።

ለ17 ዓመታት በሴራ ሊዮን ጦር ውስጥ አገልግሏል። በወር 100 ዶላር ይከፈለው ነበር። በጦሩ መካከል ያለው ውጥረት ለቅቆ እንዲወጣ አስገደደው። የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሲል በቱሪስት ቪዛ አውሮፓ ሄደ።

“ልጄ ዶክተር መሆን ትፈልጋለች። ሕልሟን እንድታሳካ ለዩኒቨርስቲ ልከፍልላት ይገባል” ሲል ነግሮኛል።

ከሩሲያ ውጭ ቪዛ የጠየቀባቸው አገራት በአጠቃላይ አልተቀበሉትም። በ2024 እዚያ ሲደርስ ከሥራ አፋላጊዎች ጋር ተገናኘ። በአንድ ዓመት ኮንትራን 15 ሺህ ዶላር እንደሚከፈለው ሲሰማ ማመን አልቻለም። በወር 2,000 ዶላር እንደሚሰጠው ተነገረው። ሩሲያኛ ባይችልም ወደ ደቡባዊቷ ሮስቶቭኦን-ዶን ከተማ ተወሰደ። ከዩክሬን የውጊያ አውድማ 200 ኪሎ ሜትር ይርቃል።

“ሮስቶቭ ስደርስ ራሴን ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ አገኘሁት” ይላል። እዚያው ያገኘው ሰው ለሩሲያ ጦር የአንድ ዓመት ኮንትራት መፈረሙን አስረዳው። በጣም ደረገጠ። ግን የሩሲያ ዜግነት እንደሚያገኝ በማሰብ ተጽናና።

“ከአንድ ዓመት በኋላ ሩሲያዊ ዜግነት ከዚያም ገንዘቤን አገኛለሁ። ቤተሰቦቼን ሩሲያ የማምጣት ዕድል ይኖረኛል። በሩሲያ የተሻለ ሕይወት ይኖረኛል።”

በሁለቱም ወገኖች በኩል ቴክኖሎጂ እያደረ ሲሄድ የጦር ግንባሩ አደገኛ እየሆነ እንደሄደ ይናገራል። ቆይታቸው እስካሁን ድረስ የሚረብሻቸው አሉ።

በሌላ መኝታ ክፍል ኬንያዊው ምርኮኛ ኢቫንስ ኪቤት አለ። መጀመሪያ ላይ ሊያናግረን አልፈቀደም። በስዋሂሊ ሳዋራው ግን ተለሳለሰ።

በሌላ መኝታ ክፍል ኬንያዊው ምርኮኛ ኢቫንስ ኪቤት አለ። መጀመሪያ ላይ ሊያናግረን አልፈቀደም። በስዋሂሊ ሳዋራው ግን ተለሳለሰ። ትክክለኛ ያልሆኑ ኤጀንሲዎች ሥራ በማስተዋወቅ ወደ ሩሲያ ሰዎችን አጭበርብረው እየወሰዱ መሆኑ ሲነገር ወላጆች መጨነቃቸውን ሲሰማ ግን ተከዘ። ለሲቪሎች የሚሆኑ ከፍተኛ ደመወዝ በሚከፍሉ ሥራዎች ተታልለው ከሄዱ በኋላ ራሳቸውን የሩሲያ ጦርነት ውስጥ እንደሚያገኙ ሪፖርቶች ሲወጡ ወላጆች ሰምተዋል።

የዩክሬን የደኅንነት መረጃ እንደሚጠቁመው በሩሲያ ጦር ከተመለመሉ አፍሪካውያን ወታደሮች አብዛኞቹ ኬንያውያን ናቸው። በመቀጠል ግብፃውያን፣ ካሜሩናውያን፣ ጋናውያን እና ኡጋንዳውያን ይገኛሉ።

የ36 ዓመቱ ኬንያዊ "ለጦርነት መሰለፍ ቀላል አይደለም። በስተግራም፣ በስተቀኝም፣ ከፊትም ሰዎች ይሞታሉ። ማንም ሰው ግድ አይሰጠውም" ይላል።

የድሮን ጥቃት እንዴት የሰዎችን ሰውነት እንደሚቆራርጥ ይናገራል።

ወታደሮች ወደኋላ ተመልሰው ለመርዳት አይችሉም፤ ወይም ፈቃደኛ አይደሉም። ስለዚህ ወደፊት ይገሰግሳሉ።

በሌላ መኝታ ክፍል ውስጥ ወደሚገኝ ኬንያዊ እየጠቆመ ካሜራ ፊት ማውራት ፈቃደኛ ሊሆን እንደሚችል ጠቆመ።

ዊሊ ማቻሪያ እውነትም ማውራት ያስደስተዋል። ይህም ለምሳ ከመውጣቱ በፊት ነው። "እዚህ ብዙ ምግብ ነው ያለው። በኋላ እበላለሁ።"

በመልክ አውቀዋለሁ። የ23 ዓመቱ ወጣት ኬንያውያን ጦሩን እንዳይቀላቀሉ ሲመክር የሚያሳይ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለተሠራጨ ነው ያወቅኩት።

ስለ ቪድዮው ስጠይቀው በዩክሬናውያን ባለሥልጣናት ተገድዶ እንደቀረጸው ተናገረ።

ስለ ጉዳዩ የዩክሬን ምርኮኞች ማዕከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ቃል አቀባይ ፔትሮ ያታስኖኮን ብጠይቅም ክሱን አስተባብለዋል።

ማቻሪያ እንደሚለው ለሦስት ወራት ጦር ግንባር ነበር። ጥሩ ገንዘብ እንደሚያገኝ እና ትምህርቱን እንደሚቀጥል ቃል ስለተገባለት ወደ ጦርነቱ ገባ። “የምዋጋው ለሩሲያ ነው። ስለዚህ በጠላት እጅ ወድቄያለሁ።”

እንደ ሌሎቹ እስረኞች ጊዜውን የሚያሳልፈው በአነስተኛ ሥራ ገንዘብ በማግኘት ነው። ሳሙና እና ስኳር የሚሸጥበት ኪዮስክ ከፈተ።

በዙሪያው ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመረዳት በእስር ቤቱ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ዩክሬንኛ ቋንቋ እየተማረ ነው። ነጻ መውጣቱን በጉጉት እየጠበቀ ያለው ወጣቱ በቅርቡ በምርኮኞች ልውውጥ ከሚለቀቁ እስረኞች መካከል ስሙ እንደሚኖር እና ወደ ሩሲያ እንደሚመለስ ተስፋ ያደርጋል።

የምርኮኞች ማዕከላት ቃል አቀባዩ በበኩላቸው የእስረኞች ልውውጥ ይደረጋል ብለው አያምኑም። በጦር ምርኮኛነት የተያዙ ዜጎቿን መልሳ ለመውሰድ ፍላጎት ያሳየችው ብቸኛ የአፍሪካ አገር ጋና ናት። ልዑካኖቿ የምርኮኞች ማዕከላትን ጎብኝተው ድርድሮች እየተደረጉ ነው።

“አሁን ላይ በእስረኞች ልውውጥ ውስጥ አፍሪካውያን የሉም። ገንዘባቸውን ስለሚፈልጉ ሩሲያ መሄድ ነው የሚፈልጉት። ሩሲያውያን መልሰው ለመውሰድ ሲሞክሩ ግን አላየንም።”

ፔትሮ ያታስኖኮን
የዩክሬን ምርኮኞች ማዕከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ቃል አቀባይ ፔትሮ ያታስኖኮን

ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዲሪ ሳይቢሃ ጋርም ቃለ ምልልስ አድርጌያለሁ። ሩሲያ የመለመለቻቸውን አፍሪካውያን "የሩሲያ ሕገ ወጥ ድርጊት እና ፕሮፓጋንዳ ሰለባዎች" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

"ሩሲያ ለትምህርት ተጋብዘው ድንገት ራሳቸውን ጦር ሜዳ ያገኙታል" ይላሉ።

ሚኒስትሩ እንደሚሉት የውጭ አገር ዜጎች ለዩክሬንም መዋጋት ይችላሉ። ነገር ግን ሩሲያ እንደምታደርገው ምልመላው ሕገ ወጥ ሳይሆን በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ እና ግልጽነት የተሞላው ነው። ምን ያህል የውጭ አገር ዜጎች ተሳትፈው እንደሆነ መረጃም ሆነ አሃዝ የላቸውም።

እውነታው ግን ያገኘናቸው አፍሪካውያን የጦር ምርኮኞች ወደ ሩሲያ ለመመለስ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ጦርነቱ እስከሚያከትም ድረስ ይህ የሚሆን አይመስልም።

ለቤቨርሊ ጉዳዩ የገንዘብ ብቻ አይደለም። ልጁ ሩሲያ ውስጥ ስለሆነች ቀጥታ ኮንጎ ከሄደ ዳግመኛ ወደ ሩሲያ መመለስ አይችልም።

ካኑ ከዚህ በኋላ በምዕራብ አፍሪካ የወደፊት ተስፋ እንደሌለው እርግጠኛ ነው። “ለሩሲያ ኮንትራት ፈርሜያለሁ። ሩሲያ መመለስ እፈልጋለሁ። ሕይወት ከሴራ ሊዮን ይልቅ ሩሲያ የተሻለ ነው።”

ከዩክሬን ከወጣን በኋላ የካኑን የ19 ዓመት ልጅ ለማግኘት ወደ ፍሪታውን ተጓዝን።

ቤቱ ከብረት ቁርጥራጭ እና ቆርቆሮ ነው የተሠራው፤ ቴንግቤህ ከተማ ይገኛል። ከዚህ የቤተሰቦቿ ቤት በር ላይ ሆና አባቷ እንደናፈቃት ትናገራለች። አባቷን ብትናፍቀውም ግን ወደ ሩሲያ እስከሚመለስ መጠበቅ እንዳለበት እሷም ታምናለች።

“ወደ ሴራ ሊዮን መመለስ አገሩን ጥሎ የሄደባቸውን ምክንያቶች አይለውጥም። የተሻለ ዕድል ያለው ሩሲያ ነው ብዬ አስባለሁ። የተሻለ ገቢ አግኝቶ ሕይወታችንን የሚለውጥበት ዕድል አለው።”

ኤልሲ ካኑ፤ ዕድሜ 19

ተመላሹ

በርካቶች ወደ ቤታቸው መመለስ አይችሉም። ኬንያዊው ደንከን ቼጌ ግን ተመልሷል። የሩሲያ ጦር ውስጥ ሳለ የአእምሮ እክል የገጠመው ሰው መስሎ ሆስፒታል ከገባ በኋላ አመለጠ።

ለቼጌ ብዙ ገንዘብ ታገኛለህ ተብሎ የተገባለት ቃል ማታለያ ነው። ቪዛ ስላላገኘ ዱባይ መሄድ አልቻለም። አንድ ኤጀንሲ ወደ ሩሲያ እንዲሞክር መከረው። በሳምንት ውስጥ የሩሲያ ቪዛ ተሰጠው።

ፎቶ፡ ደንከን ቼጌ

ለጉዞው የሚሆን ገንዘብ ያገኘው እናቱ ከጎረቤታቸው እና ዘመዶቻቸው ተበድረው ነው። ከዚያም መሄጃ ትኬት ብቻ ገዛ።

“ሠርቼ የቤተሰቤን ሕይወት መለወጥ እንድችል ስትል እናቴ ሄጄ እንድሠራ ትፈልግ ነበር።”

ደንከን ቼጌ

ሆኖም ግን የእነዚህ አፍሪካውያን የጦር ምርኮኞች ዕጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ነው

አዘጋጆች

ዘጋቢ፡ ሳሚ አዋሚ, ከምሥራቅ ዩክሬን የተጠናቀረ ዘገባ

ፕሮዲውሰር እና የቪድዮ ጋዜጠኛ፡ ሐሰን ላሊ

ዲዛይን እና ሌይአውት፡ ሚሊ ዋቺራ

የሽፋብ ንድፍ፡ ማዮዋ አላቢ

ሥዕል፡ ጆርጅ ዋፉላ

ምሥሎች፡ ዩክሬን (ጌቲ ኢሜጅስ)፣ ሴራ ሊዮን እና ኬንያ (ሳሚ አዋሚ እና ሐሰን ላሊ)

ጽሑፍ አርትኦት፡ ሉሲ ፍሌሚንግ እና ቪክተር ኦሉች

ፕሮዲውሰር እና የቪድዮ አርታኢ፡ ካቲ ሀርኮምብ

የገጽ አርታኢ፡ ዶሮቲ ኦቲየኖ

ተጨማሪ ድጋፍ፡ ሻሎም ኦላቱንጂ፣ ብሪያን ኦስዌታ፣ ንጆሮጌ ሙጋይ፣ ቦኤዝ ኦቺየንግ እና ዳሚሎላ ኦጄቱንዴ

የታተመበት ቀን፡ ሰኔ 2/2018 ዓ.ም.